#DA

#DA


የገዛ ባለቤቱ ላይ አሲድ እንዲደፋባት ያደረገዉ ግለሰብ በጽኑ እስራት ተቀጣ

________________________________________

ተከሳሽ ያሲን ዳውድ አሊ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ/ና/ለ/ እንዲሁም በአንቀጽ 539/1/ሀ/ ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ሰው ለመግደል በማሰብ ተዘጋጅቶ በገዛ በባለቤቱ ላይ አሲድ እንዲደፋባት በማድረጉ ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶበታል፡፡

ተከሳሽ ሰው ለመግደል በማሰብ ሚያዚያ 13 ቀን 2010 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 4፡10 ስዓት አካባቢ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ልዩ ቦታው ሳሬም ኢንተርናሽናል ሆቴል አካባቢ ባለቤቱ በሆነችው የግል ተበዳይ ወ/ሮ ሜላት ተሰማ ላይ በነበረበት የቅናት መንፈስ ተነሳስቶ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ ሃይድሮክሎሪክ አሲዲ በስልሳ ብር በመግዛት ቶፊቅ ረሻድ የተባለው ያልተያዘው የወንጀሉ ግብረ አበር አሲዱን እንዲደፋባት አድርጓል፡፡

ተከሳሹ ወንጀሉን ለመፈፀም በማሰቡ የግል ተበዳይና የህግ ባለቤቱ በሆነችው ወ/ሮ ሜላት ተሰማ ላይ ጉዳት ለማድረስ ወዳቀደበት ስፍራ ወስዶ ለጊዜው በቁጥጥር ሥር የላዋለው የወንጀሉ ተካፋይ እስኪመጣ ድረስ ወንጀል በተፈፀመበት ስፍራ የግል ተበዳይን እያዋራ በማቆየት የወንጀል ተካፋዩ መጥቶ ፊቷና ሰውነቷ ላይ አሲድ የደፋባት ሲሆን በዚህም 33% የሚሆነው የአካል ክፍሏ ቃጠሎ እንዲደርስበት፣ የቀኝ ጆሮዋ የመስማት ሀይሉ እንዲቀንስና የቀኝ አይኗ ሙሉ በሙሉ እንዲጠፋ በማድረግ ጨካኝነቱንና አደገኝነቱን በሚያሳይ ሁኔታ ከባድ ጉዳት በማድረስ ለመግደል በመሞከሩ በፈፀመው የግድያ ሙከራ ወንጀል ተከሶ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ 20ኛ የወንጀል ችሎት ቀርቧል፡፡

ፍ/ቤቱም ዐቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ካዳመጠና ከመረመረ በኋላ ተከሳሽ ያሲን ዳውድ ጥፋተኛ ነው ሲል የቅጣት ዉሳኔዉን አስተላልፏል፡፡ በመሆኑም ተከሳሽ ከዚህ በፊት መልካም ጸባይ ያለዉ መሆኑ፣የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑና፣ ተበዳይን ያስታመመ መሆኑ እንዲሁም ወንጀሉ በሙከራ የቀረበ መሆኑን በቅጣት ማቅለያነት ይዞለት ተከሳሹ በአስራ ስድስት አመት ከስድስት ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗበታል፡፡

ምንጭ፦ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ

@tsegabwolde @tikvahethiopia

Report Page