DW

DW

ቲክቫህ ኢትዮጵያ

የሱዳን ኃይሎች ትንኮሳና የግብርና ልማት ባለሀብቶች ቅሬታ በምዕራብ ጎንደር ወረዳዎች

በምዕራብ አርማጭሆና ቋራ ወረዳዎች በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች «በአካባቢው የሰፈረው የሱዳን ጦር የግብርና ሥራችንን እንዳናከናውን አድርጎናል» ሲሉ ከሰሱ፣ በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ የሱዳን ታጣቂዎች ሰሞኑን በአካባቢው አርሶ አደሮች ላይ ትንኮሳ ማድረጋቸውን ደግሞ የወረዳው አስተዳደር አስታውቋል፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የቋራ ወረዳ ነዋሪ ለዶይቸ ቬለ እንደተናገሩት ወቅቱ የዘር ወቅት ቢሆንም የሱዳን ታጣቂዎች በግብርና የተሰማሩ ባለሀብቶችን ከቦታቸው በማባረር የግብርና ሥራ እንዳይካሄድ አድርገዋል ብለዋል፡፡ የሱዳን ታጣቂዎች በየቀኑ አዳዲስ ታጣቂዎችን «እንዲብሎ» በተባለ አካባቢ ኃይላቸውን በመጨመርና ምሽግ በመቆፈር ለአካባቢው ስጋት መሆናቸውን እኚሁ አሰተያየታቸውን የሰጡን የአካባቢው ነዋሪ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይል ቱመትና መንዶክ በተባሉ አካባቢዎች ቢኖርም የወሰደው እርምጃ እንደሌለ ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የሚናገሩት፡፡ የቋራ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት ኃላፊ ኢንስፔክተር ዳምጠው ሞላ ተጠይቀው የሱዳን ጦር ቀደም ሲል ከ2 እና 3 ዓመት በፊት ከነበረበት ቦታ ላይ እንደቆዬ አመልክተው በየጊዜው ኃይል እየጨመረ አንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮችና በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች የእርሻ ሥራቸውን እንዲሠሩ፣ ጫና እንዳያሳድሩባቸው ስምምነት አድርገናል ያሉት ኃላፊው፤ ያሉ የድንበር ጥያቄዎች የሚመለሱት በፌደራሉ መንግሥት በመሆኑ ሱዳኖች የሰፈሩበት ቦታን የዚህ ነው ወይም የዛ ነው ማለት እንደማይችሉም ገልፀዋል፡፡

የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ግዛቸው ደረጄ በበኩላቸው ሰሞኑን በአካባቢው ያለው የሱዳን ታጣቂ ኃይል የእርሻ ቦታ ሲያፀዱ በነበሩ ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ላይ ትንኮሳ ማድረጉንና የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት አፀፋ ጉዳት ሳይደርስ ችግሩ በቁጥጥር ሰር መዋሉን ተናግረዋል፡፡ 

ከ2010 ዓ ም ጀምሮ የጓንግ ወንዝን ተሻግረው አሁን ኢትዮጵያ በምታስዳድረው አፍዴራ በተባለ አካባቢ ካምፕ ሠርተው እየኖሩ መሆኑንም አብራርተዋል። ባለፈው ረቡዕ የተፈጠረውን ግጭት የሚያጣራ ቡድን ወደ ቦታው መሄዱንና ከተጣራ በኋላ የችግሩ መንስኤ ምን እንደሆነ የሚታወቅ እንደሚሆንም ከባሕር ዳር ዓለምነው  መኮንን በላከልን ዜና ጠቅሷል።

Report Page