#E

#E


የአፍና የአፍንጫ መሸፍኛ ጭንብሎች ጥራት መረጋገጥ እንዳለበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ አሳስቧል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርዱ ይህን ያሳሰበው የኮሮና ወረርሽኝን አስመልክቶ በቅርቡ የኢትዮጵያን ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን መስሪያ ቤትን የስራ እንቅስቃሴ በአካል በተመለከተበት ወቅት ነው፡፡

በምልከታውም ወቅት ከውጭ የሚገቡና በአገር ውስጥ የሚመረቱ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎች ጥራትን፣ በአገሪቱ የመድሃኒት አቅርቦትና ስርጭት ተደራሽነትን እና የኮሮና በሽታን አስመልክቶ የሚፈጸም የኮንትሮባንድ ንግድን የተመለከቱ ጥያቄዎች በመርማሪ ቦርዱ አባላት ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሄራን ገርባ ከቦርድ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት በሆስፒታሎች የመድሃኒት አቅርቦትና ስርጭት ክፍተት እንዳይፈጠር ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን አንስተው ለሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች እና ለ9ኙ ክልሎች የመድሃኒት አቅርቦትና ስርጭት ላይም አስፈላጊው ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በህገ-ወጥ መንገድ ወደ አገር የሚገቡ የመድሃኒት ምርቶችን ለመከላከል በአገሪቱ መውጫና መግቢያ ኬላዎች ላይ ከገቢዎችና ጉምሩክ፣ ከፖሊስና ከጸጥታ አካላት ጋር ተባብረው እየሰሩ እንደሆነ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ፣ ዘርፉ ከባድ ወንጀል የሚፈጸምበት እና የወንጀል ስልቱም ከጊዜ ወደ የሚቀያየርና የረቀቀ በመሆኑ ተቋሙ የራሱ የፖሊስ ኃይል የሚያስፈልገው እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ኮሮናን ለመከላከል በአገር በቀል መድሃኒቶች ላይም ኮሚቴ ተዋቅሮ ሳይንሳዊ ምርምር እየተደረገ እንደሆነም ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን የመድሃኒት ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ገነቴ በበኩላቸው፣ የኮሮና በሽታን ከመከላከል ባለፈ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ህገ-ወጥ የመድሃኒት ዝውውርን ለመግታት ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸው፣ የኮሮና በሽታን ለማረጋገጥ የሚያስችል የላቦራቶሪ ማእከል አለመኖሩ በስራቸው ላይ ክፍተት የፈጠረባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኮሮና በሽታን ለመከላከል እንዲቻል የአፍና የፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ምርቶች ከውጭ እንዲገቡ ታስቦ ከ80 በላይ ለሚሆኑ አስመጪና ላኪዎች የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ መሰጠቱንም ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አመራሮች መረዳት ተችሏል፡፡

እንደ ሀገር የኮሮና በሽታን ለመከላከል በሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት የተቋሙ 35 በመቶ የሚሆኑ ሰራተኞች በቤታቸው ሆነው ስራቸውን እንዲያከናውኑ የተደረገ ሲሆን፣ የተቋሙን ድረ-ገጽ በማሻሻል መረጃዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተሰንደው የተያዙ እንደሆነም ባለሙያዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የመርማሪ ቦሩድ አባላት በበኩላቸው፣ ተቋሙ የኮሮና በሽታን ለመከላከል የነበረውን ቅድመ ዝግጅትና አሁን ያለውን የስራ እንቅሰቃሴ አድንቀው ህገ-ወጥ የመድሃኒት ዝውውርን በተመለከተ የበለጠ ትኩረት መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ስብሳቢው የተከበሩ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት በበኩላቸው፣ ተቋሙ በመድሃኒት አቅርቦትና ስርጭት ስራው እንዲሁም ህገ-ውጥ የመድሃኒት ዝውውርን ለመግታት እና ኮሮናን ለመከላከል በሚመረቱ የጭንብል ምርቶች ጥራት ላይ የበለጠ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የተቋሙን የላቦራቶ ማዕከል በተመለከተም በጀትን ጨምሮ ያሉት ችግሮች እንዲፈቱና አገልግሎቱን እንዲጀምር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቦርዱ የሚመክር እንደሆነም አቶ ጴጥሮስ ማስረዳታቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡

Report Page