"የወርቅ ሜዳልያው ለጀግናዋ እናቴ ይሁንልኝ "-አትሌት ጉዳፍ ፀጋዬ

"የወርቅ ሜዳልያው ለጀግናዋ እናቴ ይሁንልኝ "-አትሌት ጉዳፍ ፀጋዬ

በአብዩ ታይበሌ ከኦሪገን፣አሜሪካ


በኦሪገኑ የዓለም ሻምፒዮና ዘጠነኛው እለት በ5,000 ሜትር ርቀት ኢትዮጵያ ተጨማሪ ሜዳልያን ዛሬ አግኝታለች።በርቀቱ ፈጣን ሰዓት የነበራትን እጅጋዬሁ ታዬን በመተካት በዓለም ሻምፒዮናው በድጋሚ እንዲወዳደሩ እድልን ያገኙት ፤የ10,000 ሜትር ዓለም ሻምፒዮኗ ለተሰንበት ጊደይ እና የ1500 ሜትር የብር ሜዳልያ ባለቤቷ ጉዳፍ ፀጋዬ ውድድሩን በቡድን በመምራት ከድሉ ባሻገር ኢትዮጵያዊያን የሚታወቁበትን የቡድን ስራ በተግባር መልሰውት ታይተዋል።

በውድድሩም ጉዳፍ ፀጋዬ 14:46.29 በሆነ ሰዓት ቀዳሚ ሆና በማጠናቀቅ ኢትዮጵያ በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያገኘችውን የወርቅ ሜዳልያ መጠን ወደ አራት ከፍ ማድረግ ችላለች።


አትሌት ዳዊት ስዩም 14:47.36 በሆነ ሰዓት ለኢትዮጵያ የነሃስ ሜዳልያን አስገኝታለች።

በዚህ ውድድር የቡድን ስራውን በማቀጣጠል ለወርቁ መገኘት የአንበሳውን ድርሻ የተወጣችው ለተሰንበት ጊደይ 14:47.98 በሆነ ሰዓት 5ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።


የርቀቱን የብር ሜዳልያ ደግም 14:46.75 በሆነ ሰዓት ኬንያዊቷ ቢያትሪስ ቼቤት ወስዳለች።


ከውድድሩ በኋላ ለጋዜጠኞች አስተያየቷን የሰጠችው ሻምፒዮኗ አትሌት ጉዳፍ ፀጋዬ የወርቅ ሜዳልያውን ክብር መታሰቢያነቱ ለጀግናዋ እናቴ እና አሰልጣኜ (ባለቤቴ) ይሁንልኝ ብላለች።ውድድሩን በተመለከተ ከ6ኛው ዙር በኋላ በማክረር ወርቁን ለአገራችን የማምጣት እቅድን ይዘን በመግባት አሳክተናል ስትል አብራርታለች።

አትሌት ለተሰንበት በበኩሏ በ10,000 ሜትር አስቀድሜ ወርቅ በማግኘቴ በድጋሜ ወርቁን ከእኔ ይልቅ ለአገሬ እንዲመጣ አቅጄ ለቡድን ስራ ነው የገባሁት እሱም ተሳክቷል ብላለች።


የርቀቱ የነሃስ ሜዳልያ ባለቤቷ ዳዊት ስዩም ስለውጤቱ ተጠይቃ ስትመልስ ይህ ድል ከእኛ አትሌቶቹ ይልቅ ለኢትዮጵያ ህዝብ አስፈላጊ ነበር በማለት፤በዚህ የአሸናፊነት ጉዞ ኢትዮጵያዊያን በአሰቸጋሪ ጊዜያትን ተቋቁመን ድል ማድረግ እንደምንችል ማሳያ ነው ብላለች።

ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የምንጊዜም ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበች ሲሆን ነገ በሚደረገው የወንዶች 5,000 ሜትር ርቀት የሚጠበቀው ሜዳልያ እንደተጠበቀ ሆኖ፤እስካሁን በ4 የወርቅ፤በ4 የብር እና በ2 የነሃስ በድምሩ 10 ሜዳልያዎችን ሰብስባ አሁንም ከአሜሪካ ቀጥላ በዓለም የደረጃ ሰንጠረዥ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ኢትዮጵያ በ17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 2የወርቅ፤5የብር እና 1የነሃስ በድምሩ 8 ረዳልያን ይዛ መመለሷ ይታወሳል።


Report Page