#CP

#CP


በአማራና ቤኔሻንጉል ጉምዝ ክልሎች በተወሰኑ ወረዳዎች ላይ ከሐምሌ 5 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2011 ዓ.ም የሚቆይና በኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር የሚደረግበት ኮማንድ ፖስት ተግባራዊ እንዲደረግ ተወሰነ፡፡

ባሳለፍነው ሚያዚያ 2011 ዓ.ም በቤኔሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን አይሲካ በሚባል አካባቢ በሁለት ግለሰቦች መካከል የተፈጠረው ግጭት እየሰፋ ሄዶ ብሔር ተኮር ግጭት እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑ ይታወሳል፡፡

የግለሰቦች አለመግባባት ለፀረ ሠላም ኃይሎች ዕድል መፍጠሩን ነው የአማራና የቤኔሻንጉል ጉምዝ ክልል ከፍተኛ መሪዎች የተናገሩት፡፡ በዚህም እስካሁን ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ዜጎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈፅሞባቸዋል፤ ሀብትና ንብረታቸውም ተዘርፏል እንዲሁም አካባቢያቸውን ጥለው ተሰድደዋል፡፡

የተፈጠረውን አለመረጋጋት እልባት ለመስጠት ሙከራ ቢደረግም ችግሩን ማስቆም አለመቻሉም ተነግሯል፡፡ ለችግሩ እልባት ለመስጠት ከሐምሌ 5 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በኢፌዴሪ ሀገር መከላከያ ሠራዊት የሚመራ ኮማንድ ፖስት ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት በመከረው የኮማንድ ፖስቱ የፀጥታ ዕቅድ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ተግባራዊ በሚሆነው ኮማንድ ፖስት መሠረት በሁለቱ ክልሎች ባሉ ወረዳዎች 10 ኪሎ ሜትር ርቀት በአጠቃላይ በ20 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ ቀስትና የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከለ ሆኗል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት የሚያስተዳድራቸው የአማራ እና የቤኔሻንጉል ጉሙዝ ወረዳዎችም ተለይተው ታውቀዋል፡፡ ከአማራ ክልል ጃዊ፣ ጓንጓ፣ ዚገምና ቋራ ወረዳዎች እንዲሁም ከቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል ድባጤ፣ ማንዱራ፣ ግልገል በለስ፣ ፓዊ፣ ዳንጎርና ጉባ ወረዳዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡

የኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ኃይል የተሰጠውን ግዳጅና ኃላፊነት በሀገራዊ ስሜት እንደሚሠራ በመድረኩ ተገልጿል፡፡ ተፈናቃዮችን ወደ ነበሩበት ቀየ የማስመለስ ሀብትና ንብረታቸውን የማቋቋም ተግባር እንደሚሠራ የሁለቱ ክልል የሠላምና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊዎች በውይይቱ ወቅት ገልፀዋል፡፡

እስከ ሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ተፈናቃዮችን ወደየመጡበት አካባቢ ለማስመለስ እንዲቻል ውይይት እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡ በማጠቃለያቸውም የሁለቱ ክልል ሕዝቦች የቆየ አንድነትና ኅብረታቸውን ለማስቀጠል እንዲቻል የጋራ አቋም መግለጫ በማውጣት አጠናቅቀዋል፡፡

ምንጭ፦ አብመድ

@tsegabwolde @tikvahethiopia

Report Page