#D

#D


የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ቀዳሚ ጉዳይ ነው - የኢትዮጵያ እርቀ ሰላም ኮሚሽን

.

.

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የዜጎችን ደህንነት እና ሰላም ለማስጠበቅ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ቀዳሚው ጉዳይ በመሆኑ ለዚሁ ተፈፃሚነት መንግስት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራት እና መላው ህዝብ በጋራ እንዲቆሙ የኢትዮጵያ እርቀ ሰላም ኮሚሽን አሳሰበ።

ኮሚሽኑ በጋዜጣዊ መግለጫው እንዳስታወቀው፤ ዛሬ ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ችግሮችና በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ አሳሳቢ ውጥረት ውስጥ ገብታለች።

እነዚህን ችግሮችና ግጭቶች በአፋጣኝ ለማስወገድ፣ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባር ነው፤ ለዚህም መንግስት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራትና መላው ህዝብ በጋራ ሊቆሙ ይገባል።

በአሁኑ ወቅት ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ የመጣውን የሰላም እጦት ለማርገብና ለህዘቦች የአርምሞ ፋታ ለመስጠትእንዲቻል መላው ህዝብ ለእርቅና ሰላም እንዲቆም ጥሪ ያቀረበው ኮሚሽኑ፤ ችግሮቹ በዘላቂነት እንዲፈቱ የእርቅና ሰላም መንፈስ በኢትዮጵያ መስፈን አለበት ብሏል፡፡

ህዝቡ "በአገሪቷ ዘላቂ ሰላምን ያሰፍናል" በማለት ላመነበት ወቅታዊ የለውጥ ሂደት ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ በነቂስ ወጥቶ የተሰማውን ደስታና ድጋፍ የገለጸባቸው በርካታ አጋጣሚዎች እንደነበሩ አስታውሶ፤ በአንድ ዓመት ውስጥ ተስፋ ሰጪ የሆኑ ሁለንተናዊ ለውጦችን ለማየት እድል ማግኘቱንም ገልጿል።

በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ የታየውን የተስፋ ወጋገን የሚያጨልሙ ተግባራት መስተዋላቸውን የጠቆመው መግለጫው፤ በተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው ለሰላም እጦት መንስኤ የሆኑ ግጭቶችን በአብነት ጠቅሷል።

ዛሬ የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ ተከትሎ የታየው አሳዛኝ ክስተትም ሆነ በተለያዩ ጊዜያትና አካባቢዎች እየተስተዋለ ያለው የዜጎች የእርስ በእርስ ግጭትና መፈናቀል በአስቸኳይ እንዲቆም ኮኒሽኑ አሳስቧል።

የሃይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌ የሆኑ ጭሜሳዎች እና አባገዳዎች በየአካባቢያቸው ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ በመረዳት ህዝቡን በተለይም ወጣቱን ከማረጋጋት አኳያ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ ያቀረበው ኮሚሽኑ፤ የፍቼ ጨንበላላ ታላቅ የመቻቻል ባህል በሰረፀባት ምድር እንደዚህ ዓይነት ግጭቶችና መፈናቀሎች መከሰታቸው አሳዛኝ መሆኑንም ገልጿል።

በሌሎች የክልልነት ጥያቄ እየተነሳ ባለባቸውና መሰል ችግሮች በሚስተዋሉባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎችም ህዝቡንም ሆነ ወጣቱን በማረጋጋት የበኩላቸውን እንዲወጡም አሳስቧል።

መንግስት የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ ሆነ ሌሎች ህዝቦች የሚያነሷቸውን መሰል ጉዳዮች በህጋዊ መንገድ በወቅቱ ለመመለስ እንዲችል የእያንዳንዱን አካባቢ ህዝብ በማሳተፍ በከፍተኛ አቅም እንዲረባረብም ኮሚሽኑ ጠይቋል።

ኮሚሽኑ በመግለጫው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ደጋፊዎቻቸው የሆኑ ወጣቶች አሁን የሚስተዋለውን የግጭት አዙሪት በአግባቡ በመረዳት ከጸብ አጫሪነት መታቀብ እንዳለባቸው አሳስቧል። በተለይም ከወንጀል እና ከመጠላለፍ አካሄድ በመራቅ ኢትዮጵያን ሆነ ህዝቦቿን የመታደግ ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁሟል።

የመገናኛ ብዙሀን ድርጅቶች እና ማህበራዊ ድረ-ገፆች በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የግጭት አዙሪት በመረዳት ልዩነትን እና አለመግባባትን ከሚያቀነቅኑ ድርጊቶች እንዲታቀቡ የጠየቀው ኮሚሽኑ፤ "የሀሰት መረጃዎችን ከማሰራጨት ተቆጥበው በሚያስተሳስሩ እና በሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ ጠንክረው ይሰሩ ዘንድ አደራ እንላለን" ብሏል።

ችግሩን “መላው የሀገራችን ህዝቦች በሚገባና በአጭር ጊዜ ውስጥ ይወጡታል” ያለው ኮሚሽኑ፤ ኢትዮጵያውያን በመካከላቸው ያለውን ልዩነት በውይይት እና በንግግር ብቻ እንዲፈቱ፣ ፍትህ እንዲያገኙም ሆነ እርቅና ሰላም በመሀላቸው እንዲወርድ የሚያደርግ አጋዥ እንቅስቃሴ በቅርቡ እንደሚጀምር ይፋ አድርጓል።

ምንጭ፡- ኢዜአ

Report Page