#D

#D


አዲስ አበባ ላይ ናሙና ሰጥቶ የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘበት ተነግሮት አምልጦና ደብረብርሃን መጥቶ ስልኩን አጥፍቶ ለመሰወር የሞከረው ግለሰብ በጸጥታ አካላትና የጤና ባለሞያዎች የተቀናጀ ክትትል ተይዞ ከእርሱ ጋር ንክኪ ካላቸው 13 ግለሰቦች ጋር ማቆያ መግባቱ ተገለጸ፡፡

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳዳር ጤና ጥበቃ ጽህፈት ኃላፊ አቶ ጌታሁን ማሞ ባደረሱን መረጃ መሰረት የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነው አንድ ግለሰብ አዲስ አበባ ላይ ለሌላ ህመም ጤና ተቋም ሄዶ ናሙና ሰጥቶ የ(covid-19) ቫይረስ እንዳለበት የተነገረው አንድ ግለሰብ በትላንትናው እለት ወደ ደብረብርሃን እየመጣ እንደሆነ መረጀ ለደብረብርሃን ከተማ ጤና ጽ/ቤት ሪፖርት በመደረጉ በየደረጃው ከሚመለከታቸው የዞንና የከተማው የጸጥታ አካላት እንዲሁም ለጤና ባለሙያዎች የስራ ድርሻ በመስጠት ግለሰቡን በቁጥጥር ስር ለማዋል ኦፕሬሽኑ ማታ ተጀምሮ ፍለጋው በየአቅጣጫው ተጠናክሮ ቀጥሎ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ግለሰቡ እየተፈለገ እንደሆነ ሲያውቅ ደብረብርሃን ከተማ ገብቶ አልጋ ይዞ ካደረ በኃላ የኦፕሬሽኑን ክትትል ማምለጥ እንደማይችል ሲረዳ ተመልሶ ወደ አዲስ አበባ ሌሄድ በቅጥቅጥ የህዝብ አይሱዙ መኪና ይሳፈራል፡፡ እየተደረገ ያለው ክትትል አልመች ሲለው መጀመሪያ ከተሳፈረበት መኪና ይወርድና ሌላ ተመሳሳይ የህዝብ ትራንስፖርት ውስጥ ገብቶ ጉዞውን ወደ አዲስ አበባ ይጀምራል፡፡ በተደረገው ጥብቅ ክትትል ጫጫ ከተማ ላይ ሲደርስ ከነባለቤቱ በቁጥጥር ስር ውሎ ከእርሱ ጋር መኪናው ውስጥ የነበሩ 13 ግለሰቦች ጭምር ወደ ደብረ ብርሃን እንዲመለሱ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ግለሰቡ ጠባሴ ጤና በተዘጋጀው ህክምና መስጫ መዕከል ሲገባ ሌሎቹ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ በሌላ በኩል ባረፈበት ሆቴል ከግለሰቡ ጋር ንክኪ አላቸው የተባሉ 6 የሆቴሉ ሰራተኞችም ለይቶ ማቆያ መግባታቸውን አቶ ጌታሁን አስረድተዋል፡፡

 ኃላፊው አክለውም በየትኛውም ማዕከል ናሙና የሰጡ ግለሰቦች ውጤታቸውን እስኪያውቁ ድረስ በዚያው አካባቢ መጠበቅና ለህሊናቸው ተገዢ መሆን እንዳለባቸው በጥብቅ አሳስበው ቫይረሱ የተገኘባቸው ግለሰቦችም ራሳቸውን አሳምነው ወደ ህክምና ማዕከል ገብተው ክትትል በማድረግ ራሳቸውን ቤተሰባቸውንና ማህበረሰቡን መታደግ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎት ጉዳይም በተለይ ከአዲስ አበባ የሚደረግ ጉዞ ከፍተኛ ስጋት በመሆኑ በየደረጃው ያለ አካል መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል ያሉት ኃላፊው ህብረተሰቡም ጀመረውን የመከላከል ተግባር አጠናክሮ ሊያስቀጥል ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ምንጭ፦ የደብረ ብርሃን ኮሚኒኬሽን

Report Page