#ET

#ET


የደቡብ ክልል የ2012 በጀት አለመጽደቅ ውዝግብ አስነሳ!

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ላለፉት ስምንት ወራት መሰብሰብ ባለመቻሉ የክልሉን በጀት ያላፀደቀ ሲሆን የ2011 በጀት ላይ በመመስረት የአንድ ወር በጀት ብቻ ታስቦ መለቀቁ የዋጋ ግሽበትን ያላማከለ እና የዞን አመራሮችን ጫና ውስጥ የከከተ ነው ተባለ።

‹‹የተለቀቀው አንድ አስራ ሁለተኛ በጀት ያለፈው አመት ቀመር ላይ በመመስረቱ መደበኛ ስራዎችን ለማከናወንም ሆነ ለአስቸኳይ ወጪዎች በቂ አይሆንም፡፡ በተጨማሪም ገንዘቡ የግብር ከፋዩ ገንዘብ እንደመሆኑ ይህንን መከልከል አግባብነት የለውም›› ሲሉ የወላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ (ወብን) የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ተከተል ላቤና ለአዲስ ማለዳ ገለፀዋል።

የክልሉ ፕሬስ ሴክሪታሪያት ኀላፊ ፍቅሬ አማን በበኩላቸው የመንግስት ሰራተኞችን ደመወዝ ለመክፈል፣ መደበኛ ስራዎችን ለማስኬድ እንዲሁም አስቸኳይ ስራዎችን ለማከናወን ጊዜያዊ በጀቱ በቂ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አክለውም ክልሉ የገቢ ግብር ማሰባሰብ ስራውን በማካሄድ ላይ መሆኑን ገልጸው የገንዘብ እጥረት አይኖርም ብለዋል፡፡

ምክር ቤቱ በየትኛውም አይነት ሁኔታ ተሰብስቦ መደበኛ ስራውን መስራት በአዋጅ የተሰጠው ተግባሩ ነው ያሉት የወብን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ይህንን ስራውን በተቀመጠለት ጊዜ ገደብ ማከናወን አለመቻሉም አግባብ አይደለም ሲሉ ይተቻሉ፡፡

‹‹የክልሉ መንግስት ዋና ትኩረት ባለፉት ወራት ተነስተው የነበሩ የፀጥታ ችግሮችን በማስተካከል ላይ ነው›› ያሉት ፍቅሬ ‹‹የበጀት አመቱ ሐምሌ አንድ እደጀመረ ይታወቃል፤ ነገር ግን በጀቱን ከማፅደቅ መፊት የመዋቅር ማሰናዳት ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

በ2011 በጀት ዓመት የደቡብ ክልል በጀት 37.9 ቢሊየን ብር ነበር። ይህም የኦሮሚያ ክልል በያዝነው በጀት ዓመት ካፀድቀው በጀት ግማሽ ሲሆን የትግራይ ክልል ካጸደቀው በጀት ዕጥፍ ነው። ለ2011 በጀት ዓመት የህዝብ ተወካዮች ለዘላቂ ልማት ማስፈፀሚያ ድጋፍ በፌዴራል መንግስቱ ለክልሎች ከተመደበው ስድስት ቢሊየን ብር ውስጥ 20 በመቶው ለደቡብ ክልል የፀደቀ ሲሆን ይህም ለአማራ ክልል ከተመደበው ጋር የሚስተካከል ነው።

የደቡብ ክልል 13 ዞኖችና ስምንት ልዩ ወረዳዎች፣ 126 ወረዳዎችና 3678 የገጠር ቀበሌዎችን በስሩ አቅፎ ይገኛል። በተጨማሪም 22 የከተማ አስተዳደሮች እና 114 ምስክርነት ያገኙ በማዘጋጃ ቤት የሚተዳደሩ ከተሞች ያሉት ሲሆን በሥራቸው 238 የከተማ ቀበሌዎችን ይዘዋል። አጠቃላይ የክልሉ የህዝብ ብዛት ከ20 ሚሊየን በላይ ሲሆን 50.2 በመቶው ሴቶች ሲሆኑ 91 በመቶ የሚሆነው የክልሉ ሕዝብ በገጠር የሚኖር ነው።

የበጀት መዘግየቱ ፖለቲካዊ አንድምታ አለው የሚሉት ተከተል ‹‹ከዞኖች ለሚነሱ የክልል መሆን ጥያቄዎች እንደመደራደሪያ እየታየ ነው፣ ይህንንም ተከትሎ የተነሱ ሕገ መንግስታዊ ጥያቄዎችን ወደ ጎን እንዲሉ ጫና ለማሳደር የተደረገ ነው›› ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ ‹‹የዞን አመራሮች የህዝቡን ጥያቄ ይዘው በማቅረባቸው የዘገየ በጀት በመሆኑ የዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ ጫና ያመጣል፡፡››

ተከተል እንደሚሉት በጀቱ ከዚህ በላይ ሳይፀድቅ የሚቆይ ከሆነ ደመወዝ መክፈል የማይቻልበት ደረጃ ላይ ስለሚደርስ ዞኖች ወደ በጀት አቅራቢው እጅ እንዲያዩ እና ህዝቡም የዳቦ ጥያቄን ከመብት ጥያቄ እንዲያስበልጥ ይገፋፋል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልፃሉ፡፡

‹‹ የተመደበውን በጀት ለሁለት ወር የተጠቀምን ሲሆን በቅርቡም ምክር ቤቱ ተጠርቶ ወደ መደበኛ ስራው ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል›› ሲሉ የክልሉ ፕሬስ ሴክሪታሪያት ፍቅሬ በበኩላቸው አስታውቀዋል፡፡

በኮማንድ ፖስት እየተዳደረ የሚገኘው የደቡብ ክልል ከሶስት ሳምንት በፊት የክልል እንሁን ጥያቄ ወደ ግጭት እና ኹከት አምርቶ ለሰዎች ህይወት መጥፋት፣ ለንብረት ውድመት እና በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች መታሰር ምክንያት መሆኑ ይታወሳል፡፡ በዚህም ምክንያት ከልሉ በተለይም የሐዋሳ ከተማ በከፍተኛ የስራና የንግድ እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ ውስጥ ይቀኛሉ፡፡

የደኢህዴን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሃምሌ 21/2011 ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በሲዳማ ዞን ለተከሰተው ችግር ድርሻ አላቸው ያላቸውን አመራሮች ከስራ አግዷል። ተመሳሳይ የእግድ እርምጃም በሃዲያ ዞን ከፍተኛ አመራሮች ላይ ወስዶ የወላይታ እና ከፋ ዞን አመራሮችንም ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። በመግለጫውም በክልሉ የሚነሱትን የክልልነት ጥያቄዎች የሚመለስበት አግባብ ላይ ግልጽ አቅጣጫ በድርጅቱ ጉባዔ መቀመጡን አስታውቋል፡፡

የደቡብ ክልል ከኢትዮጲያ ህዝብ 20 በመቶ የሚሆነውን የያዘ ሲሆን በህዝብ ብዛትም ከኦሮሚያና አማራ ክልሎች በመቀጠል በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

#አዲስማለዳ

Report Page