#ET

#ET


በ2012 ዓ.ም ወደ መንግሥትም ሆነ የግል ዩኒቨርሲቲዎች የሚገቡ አዲስ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ትምህርት የሚጀምሩት በ15 አዳዲስ ትምህርቶች መሆኑን የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ አስታወቀ። በሦስት ዓመታት ይጠናቀቅ የነበረው የዲግሪ ፕሮግራም ወደ አራት ዓመት ከፍ ብሏል።

ዩኒቨርሲቲዎቹ በ2012 ዓ.ም ለመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች የሚሰጡት ክሪቲካል ቲንኪንግ፣ ሂስትሪ(ታሪክ) ኤንድ ዘሆርን፣ ጂኦግራፊ ኤንድ ዘሆርን፣ አንትሮፖሎጂ፣ ሳይኮሎጂ፣ ሂሳብ እና ሌሎቹም ለሁሉም የሚሰጡ የጋራ (ኮመን ኮርሶች ) ሲሆኑ ይህም ተማሪዎች በአስተሳሰብ ምጡቅ እንዲሆኑ፣ ብዝሀነትን፣ የሀገርን ባህል፣ አገር በቀል ዕውቀቶችንና ታሪክ እንዲያውቁ የሚያደርጉ ናቸው።

 የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዱአለም አድማሴ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት፣ ስነምግባር እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በሚመለከት የሀገሪቱ የትምህርት ስርዓት እንዴት ይቃኝ በሚለው ላይ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በምሁራን ሰፊ ጥናት ሲደረግና በርካታ ህዝብም ሲወያይበት ቆይቷል። ይሄንኑ መነሻ በማድረግም ብዙ ማሻሻያ እና ለውጦች ተደርገዋል።

በዚሁ መሰረት በ2012 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለሚገቡ ተማሪዎች አዳዲስ ኮርሶችን መስጠት እንዲችሉ ስምምነት ላይ ተደርሶ ለዚሁ ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው፣ አሁን ያለው ሁኔታ ትምህርቱን ለመጀመር የሚቻል ነው ብለዋል።

ትምህርቱን መስጠት ከተጀመረ በኋላም ኤጀንሲው የሬጉሌሽን ሥራዎችን እንደሚሠራ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የትምህርት ጥራቱ ምን ይመስላል? ጥራቱን ጠብቆ እየሄደ ነው ወይ? የሚሰጠው ትምህርት አስፈላጊና ለሀገሪቱ ተገቢ ነው ወይ? የሚለውን የሚገመገም መሆኑን ገልጸዋል። እስከአሁን በነበረው ሂደት የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ተሳታፊ እንደነበሩ ጠቅሰው፣ በሚጀመሩት የትምህርት ዓይነት እና በተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ቆይታ ጊዜ ላይ በመግባባት ወደ ሥራ መገባቱን አስታውቀዋል። ይህም ተግባራዊ የሚሆነው በሀገሪቱ ባሉ የግልም ሆነ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች መሆኑን አረጋግጠዋል።

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፋሲል ተሊል በበኩላቸው እንዳሉት በሚቀጥለው ዓመት የሚሰጡት አዳዲስ ‹‹ኮመን ኮርሶች›› ሰብዕናን የሚገነቡ፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ብዝሀነትን የሚያሳውቁ እንዲሁም ክሪቲካል ቲንኪንግ (ሚዛናዊ እይታ) እንዲኖር የሚያስችሉ፣ የሂሳብ እና እንግሊዝኛ ትምህርቶችን የሚያጠቃልሉ ናቸው።

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በነበረው ሂደት ዕውቀትና ክህሎቱ እንዳለ ሆኖ በትምህርት ጥራት በተለይም በሰብዕና ግንባታ ላይ በጣም የሚያስፈልጉና የጎደሉ ኮርሶች እንደነበሩ አስታውሰው፣ በዚህ ዙሪያ በሀገር አቀፍ መድረኮች በጋራ በመምከርና በጥናት በማረጋገጥ አዳዲስ ኮርሶች እንዲካተቱ መደረጉን አስታውቀዋል። እነዚህን ኮርሶች በትምህርት ፕሮግ ራሙ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልጉ የግብአት አቅርቦት እና መምህራን የማሟላት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

“ ከሰብዕና ግንባታና ከሞራል ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል ይሰጥ የነበረው የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት ተማሪው መብቱን አውቆ መብቱን ጠያቂ እንጂ ከራሱ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ የሚያደርግ አልነበረም” ያሉት ዶክተር ፋሪስ፣ ከዚህ አንጻር አሁን እንዲካተት የተፈለገው አዳዲሱ ኮርስ ግብረ ገብነትን የሚመለከት፣ ከባህልና ከእምነት ጋር ተያይዞ ተማሪው በስነ ምግባር የታነፀ / ዲስፕሊንድ/ እንዲሆን የሚያደርገው ነው። በተለይ ዋና ዋና በሚባሉ የሳይንስ ኮርሶች የሂሳብ ትምህርት ላላፉት በርካታ ዓመታት መስጠት ቆሞ እንደነበር አንስተው፣አሁን ግን ለመጀመሪያ ዓመት ለሁሉም ተማሪዎች ይሰጣል ብለዋል።

ይሄ ተማሪው ወደፊት ለሚማረው ትምህርት በቂ ዝግጅት እንዲያ ደርግ የሚያግዝ በመሆኑ መካተቱ አግባብነት ያለው መሆኑን ገልጸዋል። ተማሪዎች ስርዓተ ትምህርቱን ከመረዳትና ራሳቸውንም ከመግለጽም አንጻር የቋንቋ ክህሎታቸው በጣም እየወረደ የመጣ መሆኑን ጠቅሰው፣የእንግሊዝኛ የመናገር እና የመጻፍ ክህሎት እንዲማሩ የሚደረግ መሆኑን አስረድተዋል።

ተማሪዎች የሀገራቸውን ባህልና ታሪክ እንዲያ ውቁ የሚያደርግ “ሂስትሪ፣ ኢትዮጵያ ኤንድ ዘ ሆርን”፣ ሳይኮሎጂ እና አንትሮፖሎጂ ኮርስ ተካቷል። እነዚህ ኮርሶች ተማሪዎች ሀገራቸውን፣ ባህላቸውንና ታሪካቸውን በደንብ እንዲያውቁ የሚያደርጉ ናቸው። ካለፈው ታሪክ ተምረው ለወደፊቱ ጠንካራና ሀገር ተረካቢ ትውልድ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህ የሚያስፈልጉ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ግብአት የማሟላት ሥራ እየሠራን እንገኛል ብለዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን በበኩላቸው እንዳስታወቁት የ2012 ዓ.ም የተማሪዎች አቀባበል ቅድመ ዝግጅት ሥራ እየሠራን ነው። የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች 38 ክሬዲት ያላቸው 15 የሚሆኑ ‹‹ኮመን ኮርሶችን›› ይወስዳሉ። ይህም ስምንቱ በመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት ሲሆን፣ ሰባቱ በሁለተኛ መንፈቅ ዓመት የሚሰጡ ይሆናል። እነዚህ የተማሪው የብስለት መገምገሚያ ኮርሶች ናቸው። ለዚህ የሚያስፈልጉ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ ሲሆን ለሚጀመሩት ትምህርቶች አስፈላጊ የሆኑ መምህራንን በቅጥርና በዝውውር የማሟላት ሥራ ተጀምሯል።

አብዛኛው ከኢንጂነሪግ እና ከጤና ትምህርት ውጪ በርካታ የትምህርት ክፍሎች የማሸጋሸግ ሥራ እንደሚሠራ የተናገሩት ዶክተር አባተ፣ ሦስት ዓመት የነበሩት ወደ አራት ዓመት ከፍ ይላሉ። አምስት እና ስድስት ዓመት ይማሩ የነበሩትን ግን አላስፈላጊ የነበሩ ኮርሶችን በመቀነስ ጊዜውን በዚያው የማስተካከል ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል። የእንግሊዝኛ ትምህርት ክፍል አንድ እና ክፍል ሁለት ያለው ሲሆን፣ ሌሎች ትምህርቶች ግን ቅደም ተከተል ሳይኖራቸው የሚሰጡ ይሆናሉ ብለዋል።

መቻቻል፣ ሰላም፣ ብዝሀነት፣ የጋራ ታሪክ እና የጋራ ሀብት እንዲያውቁ በጋራ ነገሮቻችን ላይ በጋራ የምንዘምርበት፤ ለሁሉም ዜጋ የሚጠቅሙ ትምህርቶችን በመጀመሪያው ዓመት ማስተማር በቀጣይነት ለሚማሩትም ትምህርት ብስለትን የሚጨምር መሆኑን አስረድተዋል። ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ያለውን የትምህርት አሰጣጥ የሚለውጠው የኢትዮጵያ ትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ጥናት የተጠናቀቀ ሲሆን ነገ በሸራተን አዲስ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አዲስ ዘመን ነሀሴ 12/2011


Report Page