#CP

#CP


ከቤኔሻንጉል ጉሙዝ እና ከአማራ ክልል መንግሥታት የጋራ ኮማንድ ፖስት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ፡፦

የአማራ እና የቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕዝቦች ለረጅም ዘመናት በፍቅር፣ በሠላም እና በአንድነት ሲኖሩ የነበሩ እና እየኖሩ ያሉ ሕዝቦች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ ሕዝቦች ለዘመናት የአብሮነት ቆይታቸው ለሌሎች ሁሉ በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል እና ከማኅበራዊ፣ ከኢኮኖሚያዊ እና ከፖለቲካዊ ቁርኝት ባለፈ ቤተሰባዊ ትስስር እና አኩሪ ታሪክ ያላቸው ናቸው፡፡

በሌላ በኩል ከአመራር ብልሽት፣ ከድህነትና ከኋላ ቀርነት፣ ከልማት፣ ከመልካም አስተዳደር እጦት፣ ከኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት እና ተግባር ጋር ተያይዞ በሚነሱ አለመግባባቶች በተወሰኑ አጎራባች ቀበሌዎች በሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል አልፎ አልፎ ግጭት እና ሁከት ሲያስከትሉ ቆይተዋል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይም ባለፉት ጥቂት ጊዜያት በግለሰቦች መካከል በተፈጠረው ያለ መግባባት የፀጥታ ኃይሉ በተወሰደው እርምጃ የአንድ ሰው ሕይወት በማለፉ ምክንያት ችግሩ የብሔር መልክ ይዞ እስከ አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ተስፋፍቶ ለሌሎች ግለሰቦች ሕይወት ማለፍ፣ አካል መጉደል፣ ንብረት መጥፋት እና መፈናቀል ምክንያት ከመሆኑም ባሻገር ለሁለት ክልሎች ወሳኝ እና ቁልፍ ከሆነው የልማት አጀንዳ እየነጠለን ይገኛል፡፡

ይህንንም ችግር ለመቅረፍ የሁለቱ ክልሎች መንግሥታት ከኢፌድሪ የሠላም ሚኒስቴር፣ ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከፌድራል ፖሊስ እና ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ግጭቶችን ለማስቆም፣ ግጭት የተከሰተባቸውን አካባቢዎች ለማረጋጋት፣ የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀድሞ ቀያቸው ለመመለስ እና በግጭቱ የተሳተፉ አካላትን ለሕግ በማቅረብ የሕግ የበላይትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት በመደረግ ላይ ቢሆን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትና የቀጠናውን ፀጋና አቅም ከማልማትና የሕዝቦችን አንድነትና ትስስር ከማጠናከር አኳያ የሁለቱ ክልሎች ማለትም የቤኔሻንጉል ጉሙዝ የመተከል ዞንና በአማራ ክልል የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር አዋሳኝ ወረዳዎችና ቀበሌዎች የጋራ ኮማድ ፖስት ዛሬ ሐምሌ 5 ቀን 2011ዓ.ም ያለውን የፀጥታ ሁኔታ በጥልቀት በመገምገም ወቅትና ጊዜ እየጠበቁ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማስቆምና አካባቢውን ቀድሞ ወደነበረበት ለመመለስ በሚያስችሉ አቅጣጫዎች ላይ በጥልቀት ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ በአሁኑ ሰዓት በመተከል ዞንና በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር አዋሳኝ ወረዳዎች ምንም እንኳ አመራሩና የፀጥታ ኃይሉ ተቀናጅቶ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ቢሆንም በአካባቢው የሕግ የበላይነት ያልሰፈነበት፣ ግድያና ዘረፋ ያልቆመበት፣ ሕገ-ወጥ መሣሪያ ዝውውርና የመሣሪያ ተኩስ ያልቆመበት፣ ዜጎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ያልቻሉበት፣ ይልቁንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጉዳዩ የብሔር ግጭት መልክ እየያዘ በንጹሐን ዜጎች ጭፍጨፋና ግድያ እየተበራከተ በመምጣቱ ይህ ሁኔታ በአስቸኳይ ካልተስተካከለ በስቀር ወደ ከፋ ግጭት የማያመራበት ምክንያት እንደማይኖር በጥልቀት ገምግሟል፤ የጋራ ኮማድ ፖስቱ፡፡

በግምገማው ማጠቃለያ በመተከል ዞንና አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር በማሻሻል ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ በማቋቋም፣ የተዘረፉ እንስሳትና ንብረቶችን በማስመለስ የሕግ የበላይነት ለማስፈን እንዲቻል እስከ ጎጥ ድረስ የሠላም ኮንፈረንሶችን በማካሄድ በሕዝቦች መካከል ቀደም ሲል የነበረውን ወንድማማችነትና አብሮ የመኖር እሴት ጎልብቶ የሕዝቦችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ፣ ዘላቂነት ያለው ሠላም ልማትና ዴሞክረሲ የቀጣይ ተግባር ማጠንጠኛ ማዕከል ማድረግ እንደሚገባው የጋራ ድምዳሜ ላይ ተደርሷል፡፡ በዚህም ችግሮችን ለመፍታት አመራሩ ቁልፍ ሚና ያለውና የሕዝቡም ተሳትፎ ወሳኝ (ጉልህ) መሆኑን በጥልቀት በመገምገም መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

ከዚህ በመነሳት ኮማንድ ፖስቱ የሚከተሉትን የአፈጻጸም አቅጣጫዎችና ክልከላዎች አስቀምጧል፡፡

1. የአፈጻጸም አቅጣጫዎች

1.1. የሕዝቦችን አብሮነትና ወንድማማችነት ለማጎልበት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች ይበልጥ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

1.2. የአካባቢውን ሠላምና ፀጥታ በማሻሻል የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የጋራ ጥረትና ርብርብ ይደረጋል፡፡

1.3. በተፈጠረው ችግር ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን በፍጥነት መልሶ ማቋቋምና ተጨማሪ መፈናቀሎች እንዳይከሰቱ በቅንጅት የሚሠራ ይሆናል፡፡

1.4. በአዋሳኝ አካባቢ ያሉ የፀጥታ ጥምር ኮሚቴዎችና አደረጃጀቶችን አጠናክሮ ግጭቶችን ቀድሞ የመከላከል ሥራ በልዩ ትኩረትና በከፍተኛ ትጋት የሚፈፀም ይሆናል፡፡

1.5. የአመራሩ ሚና ቁልፍ በመሆኑ አመራሩ ከምንጊዜውም በላይ ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል፡፡

2. የፀጥታ ችግሮች በተከሰቱባቸው አካባቢዎች በኮማንድ ፖስቱ የተደነገጉ ክልከላዎች:-

 ነፃ ቀጠና (በፈር ዞን) ተብለው በተከለከሉ ቦታዎች የጦር መሣሪያ ይዞ መገኘት በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

 በግለሰብ ቤቶችና በተለያዩ መካዝኖች የመሣሪያ ማከማቸት የተከለከለ ነው፡፡

 በየትኛውም አካባቢ ቀስትና ሌሎች በሰዎች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ስለታማ ባሕላዊ መሣሪያዎች ገጀራ፣ ጩቤ፣ ቀስት ወ.ዘ.ተ ይዞ መንቀሳቀስ በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

 በቡድንም ይሁን በግል የመሬት ወረራ ማካሄድ በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

 ከኮማንድ ፖስቱ ዕውቅና ውጭ የሚደረጉ ለከብትና ንብረት ፍለጋ ሰበብ ከፀጥታ ኃይሉ ውጭ መንቀሳቀስ ፈፅሞ የተከለከለ ነው፡፡

 በቡድንም ይሁን በግል የሕዝብ ትራንስፖርትና ሌሎች ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ማስቆም ወይም ማስተጓጎል የተከለከለ ነው፡፡

 ወንጀሎኞችን በሕግ ቁጥጥር ስር ለማዋል በሚደረግ እንቅስቃሴ ውስጥ አለመተባበር እንዲሁም ለማደናቀፍ መሞከር በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

 ያልተጨበጡ በሕዝብና በሀገር ኅልውና ላይ ወሬና አሉቧልታዎች በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያ ማናፈስ በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

 በሕገ ወጥ በሆነ መንገድ መሣሪያ ታጥቆና ተደራጅቶ ጥፋት ለመፈፀም መንቀሳቀስና የፀጥታ ኃይሉን መተንኮስ ፈፅሞ የተከለከለ ነው፡፡

 ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያና የገንዘብ ዝውውር በቀጠናው ውስጥ ማዘዋወር የተከለከለ ነው፡፡

ይህ ክልከላ ፀንቶ የሚቆየው በአካባቢው የተፈጠረው ችግር ተፈትቶ ሠላማዊ ሁኔታ ሲረጋገጥና ኮማንድ ፖስቱ ሥራውን ሲያቆምና፣ የትግበራው ጊዜ ሲጠናቀቅና፣ በመካከለኛና በረጂም ጊዜ ሥራዎች የተረጋጋና ምቹ ሁኔታ መፈጠር ሲችል ነው፡፡ በመሆኑም በቀደምትነት የሁለቱ ክልል ሕዝቦች በዋናነት ደግሞ በሁለቱ ክልል አጎራባች ወረዳዎች የሚኖሩ ሕዝቦች የጋራ ኮማንድ ፖስቱ ካስቀመጣቸው የአፈፃፀም አቅጣጫዎችና ባስተላለፋቸው ክልከላዎች ተፈጻሚነት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

የቤኔሻንጉል ጉሙዝ እና የአማራ ክልል መንግሥታት የጋራ ኮማንድ ፖስት

ሐምሌ 05 ቀን 2011ዓ.ም

ቻግኒ

Report Page