#ET

#ET


በቀን 06/12/2011 ዓ.ም በቁጥር ፐረ/1 /20578 በተፃፈ ደብዳቤ በአዲስ አበባ ቦሌ ለም አቀፍ አየር ማረፊያ አዲስ በተገነባው የመንገደኞች ማስተናገጃ ቁጥር 2 (Terminal 2) ማስፋፊያ ላይ ያወጣነውን ጨረታ አስመልክቶ ቅሬታ መቅረቡንና በቀረበው ቅሬታ ላይ ዘገባ ለመሥራት መረጃ በጠየቃችሁን መሠረት የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተናል።

የጨረታ መመሪያው አየር መንገዱ ብቻ የሚጠቀምበት ተቋማዊ ሰነድ በመሆኑ ግልባጭ ለመስጠት የምንቸገር መሆኑን እየገለጽን ነገር ግን መመሪያውን በተመለከተ አስፈላጊና ሙሉ ማብራሪያ የምንሰጥ መሆኑን በአክብሮት እንገልፃለን። ከዚህ ጋር በተያያዘ በሁለቱ ዙር የተዘጋጁትን የጨረታ ሰነዶች ቅጂ ከዚህ ደብዳቤ ጋር አባሪ አድርገን የላክን መሆኑን እንገልጻለን።

በተጨማሪም ለቦታ ኪራይ ጨረታ መሰረዝ በተመለከተ ከተጫራቾች ለቀረቡ ጥያቄዎች የተሰጠውን ምላሽ 2 ገጽ አባሪ በማድረግ አያይዘናል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጨረታ ዋና ዓላማ በግልጽ አሰራር ሂደት ከፍተኛ ፉክክርና ውድድር በተጫራቾች መካከል እንዲኖርና በዚህም መሰረት ለአየር መንገዱ የተሻለ ዋጋ፣ ጥራትና በተቀላጠፈ ጊዜ (best combination of price,quality and time) ማግኘት ነው። በመጀመሪያው ዙር የጨረታ ማስታወቂያው በአዲስ ዘመን፣ በኢትዮጵያን ሄራልድ እንዲሁም በአየር መንገዱ ድረ ገጽ የወጣ ሲሆን፣ ተጫራቾች ባቀረቡት የማብራሪያ ጥያቄዎች መሠረት ማብራሪያ ተሰጥቷል፤ ተጫራቾች የጨረታ ሰነዱን ለማዘጋጀት ተጨማሪ ጊዜ በጠየቁት መሠረት ጨረታው ለ14 ቀናት እንዲራዘም ተደርጎ ተዘግቷል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የግዥ መመሪያና ሂደት መሠረት የጨረታ ጠቅላላ ውጤት የሚታወቀው የቴክኒካል እና የፋይናንሻል ግምገማ የድምር ውጤት ከታየ በኋላ በመሆኑ ምንም እንኳን በቂ የሚባል ተጫራች በመጀመሪያ ዙር ባይገኝም የጨረታ ገምጋሚ ኮሚቴው የድምር ውጤቱን በአግባቡ ገምግሞ ለውሳኔ ማቅረብ ስለነበረበት የፋይናንሻል ግምገማውን ቀጥሏል። ይህ ማለት ግን የጨረታ ገምጋሚ ኮሚቴው በቂ የሆነ ተጫራች አግኝቷል ማለት አይደለም።

የጨረታ ገምጋሚ ኮሚቴው የጨረታ ሂደቱን በአየር መንገዱ የግዥ መመሪያ መሠረት ያካሄደ ሲሆን በመመሪያውም የፋይናንሻል ሰነድ አከፋፈት ሂደት ላይ ዋጋ ለተጫራቾች እንዳይገለጽ በግልጽ የሚያስቀምጥ በመሆኑ የጨረታ ገምጋሚ ኮሚቴው ስራውን ያከናወነው በመመሪያው መሠረት ሲሆን ተጫራቾች ያቀረቡት ዋጋም አልተነበበም።

ጨረታውን የመሠረዝ ውሳኔ ላይ የተደረሰው የተለያዩ ቦታዎች ላይ በግዥ መመሪያው መሰረት ለዋጋ ድርድር (Financial Negotation) የማያበቁ እንዲሁም በርከት ያሉ ተጫራቾች ቢቀርቡም መመዘኛውን አሟልተው የተገኙት ተጫራቾች ለአንዳንዶቹ የጨረታ መወዳደሪያ ቦታዎች (premises) ምንም ያልተገኘ ሲሆን፣ ለአንዳንዶቹ አንድ ብቻና በጣም ጥቂት ለሆኑት ደግሞ ሁለት ብቻ በመሆናቸው ምክንያት ነው።

በመመሪያው መሰረት ጨረታውን በማንኛውም ጊዜ የመሰረዝ መብት እንዳለው የተገለጸ ሲሆን ይኽውም በጨረታ ሰነዱ ተገልጾ የአየር መንገዱን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል እንዲሰረዝና በድጋሚ እንዲወጣ ተወስኗል።

በመጨረሻም አንጋፋው አየር መንገዳችን ለበርካታ ዓመታት ያካበተው ልምዱ ጨረታን እና ሌሎች ጉዳዮችን ዓለምአቀፍ ደረጃውን በጠበቀ እና ከብልሹ አሰራር በጸዳ መልኩ የሚያከናውንበት ሥርዓት እንዲኖረው ረድተውታል፤ ስለሆነም ማንም ተወዳዳሪ ህጉን እና መመሪያውን አክብሮ እስከተንቀሳቀሰ ድረስ ያለአድሎ የሚስተናገድ መሆኑን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።

ከሠላምታ ጋር

አስራት በጋሻው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ማኔጀር

አዲስ ዘመን ነሀሴ 9/2011



Report Page