#DW

#DW


ግብፅ በዚህ ሳምንት በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ በሚደረገው ድርድር የውጭ አሸማጋይ ጣልቃ እንዲገባ ግፊት እንደምታደርግ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናገሩ። የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታኅ አል-ሲሲ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከነገ በስቲያ ረቡዕ በሩሲያዋ ሶቺ ከተማ በሚጀመረው የሩሲያ እና አፍሪካ ጉባኤ ጎን በጉዳዩ ላይ ይነጋገራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ሬውተርስ ዘግቧል።

“በዚህ ስብሰባ በድርድሩ አራተኛ ወገን እንዲሳተፍ ከስምምነት እንደርሳለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ አንድ የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ባለሥልጣኑ “በሚቀጥሉት ሳምንታት ከአንዳች ቀመር ላይ እንስማማለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል። ግብፅ በታላቁ የህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል እና አስተዳደር ላይ ለአመታት የተደረገው ድርድር ፍሬ ባለማፍራቱ በአሸማጋይነት እንዲገባ በተደጋጋሚ ብትጠይቅም ኢትዮጵያ ግን ግብፅ ያቀረበችውን የአደራዳሪ ይግባ ጥያቄ «ተገቢ ያልሆነ» ስትል ውድቅ አድርጋለች።

የግብፅ ባለሥልጣናት በታላቁ የህዳሴ ግድብ የውሀ አሞላል እና አስተዳደር ላይ በሚደረገው ድርድር የዓለም ባንክ በአሸማጋይነት እንዲገባ ሐሳብ ማቅረባቸውን ሬውተርስ ዘግቧል። ግብፅ በውሃ መጋራት ላይ ልምድ ያላቸው አሜሪካ ወይም የአውሮፓ ኅብረት አሸማጋይ ቢሆኑ ፈቃደኛ መሆኗንም ዘገባው ጠቁሟል። በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በቅርቡ በካይሮ እና በኻርቱም የተደረጉ ድርድሮች አንዳች ውጤት ሳያፈሩ ቀርተዋል። የግብፅ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባለሥልጣን «ልዩነታችን እየሰፋ ነው» ሲሉ ተናግረዋል።

Report Page