DW

DW

ቲክቫህ ኢትዮጵያ

በኮሌራ ምክንያት አስራ አንድ(11) ሰዎች ሞተዋል ከ700 በላይ ተጠቅተዋል

በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ 11 ሰዎች በኮሌራ መሞታቸውንና ከ700 ባላይ ደግሞ በኮሌራ መያዛቸውን የዳሰነች ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት አስታውቋል። የወረዳው ጤና ሃላፊዎች እንዳሉት ኮሌራ የተከሰተውም ካለፈውሳምንት መጀመሪያ አንስቶ ኢትዮጵያን ከኬንያ በሚያዋስነው የቱርካና ሐይቅ ዙሪያ በሚገኙት ቡቡዋ አቹጋ እና ሎዬሬ በተባሉት ቀበሌዎች ነው።

ዶቼቬለ ያነጋገራቸው የደቡብ ኦሞ ዞን ጤና መምሪያ የበሽታ መከላከልና ጤና ማጎልበት የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ታምራት አሰፋ በወረዳው ኮሌራ መከሰቱን አረጋግጠው ሆኖም የወረዳው ጽህፈት ቤት ሞተዋል ያላቸው ሰዎች በኮሌራ ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት መሞታቸው እየተጣራ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ከዳሰነች ወረዳ በተጨማሪ በሰሜን አሪ ወረዳም ኮሌራ መከሰቱን የተናገሩት አቶ ታምራት የጤና ባለሞያዎችን ከሌሎች አካባቢዎች ወደ ወረዳዎቹ በማዛወር ታማሚዎችን እያከሙና በሽታውንም የመከላከል ሥራ እያካሄዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በሽታው የተከሰተባቸው አካባቢዎች በቱርካና ሐይቅ ዳርቻ የሚገኑት እና የአሳ ምርትን ጨምሮ የተለያዩ የንግድ ልውውጦች የሚካሄዱባቸው በመሆናቸው የበሽታው ሥርጭት ሊሰፋ ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል። በደቡብ ክልል ባለፈው ታህሳስ በጎፋና በደቡብ ኦሞ ዞኖች ተከስቶ በነበረው የኮሌራ በሽታ አስራ ስምንት ሰዎች ሲሞቱ አንድ ሺህ የሚጠጉ ደግሞ በበሽታው ተይዘው እንደነበር ይታወሳል።

Report Page