#ET

#ET


ኢትዮጵያ ከጥቂት ወራት በኋላ የመሬት ምልከታ ሳተላይት ልታመጥቅ መሆኗን አስታውቃለች።

በመሬት ያሉ ነገሮችን እና ስለመሬት መረጃ የምታሰባስብ በኢትዮጵያውያን እና በውጭ ሀገራት ምሁራን የተሰራች ሳተላይት ለማምጠቅ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እንደተናገሩት የመሬት ምልከታ ሳተላይቷን ለማምጠቅ ጥሩ የሚባል ዝግጅት ተደርጓል።

ሳተላይቷን ለማምጠቅ የ‹‹ግራውንድ ስቴሽን›› ግንባታውም እንደተጠናቀቀ ዶክተር ሰሎሞን ገልፀዋል። አሁን ለማምጠቅ በዝግጅት ላይ ከምትገኘው ሳተላይት በኋላ ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች ያለማንም አጋዥ ራሳቸውን ችለው የሚሰሩበት መንገድ እንደሚፈጠርም ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። ‹‹ሳተላይቷ ወደ ሕዋ የምትመጥቀው ዘርፈ ብዙ ተልኮ ይዛ ነው›› ያሉት ዶክተር ሰለሞን በዋናነት ለእርሻ አመቺ የሆኑ አካባቢዎችን እና ሰብሎቹን ለመለየት፣ ለአካባቢ እና ለደን ጥበቃ፣ ለውሃ ልማት፣ ለማዕድን ፍለጋ ሥራ እና ለአየር ንብረት ቁጥጥር እና ትንተና የሚያገለግሉ መረጃዎችን እንደምትሰበስብ ገልጸዋል፡፡

የተገጠመላት መሳሪያ ብዙ ነገሮችን መቃኘት የሚያስችል በመሆኑ በርካታ መረጃዎችን በመሬት ምልከተዋ እንደምትሰበስብም ተገልጿል። የሳተላይቷ መቆጣጠሪያ፣ መከታተያ እና ትዕዛዝ መስጫ ጣቢያ እንጦጦ ላይ እንደሚሆንም ዶክተር ሰለሞን ተናግረዋል። ሳተላይቷ የ‹‹ፍሪክዌንሲ›› ምዝገባ ተደርጎላታል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንድትተዋወቅም ተደርጓል ነው የተባለው፡፡ የሳተላይት ሶስተኛ ወገን የኢንሹራንስ ጥያቄም ተጠይቋል። ማምጠቂያ ጣቢያውን የቻይና መንግስት እንደፈቀደ እና በኢትዮጵያ በኩልም ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

“ስፔስ ዓለምን አንድ ያደርጋል” ያሉት ዶክተር ሰለሞን ሳተላይቷ ዓለምን በማካለል የምድርን ምልከታ እንደምታደርግም ገልፀዋል። ሳተላይቷ ከባህር ጠለል በላይ 700 ኪሎ ሜትር ርቀት ትመጥቃለች። “በስፔስ ሳይንስ አንድ አድርጎ የበለፀገች ኢትዮጵያን መፍጠር ዓላማችን ነው፤ ሕዝቡም አንድ ሆኖ ጠንካራ ኢትዮጵያን መፍጠር አለበት” ብለዋል ዶክተር ሰለሞን።

ሳተላይቷ በምድር ምልከታ ላይ ኢትዮጵያ የምታወጣውን ወጪ ከማስቀረትም በላይ ገቢ ታስገኛለች ተብሎ ይጠበቃል። ሳተላይቷ በጣም ዘገየ ቢባል ታህሳስ 2012 ዓ.ም መጀመሪያ አካባቢ እንደምትመጥቅም ዶክተር ሰለሞን ለአብመድ ገልፀዋል።

Via #AMMA

@tsegabwolde @tikvahethiopia

Report Page