#et

#et


ከሕዝብ ቁጥር መጨመርና ከከተሞች መስፋፋት ጋር በተያያዘ የድምፅ ብክለት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሄዱ ችግሩን ለመቆጣጠር የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ደንብ እያረቀቀ መሆኑን አስታወቀ።

መቐለና አዲስ አበባ በድምፅ ብክለት ቀዳሚዎቹ ከተሞች መሆናቸውን አመልክቷል።

ኮሚሽኑ በረቂቅ ደንቡና በአገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ያሉበትን የድምፅ ብክለት ደረጃ እንዲሁም ችግሩን ለመፍታት መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች ከባለ ድርሻ አካላት ጋር እየተወያየ ይገኛል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ከሕዝብ ቁጥር መጨመርና ከከተሞች መስፋፋት ጋር በተያያዘ የድምፅ ብክለት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል።

ከትራንስፖርት አገልግሎት፣ ማምረቻ ተቋማት፣ ንግድና መኖሪያ ቤቶች፣ ሐይማኖትና መሰል ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች የሚመነጭ የድምፅ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ፕሮፌሰሩ አብራርተዋል፡፡

አብዛኞቹ ከተሞች ላይ ከፍተኛ የድምፅ ብክለት እየተስተዋለ እንደሚገኝ ባለፉት ዓመታት የቀረቡ ሪፖርቶችና የዳሰሳ ጥናቶች መጠቆማቸው ተገልጿል ።

በመሆኑም ችግሩን ለመፍታትና ከዚህ በፊት የወጣውን የአካባቢ ብክለት ስታንዳርድ ለማስከበር ኮሚሽኑ ክትትል ከማድረግ ባሻገር የድምፅ ብክለት ቁጥጥር ደንብ በማርቀቅ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የኮሚሽኑ የድምፅ ብክለት ባለሙያ አቶ እንዳሻው ግርማ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ የድምፅ ብክለት በሕብረ ተሰብ ጤናና ኢኮኖሚ ላይ የተለያዩ ችግሮችን ያስከትላል። ኮሚሽኑ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት እንዲሁም ቁጥጥርና ክትትል የመቐለና አዲስ አበባ ከተሞች በድምፅ ብክለት ቀዳሚ ናቸው።

የመቐለ ከተማ ካለው የቆዳ ስፋትና ካለው የድምፅ ብክለት ልኬት አኳያ ቀዳሚ ደረጃ ሊይዝ የቻለው በጭፈራ ቤቶችና ሆቴሎች ላይ በሚወጡ ድምፆች በተደረገው ጥናት መሰረት ነው።

ተከታዩን ደረጃ የያዘው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲሆን በተደረገው ክትትል ከ354 የማምረቻ ተቋማት፣ ኢንደስትሪዎች፣ የመጠጥና ምግብ ቤቶች እንዲሁም ጭፈራ ቤቶች ከ250 በላይ በሚሆኑት የእርምት እርምጃ ተወስዷል።

ረቂቅ ደንቡን ያቀረቡት በኮሚሽኑ የፖሊሲ፣ የህግና ደረጃዎች ጥናት ዝግጅት ዳይሬክቶሬት የፖሊሲ ዝግጅት ባለሙያው አቶ ዮሐንስ ዘይኑ፣ ረቂቅ ደንቡ የብክለት አዋጅ 300/2002 ዓ.ም መሰረት አድርጎ እንደረቀቀና የድምፅ ብክለትን ለመቆጣጠር እንደሚረዳ ተናግረዋል።

በረቂቅ ደንቡ የድምፅ ብክለትን ለመቆጣጠር አራት ቀጠናዎች የተለዩ ሲሆን የመኖሪያ፣ የኢንደስትሪ፣ የንግድና የቅይጥ ተብለው እንደተለዩ አቶ ዮሐንስ አስረድተዋል።

የቅ ይጥ ቀጣና ተብሎ የተለየው የመኖሪያ፣ ኢንደስትሪና የንግድ አካባቢዎችን አጣምሮ የያዘ መሆኑንም ገልፀዋል።

ረቂቅ ደንቡ ማንኛውም አካል ከውጭ አገር የድምፅ ብክለትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ቴክኖሎጂን ለማስገባት ፍላጎት ካለው ቴክኖሎጂውን በምን አይነት መልኩ ማስገባት እንዳለበትና ሌሎች የማበረታቻ ድንጋጌዎችን መያዙን አቶ ዮሐንስ ተናግ ረዋል።

በረቂቅ አዋጁ በየቀጠናዎቹ የሚቀመጡ የድምፅ ብክለት ደረጃዎች ያሉ ሲሆን ደረጃዎቹን የሚተላለፍ ማንኛውንም አካል ተጠያቂ የሚያደርግ መሆኑን አስገንዝበዋል።

#ETV

Report Page