DW

DW



ትንሿ በአራት፣ ትልቋ በ 17 ዓመቷ ነው የተዳረችው»

ኢትዮጵያ ውስጥ 18 ዓመት ሳይሞላቸው የሚዳሩ ልጆች ቁጥር ካለፉት 15 ዓመታት ጋር ሲነፃፀር እየቀነሰ ቢመጣም አሁን ድረስ ትንሽ የማይባሉ ልጃገረዶች በግዳጅ ይዳራሉ። በዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ይህ ጎጂ ልማድ ከሚዘወተርበት ማህበረሰብ የመጡ ወጣቶች አሁን ድረስ በህፃናት እና አዳጊ ወጣቶች ላይ ስለሚፈጠረው ከፍተኛ ጫና ይገልፁልናል።

ያምሮት ተወልዳ ያደገችው ምስራቅ ጎጃም ውስጥ ነው። ዛሬ በ 20ዎቹ አጋማሽ የምትገኘው ወጣት አዲስ አበባ ውስጥ ትኖራለች። «አንድ አጎቴ ናቸው ወደ አዲስ አበባ ሲሄዱ በልጅነቴ ከገጠር ይዘውኝ የወጡት» ትላለች። ይህ ባይሆን ኖሮ እሷም እንደ ሌሎቹ የአካባቢዋ ልጆች በልጅነቷ ተድራ እንደሚሆን አትጠራጠርም። ዛሬ ተምራ የመንግሥት ሰራተኛ ሆናለች። አልፎ አልፎ ዘመዶቿን ለመጠየቅ ወደ ገጠር ስትሄድ ተበሳጭታ ነው የምትመለሰው። የቅርብ ዘመዶቿ ሳይቀሩ በዚህ ዓመት ህፃን ልጆቻቸውን ድረዋል። «የተዳሩት ትንሿ አራት ዓመቷ ነው። ትልቋ ደግሞ 17 ፤ ሌሎቹ ደግሞ 16 እና የ 15 ዓመት ልጆች ናቸው የዳሩት። ሁሉም በአንዴ ነው የተዳሩት። »

እንደ የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት UNICEF ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ እድሜ ጋብቻ ከጎርጎሮሲያኑ 2005 ዓ ም ጋር ሲነፃፀር እየቀነሰ ነው። ቢሆንም አሁን ድረስ ከአስር ልጃገረዶች አራት ያህሉ 18 ዓመት ሳይሞላቸው ይዳራሉ። ለመሆኑ ገና በህፃንነት እድሜያቸው የተዳሩት ልጆች ህይወት በምን መልኩ ይቀጥላል? ያምሮት ይህን በሚመለከት ከድሮ በመጠኑም ቢሆን የተሻሻለ ነገር አለ ብትልም ልጃገረዶቹ ምንም አይነት ዋስትና እንደሌላቸው ታስረዳለች። « በርግጥ ተድረው የግብረ ስጋ ግንኙነት እንደድሮው አይፈቀድም። ተፅዕኖው ግን አብዛኛውን ጊዜ ወንዱ ትልቅ ስለሆነ ከፈለገ ራሱ ጋር ያስቀራታል። » በዚህም ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ ልጃ ገረዶቹ ብዙም ሳይቆዩ በ10 እና በ 12 ዓመታቸው የግብረ ስጋ ግንኙነት እንዲጀምሩ ስለሚደረግ ያረግዛሉ ትላለች ያምሮት። ያምሮት ወደ ገጠር ሄዳ በልጅነታቸው ከተዳሩ የሰፈሯ ወይም የዘመዶቿ ልጆች ጋር ስትወያያይ « እንደ አንቺ ሳንማር የልጅ እናት ሆነን ቀረን እያሉ » ብዙ ብሶት ይነግሯታል።

« ስራ አጥነት የወለደው ለትምህርት ዝቅተኛ አመለካከት የመስጠት ሁኔታ አለ።»


ኤልያስ ምስራቅ ጎጃም ውስጥ የሚኖር የ 26 ዓመት ወጣት ነው። « ሴቶቹ ናቸው እንጂ ያለ እድሜው የሚዳር ወንድ ልጅ በአሁን ጊዜ ገጥሞኝ አያውቅም» ይላል። እሱ እንደሚለው ያለ እድሜ ጋብቻን በሚመለከት ያለው ችግር በመጠኑም ቢሆን እየተቀረፈ ነው። « የሴቶች ጉዳይ የሚባሉ ተቋቁመዋል። ካለፍላጎት የሚዳረው ቀንሷል። ግን አንዳንድ በጣም ገጠራማ ቦታ ለጉርብትና ፣ ዝምድናችንን እናጥብቅ እያሉ ወላጆች የሚያጋቧቸው አሉ። እድሜያቸው ሳይደርስ እና አብረው ያድጋሉ።» ይላል ኤልያስ። ያለ እድሜያቸው የሚዳሩት ልጆች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ወጣቱን ቢያስደስተውም አሁንም ድረስ ለአቅመ አዳም እና ሄዋን የደረሱት ልጆችም እንኳን የፈለጉትን ሰው መርጠው ማግባት አለመቻላቸው ያናድደዋል። እሱም ቢሆን ቤተሰብ ጣልቃ ሳይገባ የመረጣትን ልጅ ዝምብሎ ማግባት አይችልም። ኤልያስ አብዛኞቹ ያለ እድሜ የተዳሩት ልጃገረዶች ቤተሰባቸውን እና ባላቸውን ስለሚፈሩ ተገደው ስለመዳራቸው አይናገሩም ይላል። በሌላ በኩል ደግሞ ደፍረው ወላጆቻቸውን የከሰሱ እና ያሳሰሩም እንዳሉ ያውቃል። ኤልያስ «በጭፍኑ ተድረው የልጅ እናት ከሚሆኑና ብዙ ጉዳት ከሚደርስባቸው » ድፍረታቸውን ያበረታታል። 

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቀረት መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እየሰሩ ይገኛሉ። ሆኖም የሴቶች ህፃናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር በግንቦት ወር ይፋ እንዳደረገው በአማራ ክልል በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የትምህርት ቤቶች መዘጋትን ወላጆች እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅመው 585 ልጆችን ያለዕድሜያቸው ድረዋል። እንዲሁ በዚሁ ዓመት ደግሞ ከወላጆች ጋር በመነጋገር 1070 የልጅነት ጋብቻዎች እንዲቋረጡ ተደርጓል። ያለዕድሜ ጋብቻው በስፋት የተስተዋለባቸው አካባቢዎች ምሥራቅ ጎጃም፣ ደቡብ ጎንደር፣ ሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞኖች መሆናቸውም ተዘግቧል። አቶ መንግሥቴ ተገኔ አዲስ አበባ ውስጥ ቢሮ ያለው የኖርዌይ ቤተ ክርስትያን ርዳታ ድርጅት የፆታዊ ጥቃት እና የስነ ተዋልዶ ጤና ፕሮግራም አማካሪ ናቸው። በዚህ በኮሮና ወቅት ያለ እድሜ ጋብቻ የጨመረበትን ምክንያት ሲገልፁ « በዚህ ሰዓት ሪፖርት የሚደረግበት መንገድ ጠፍቷል። ትምህርት ቤቶች ዝግ ናቸው። ቁጥሩም ከዚህ በላይ ሊሆን ይችላል» ይላሉ። አክለውም « በዋንኛነት የህብረተሰቡ አመለካከት አለመለወጡ እና ስራ አጥነት የችግሩ መንስኤ እንደሆኑ ይናገራሉ። « ስራ አጥነት የወለደው ለትምህርት ዝቅተኛ አመለካከት የመስጠት፣ ተምረሽ የት ትደርሻለሽ የማለት አመለካከት አለ።» ለዚህ መፍትሄው ደግሞ በዚህ በኮሮና ወቅት ከኮሮና ግብረኃይል ጋር ተባብሮ መስራት እንደሆነ ለ ዶይቸ ቬለ DW ገልፀዋል።



የኢትዮጵያ መንግሥት እጎአ እስከ 2025 ድረስ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ሙሉ በሙሉ ለማስቆም ቃል በመግባት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቷል። ለዚህም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር እየሰራ ይገኛል። የኖርዌይ ቤተ ክርስትያን ርዳታ ድርጅት ከነዚህ ተካፋይ አካላት አንዱ ነው። « የኖርዌይ ቤተ ክርስትያን ርዳታ ድርጅት እና አጋር ድርጅቶች በዚህ ፍኖተ ካርታ እንዲካተት ያደረግነው የቤተ እምነቶችን ሚና ነው።» ይላሉ አቶ መንግሥቴ። 

 አቶ ሳሙኤል ህሩይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የልማት እና ክርስትያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት የማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት የማህበረሰብ አሰባሳቢ ወይም ሶሻል ሞቢላይዘር ናቸው። ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቆም ለካህናት፤ ለፅዋ ማህበራት ፣ ለማህበረሰብ አወያዮች እና ሌሎችም አካላት ስልጠና ይሰጣሉ። በተለይ ከካህናት ስልጠና ከመስጠት ያለፈ ከፍተኛ ትብብርም እንደሚጠበቅ አቶ ሳሙኤል ገልፀውልናል። « አንኮበር ወረዳ ላይ ከአራት አመት በፊት ስንመጣ እና ለካህናት ስልጠና ስንሰጥ በስልጠናው መጨረሻ ላይ የተግባቡት ቃል ነበራቸው። ይህ ደግሞ ማንኛውም ካህን ወይም ቄስ የሴትልጅ አስገርዞ ቢገኝ ወይም ከንሰሀ ልጆቹ ያስገረዙ ቢገኙ ሲቀጥል አንድ ሰው ጾታዊ ጥቃት አድርሶ በወንጀል ቢከሰስ ለዚህ ሰው ሽምግልና እንደማይቆሙ ተፈራርመዋል» ካህኑም ይህንን ህግ ተላልፎ ቢገኝ ከክህነቱ እንዲሰረዝ ይደረጋል። ይላሉ። አቶ ሳሙኤል በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን በየጊዜው ለማህበረሰቡ ከሚደረጉ መጠይቆች መረዳት መቻላቸውንም ገልፀውልናል። ይህ ብቻ አይደለም። ስልጥና ያገኙ የማህበረሰቡ አካላትም ያለ እድሜ ጋብቻን በማጋለጥ ጉዳዮን ወደ ህግ አካል የወሰዱበት አጋጣሚዎችም አሉ።  


Report Page