DW

DW

ቲክቫህ ኢትዮጵያ

በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ከተሞች ወደ መዲናይቱ አዲስ አበባ የሚወስዱ አውራ ጎዳናዎች የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ከወትሮ ቀንሶ መታየቱን አሽከርካሪዎች እና ነዋሪዎች ተናገሩ።

የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ በበኩሉ ትናንት ዲለላ ከተማ አቅራቢያ ለ30 ደቂቃ ከተፈጠረ የተሽከርካሪዎች መስተጓጎል በስተቀር በክልሉ በየትኛውም አካባቢ የጸጥታ ችግር አልተከሰተም ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ለዶይቸ ቬለ የገለጹት እንዳሉት ከአዲስ አበባ ጅማ ከሻሸመኔ አዲስ አበባ እና ከሻሸመኔ ባሌ የሚወስዱ መንገዶች ከትናንት ጀምሮ ተዘግተዋል አልያም የተሽከርካሪዎች ፍሰት ከወትሮው እጅጉን አንሶ ተስተውሏል።

ከአዲስ አበባ ጂማ መስመር በተለይም  ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ በምትገኘው የዲለላ  ከተማ አካባቢ ትናንት መንገድ መዘጋቱን ተከትሎ  የመንግስት ጦር በስፍራው እስኪደርስ ድረስ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ተስተጓጉሎ እንደነበር ከአዲስ አበባ ጅማ የህዝብ ማመላለሻ ላይ የሚሰሩ እና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁን አሽከርካሪ ነግረውናል።

በተመሳሳይ ከሻሸመኔ አዲስ አበባ መስመርበ ተለይ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ መቋረጡን የነገሩን ደግሞ አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪ ናቸው ። እርሳቸው እንዳሉት መንገድ ይዘጋል በሚል ስጋት እና ሊደርስ ይችላል ካሉት ጥቃት ለመከላከል የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ተገቷል።

በዚህም ከሻሸመኔ አዲስ አበባ ባለው አውራ ጎዳና ላይ በሚገኙ ከተሞች የመንግስት የታጠቁ ሃይሎች ከወትሮው በተለየ ቁጥራቸው በርከት ብሎ መስተዋሉን መረጃ እንዳላቸው ነግረውናል።

ከሻሸመኔ ባሌ በሚወስደውአውራ ጎዳናዎች ላይ ዛሬ ጥዋት ለመንቀሳቀስ ሙከራ ያደረጉ ሶስት የሕዝብ እና የጭነት ተሽከርካሪዎች መስታወታቸው ተሰባብሮ መመለሳቸውን ማየታቸውን አስተያየታቸውን የሰጡን የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪ ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ በበኩሉ« በክልሉ ሊፈጸም ታቅዶ የነበረው የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አውታሮች እንቅስቃሴ ዕቀባ በህዝቡ እና በጸጥታ ኃይሎች ትብብር ከሽፏል »ብሏል።

በክልሉ በተለይ በምዕራብ ሸዋ በምትገኘው የዲለላ ከተማ አካባቢ ለደቂቃዎች ተፈጥሮ ከነበረው የተሽከርካሪዎችመስተጓጎል ውጭ የተፈጠረ ችግር አለመኖሩን የክልሉ አስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጅብሪል መሐመድ ተናግረዋል።

ባለፈው ሰኔ 22 ቀን የዝነኛውን የአፋን ኦሮሞ ሙዚቃ አቀንቃኝ  ሃጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ መዲናይቱ አዲስ አበባን ጨምሮ በኦሮሚያ ክልል ፣ በድሬ ዳዋ እና የሀረር ከተሞች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፉ እና ከፍተኛ የንብረት ውድመት ያስተናገዱ ነውጦችን አስተናግደው ማለፋቸው ይታወሳል።

Report Page