#DW

#DW


በወልዲያ ዩኒቨርስቲ ተስተጓጉሎ የነበረው መደበኛ ትምህርት እንደገና መጀመሩን ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ። ትላንት በአንዱ ህንጻው ላይ የእሳት ቃጠሎ ደርሶበት በነበረው የጎንደር ዩኒቨርሲቲም የመማር ማስተማሩ ሂደት ያለ ችግር እየተከናወኑ መሆኑን ዩኒቨርሲቲው ገልጿል።

የወልዲያ ዩኒቨርስቲ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ተፈራ አስናቀ ለዶይቼ ቬለ (DW) በስልክ እንደተናገሩት በዩኒቨርሲቲው ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት በዩኒቨርስቲው ትምህርት ተቋርጦ መቆየቱን ገልጸዋል። ባለፉት ቀናት የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የመንግስት አካላት ባደረጉት የማረጋጋት ሥራ ተማሪዎቹ ትምህርት መጀመራቸውን አስረድተዋል። የተወሰኑ “ስጋት የነበረባቸው፣ ከግቢ ውጪ የነበሩ እና ቤተሰቦቻቸው ጋር ደርሰው ለመመለስ ወስነው የነበሩ ተማሪዎችም ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰዋል” ብለዋል።

የሁለት ተማሪዎች የተቀጠፈበት የወልዲያ ዩኒቨርስቲ ግጭት ተከትሎ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች አለመረጋጋት መከሰቱ ይታወሳል። ከወልዲያው ግጭት በኋላ በጎንደር ዩኒቨርስቲ ትምህርት የተቋረጠው ለአንድ ቀን ብቻ እንደነበር የዩኒቨርስቲው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወ/ሮ ይዳኙ ማንደፍሮ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት በሁሉም ካምፓሶች ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ያመለከቱት ዳይሬክተሯ ሆኖም የተወሰኑ ተማሪዎች “ወደ መማሪያ ክፍሎቻቸው ያለመግባት አዝማሚያ ይታይባቸዋል” ብለዋል።

በጎንደር ዩኒቨርስቲ በትላትናው ዕለት ተከስቶ ስለነበረው የእሳት ቃጠሎ የተጠየቁት ወ/ሮ ይዳኙ መንስኤው ገና እንዳልታወቀ እና በፖሊስ እየተጣራ እንደሆነ ምላሽ ሰጥተዋል። ቃጠሎው የተከሰተው ማራኪ ካምፓስ ተብሎ በሚጠራው የዩኒቨርስቲው ግቢ እንደሆነ እና የአንድ ህንጻ አራተኛ ፎቅ ጣራና ኮርኒስ ላይ ጉዳት መድረሱን አብራርተዋል። የእሳት ቃጠሎው ተጨማሪ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር መዋሉንም ገልጸዋል።

ትናንትና ምሽት በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ “ምግብ ተመርዟል ተብሎ የተነዛው ወሬ ከእውነት የራቀ” መሆኑን ደግሞ የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ አስታውቋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ባለው ባዬ የተባለው ነገር ሀሰት እንደሆነና “ተመረዝን” ያሉ ተማሪዎች በጤና ባለሙያዎች ተመርምረው ጤነኛ መሆናቸው ገልጸዋል። ጉዳዩ “ሆን ተብሎ የተሰራ ሴራ ነው” ብለዋል፡፡ ተመረዝን ብለው ችግር ለመፍጠር የሞከሩ ተማሪዎች ጉዳያቸው በፖሊስ እየተመረመረ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

(DW)

Report Page