#ET

#ET


አንዲት ግለሰብ ባሕር ዳር ውስጥ በሚገኘው የክልሉ የመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ውስጥ በሚሰሩ ኃላፊ ላይ አሲድ በመድፋት ጥቃት ፈጽማ ጉዳት እንዳደረሰችባቸው ፖሊስ ለቢቢሲ ገለጸ።

ድርጊቱ የተፈጸመው ነሐሴ 02/2011 ዓ.ም ጠዋት ላይ ሲሆን ግለሰቧ ባሕር ዳር በሚገኘው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ የስምሪት ዳይሬክቶሬት ዳይሬከተሩን ለማግኘት እንደምትፈልግ ብትገልጽም ኃላፊው ስብሰባ ላይ እንደሆኑ ተገልጾላት ትመለሳለች።

ግለሰቧ በድጋሚ በዚያኑ ቀን ከሰዓት በኋላ ተመልሳ ወደ ኃላፊው ቢሮ እንደመጣች በባሕር ዳር ከተማ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ የምርመራ የሥራ ሂደት አባል የሆኑት ምክትል ኢንስፔክተር ይስማው ታሪኩ በዕለቱ የተፈፀመውን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ግለሰቧ በ2008 ዓ.ም በህጋዊ መንገድ 'እፎይታ' በሚባል ማህበር የተመዘገበ ባጃጅ መግዛቷን እና በዚህም ለተወሰነ ግዜ የስምሪት መርሃ ግብር ወጥቶላት ባጃጇ በሥራ ላይ ተሰማርቶ መቆየቱን ተናግረዋል።

ኢንስፔክተር ይስማው ጨምረውም "በኋላ ላይ ተጠርጣሪዋ 'ምክንያቱን አላውቀውም' በምትለው ሁኔታ የማህበሩ ታፔላ እንዲነሳ ተደርገ፤ ባጃጇም እንድትያዝ ተደረገች" ይላሉ።

ግለሰቧ ይህ እንዲሆን ያደረገው ቀደም ሲል የባሕር ዳር መንገድ ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት እና አሁን የክልሉ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የስምሪት ዳይሬክቶሬት ዳይሬከተር የሆኑት አቶ ደመላሽ ስንሻው ናቸው ብላ ማሰቧን ፖሊስ ተናግሯል።

በድርጊቱ የተጠረጠረችው ግለሰብ ለፖሊስ ቃሏን እንደሰጠችው፤ ጥቃቱን ለመፈጸም አሲድ ገዝታ ነሐሴ 2 ቀን ጠዋት ወደ አቶ ደመላሽ ቢሮ ብትሄድም ስብስባ ላይ ናቸው ስለተባለች ተመልሳለች።

ከሰዓት በኋላ ስትመለስ ግን አቶ ደመላሽን ቢሯቸው ውስጥ ሥራ ላይ እንዳሉ ታገኛቸዋለች። ከዚያም ተጠርጣሪዋ በጆግ ይዛው የመጣችውን አሲድ ከቅርብ እርቀት ላይ ሆና በግለሰቡ ላይ እንደደፋችና ምን እንደተከሰተ መለስ ብላ ሳታይ እየሮጠች መውጣቷን ለፖሊስ ቃሏን ሰጥታለች።

ተጠርጣሪዋ ድርጊቱን ፈጽማ ለማምለጥ ብትሞክርም በአካባቢው በነበሩ ሰዎች ትብብር በቁጥጥር ሥር የዋለች ሲሆን ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ግለሰብም ወዲያውኑ ወደ ሐኪም ቤት ተወስደው ህክምና እንዲያገኙ ተደርጓል።

የተደፋባቸው አሲድ ሙሉ ለሙሉ ሰውነታቸው ላይ ስላላረፈ በግለሰቡ ላይ የከፋ ጉዳት እንዳላደረሰ የተገለጸ ሲሆን፤ ነገር ግን አሲዱ በተጎጂው ሁለት እጆች ላይ በማረፉ እጃቸው መጥቆር እና እብጠት፣ ሆዳቸው ላይ የመጥቆር ምልክቶች እንዲሁም በፊታቸው ላይም አልፎ አልፎ የመቃጠል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ተጠርጣሪዋ ጥቃቱን ለመፈጸም የተጠቀመችበትን አሲድ ለመኪና ባትሪ በሚል እንደገዛችው ለፖሊስ የተናገረች ሲሆን ፖሊስም የአሲዱን ምንጭ ለማወቅ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ተናግሯል።

ጥቃቱ የተፈጸመባቸው አቶ ደመላሽን በሥራቸው ግለሰቧን ኢላማ እንዳላደረጉና ሌሎችም ከስምሪት ቦታቸው ውጪ የሚሰሩ ባጃጆችን ሥርዓት ለማስከበር ሲባል ሌሎችም እንደተያዙ ለፖሊስ ተናግረዋል።

ፖሊስ በአሁኑ ወቅት የተጠርጣሪ እና የተጎጂን ቃል እንዲሁም ሌሎች ማስረጃዎችን እንዳሰባሰበና አስፈላጊውን ማስረጃና ምስክሮችን አሟልቶ መዝገቡ በፍጥነት እንዲታይ ወደ ባሕር ዳር ፍትህ ጽህፈት ቤት መላኩን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ጥቃቱ የተፈጸመባቸው አቶ ደመላሽ ስንሻው እያደረጉ የነበረውን የህክምና ክትትል አጠናቀው ከሆስፒታል መውጣታቸውን አረጋግጠናል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ


Report Page