#ET

#ET


“በኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በቡራዩ ቅርንጫፍ ለአራት ዓመታት ስማር ቆይቻለሁ። የተማርኩት ለማወቅ ብቻ ሳይሆን ዲግሪ አግኝቼ በሥራዬ ዕድገት ለማግኘትና ለመሻሻል ነበር” የሚሉት አቶ ገመቹ ዳባ፤ ትምህርቱን ሲያጠናቅቁ ያልገመቱትን ‘ዲግሪ አይሰጥህም’ የሚል ምላሽ ማግኘታቸውን ይናገራሉ።

እንደ አቶ ገመቹ ገለፃ፤ ትምህርቱን ለአራት ዓመታት ሲከታተሉ ዲግሪ ከተሰጣቸው ጓደኞቻቸው የተሻለ ውጤት ሲያስመዘግቡ ቆይተዋል። ሆኖም ትምህርቱን ሲያጠናቅቁ ጓደኞቻቸው ዲግሪ ሲሰጣቸው ለእርሳቸው እና ለተወሰኑ ሰዎች “ቀድሞ ስትመዘገቡ መስፈርቱን አታሟሉም ነበር” በሚል ሰበብ ዲግሪ አይሰጣችሁም ተብለዋል።

ምንም እንኳን የአስራሁለተኛን ክፍል ብሔራዊ ፈተና አልፈው ዩኒቨርሲቲ ባይገቡም በቴክኒክና ሞያ ኮሌጅ በመማር የደረጃ ሦስትን የትምህርት ብቃት ምዘና ሲኦሲወስደው አልፈዋል።

ዩኒቨርሲቲውም በዲግሪ መርሐ ግብር መማር ትችላለህ ብሎ የመዘገባቸው፤ ይህንን መስፈርት እንደመግቢያ በመውሰድ እና ዩኒቨርሲቲው ያዘጋጀውንተጨማሪ የመግቢያ ፈተና በማለፋቸው ነበር። አሁን ከአራት ዓመታት በኋላ ግን ‘በወቅቱ የተመዘገባችሁበት መስፈርት ትክክል ባለመሆኑ ዲግሪውን አታገኙም’ መባሉ እጅግ አስደንግጧቸዋል።

“ለባከነው ጊዜና ገንዘብ ተጠያቂው ማን ነው” ካሉ በኋላ፤ ዩኒቨርሲቲው የፈለጋችሁትን ውጤት ብታስመዘግቡም ዲግሪውን አንሰጣችሁም ማለቱን ተናግረዋል።

ሌላው ስሙ በሌላ እንዲተካልት የጠየቀን ወጣት ቴዎድሮስ አየለምእንደአቶ ገመቹ ሁሉ ዲግሪውን እንደተከለከለ ገልፆ፤ “ተማሪዎች ለዲግሪ መስፈርቱን አታሟሉም መባል ያለባቸው ትምህርቱን ከጨረሱ በኋላ ሳይሆን መጀመሪያውኑ ሳይመዘገቡ በፊት መሆን ነበረበት” ይላል።

እንደወጣቱ ገለፃ፤ ወደ ዩኒቨርሲቲው ለመግባት ሲመዘገቡ የመግቢያ ፈተና ከወሰዱ በኋላ ያንን አልፈውና ለደረጃ ሦስት የትምህርት ብቃት ምዘና ሲኦሲ ማለፋቸው ተረጋግጦ መስፈርቱን ታሟላላችሁ ተብለው ገብተው ተምረዋል።

ዩኒቨርሲቲው መስፈርቱን ታሟላላችሁ ብሎ አስተምሮ ከጨረሰ በኋላ ተማሪዎቹ ዲግሪያቸውን ሊቀበሉ ሲሄዱ በተሰጣቸው መልስ ‘እንደገና ለአንድ ዓመት ደረጃ አራትን ተምራችሁ ትፈተናላችሁ፤ ካላለፋችሁ ዲግሪያችሁ አይሰጣችሁም’ መባሉ ግራ እንዳጋባቸው ተናግሯል።

ተማሪ ቴዎድሮስ “ከኛ በፊት የተመረቁት ልክ እንደኛው የደረጃ ትን የትምህርት ብቃት ምዘና ሲኦሲየወሰዱ መሆናቸውን ሰምቻለሁ።” ይላል። አሁን ዲግሪው ከተከለከለ ለተፈፀመው ጥፋት ዩኒቨርሲቲውም ተጠያቂ መሆን እንዳለበትም አመልክቷል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ገመቹ አራርሳ በበኩላቸው፤“በደረጃ ሦስት ለዲግሪ ሲማሩ የነበሩ ተማሪዎች ዲግሪ አንሰጣችሁም የተባሉት ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣውን የዲግሪ መመዝገቢያ መስፈርት የማያሟሉ በመሆናቸው ነው፤” ይላሉ።

አንድ ሰው በዩኒቨርሲቲ ለዲግሪ መማር የሚችለው በአገር አቀፈ ደረጃ በወጣው መስፈርት መሰረት ኛ ክፍል ደርሶ ባስመዘገበው የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ውጤት ወይም በበፊቱ ሥርዓተ ትምህርት ዲፕሎማ ያለው፤ ወይንም በደረጃአራትየትምህርት ብቃት ምዘና ሲኦሲካለፈ ብቻ ነው። ይህንን ዩኒቨርሲቲዎችም ሆኑለመማር የሚሄዱ ተማሪዎች ማወቅ እንደሚጠበቅባቸው ይናገራሉ።

በአሁኑ ሰዓት በኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ አዲስ አመራር የተመደበ ሲሆን፤ የተመራቂ ተማሪዎች ለዩኒቨርሲቲው ሴኔት ሲቀርቡ የዩኒቨርሲቲውን መግቢያና መውጫ ፈተና ማለፋቸው ብቻ ሳይሆን፤ ተመራቂዎቹ ሲመዘገቡ ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣውን መስፈርት ስለማሟላታቸው ሲጣራ ያላሟሉ ተማሪዎች በመገኘታቸው መመረቅ የለባቸውም ተብሎ ውሳኔ ተላልፏል።

እንደፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ ተማሪዎቹ ቀድሞም ቢሆን መስፈርቱን ሳያሟሉ መመዝገብ አልነበረባቸውም። ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም። ስለዚህ ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣውን መስፈርት ያላሟሉ ተማሪዎች ዲግሪ ሊሰጣቸው እንደማይገባ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት በግልጽ ወስኗል።

“እውነት ለመናገር ወደ ኋላ ሲጣራ ተማሪዎቹ የተሳሳተ መረጃ ተሰጥቷቸዋል። በወቅቱ የወጣው ማስታወቂያም ግልጽ አልነበረም።” የሚሉት ዶክተር ገመቹ፤ ስህተቱን የፈጠሩት የመዘገቧቸው ግለሰቦችና ተመዝጋቢተማሪዎቹእንጂ ተቋሙ አይደለም ይላሉ።የተፈጠረውን ስህተት በመግለጽጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ሲነገራቸው፤ ዲግሪው ከተሰጣቸውዩኒቨርሲቲውንም ሆነ ተማሪዎቹን ተጠያቂ የሚያደርግ መሆኑን በመናገራቸው ውሳኔ ላይ መደረሱን አመልክተዋል።

ነገር ግን ተማሪዎቹን ያሳሳቷቸው ቡድኖች በመኖራቸው ጉዳያቸው ይታይ የሚል ውሳኔ ላይ ተደርሷል። ከትምህርት ሚኒስቴር፤ ከዩኒቨርሲቲው፤ ከኦሮሚያ ቴክኒክና ሙያ፤ እንዲሁም ከኦሮሚያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የተወጣጣ ኮሚቴ በማዋቀር በወቅቱ የመዘገቡትን ተጠያቂ ከማድረግ አልፎ በዩኒቨርሲቲው ቦርድ በተወሰነው መሰረት ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሄደው የደረጃ አራትን የትምህርት ብቃት ምዘና ከተፈተኑ በኋላ ላለፉት ብቻ ዲግሪ እንዲሰጥ ብቻ የታሰበ መሆኑን ተናግረዋል። ለዚህም ሲባል የማጠናከሪያ ትምህርት ተሰጥቷቸው እንዲፈተኑ ዩኒቨርሲቲው እየተዘጋጀ መሆኑን አመልክተዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዷለም አድማሴ በሰጡት ምላሽ ጉዳዩ ወደ ተቋማቸው እንዳልመጣና እንደማያውቁት ገልጸው፤ ሆኖም ዩኒቨርሲቲው ለመዘገባቸውና ላስተማራቸው ተማሪዎች የትምህርት ማስረጃ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት አመልክተዋል።

በዚህም ማንኛውም ተቋም ተማሪዎችን ሲመዘግብ መጀመሪያ መስፈርቱን ማሟላታቸውን ማጣራት ያለበት መሆኑን አስታውሰው፤ ከመዘገበ ደግሞ ማስረጃቸውን የመስጠት ግዴታ አለበት፤ ሆኖም አየር ላይ መዝግቦ አስተምሮ ማስረጃ መከልከል ግን በፍጹም የማይቻል ነው ብለዋል።

 አዲስ ዘመን ነሃሴ 10/2011


Report Page