COVID19

COVID19


የኮቪድ-19 (የኮሮና ቫይረስ በሽታ) አስመልክቶ የተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ

የካቲት 10/2012

ሀገር ዓቀፍ፦

• ከጥር 15/2012 ጀምሮ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በ7ቱ መግቢያዎች 146,357 በላይ የሚሆኑ መንገደኞች በሙቀት ልየታው ያለፉ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 3,901 በሽታውን ሪፖርት ካደረጉ ሃገራት የመጡ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በሁሉም ወደ ሀገር መግቢያ ጣቢያዎች 248,734 በሙቀት መለያው አልፈዋል፡፡ እንዲሁም 697 የሚሆኑት ደግሞ ባሉበት ቦታ ሆነው የጤና ክትትል አየተደረገላቸው ሲሆኑ እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮና ቫይረስ በሽታ ያለበት ሰው የለም፡፡

• ከጥር 15/2012 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ 60 ጭምጭምታዎች ለኢንስቲትዩቱ የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል (Emergency Operation Center) ደርሰው በሁሉም ጥቆማዎች ላይ ማጣራት ተደርጓል፡፡

• ከነዚህም ጥቆማዎች 17ቱ የበሽታውን ምልክቶችን በማሳየታቸው እና የቻይና ጉዞ ታሪክ ስላላቸው በተለያየ ጊዜ በለይቶ ማቆያ ማእከል እንዲቆዩ ተደርጓል፡፡ በመሆኑም 17ቱንም የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው በመረጋገጡ ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል፡፡

• ይህ መረጃ እስከ ተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ አንድ የበሽታውን ምልክት ያሳየ ሰው በሽታው እንደሌለበት እስኪረጋገጥ ድረስ በለይቶ ማቆያ ማዕከል ውስጥ የህክምና ክትትል እየተደረገለት ቆይቶ ከቫይረሱ ነጻ መሆኑ በመረጋገጡ ከማዕከሉ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡

• ቁልፍ የኮሮና ቫይረስ በሽታ (COVID-19) መከላከያ መልዕክቶችን በሀገር ውስጥ እና በውጪ ቋንቋዎች ተዘጋጅተዋል፡፡

• ለተለያዩ የፌደራል ሚኒስቴር መስሪያቤቶች የህዝብ ግንኙነት ሀላፊዎች ስለ ኮሮና ቫይረስ (COVID-19) የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ተግባቦት( risk communication) ስልጠና ተሰጥቷል ፡፡

• የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና ከጤና ሚኒስቴር የተውጣጡ አካላት የኢንስቲትዩቱን አደጋዎች ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል፣ የኢንስቲትዩቱን ላቦራቶሪ እና ኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታልን ጎብኝተዋል፡፡

ጥንቃቄ መደረግ ያለባቸው ጉዳዮች

የኮሮና ቫይረስ በሽታ (ኮቪድ-19) ካለባቸው አገሮች የመጡ ከሆነ፦

• እራስዎን ከሌሎች ሰዎች እና ከቤተሰብ አባላት ለ14 ቀናት በማግለል ጤናዎን ይከታተሉ!

• በየዕለቱ የጤናዎትን ሁኔታ ለመከታተል ለሚደውሉ ባለሙያዎች ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ይተባበሩ!

• ትኩሳት፣ ሳልና የመተንፈስ ችግር ካጋጠመዎት ላስቸኳይ የህክምና እርዳታ 8335 ይደውሉ፤

• በሚያስሉበት እና በሚያስነጥሱበት ጊዜ አፍና አፍንጫዎትን ክንድዎን በማጠፍ ወይም በሶፍት ይሸፍኑ፤ እጅዎን በሳሙናና በውሃ ይታጠቡ!

• በተጨማሪም ህብረተሰቡ በሀገራችን እስካአሁን በቫይረሱ መያዙ የተረጋገጠ ሰው አለመኖሩን አውቆ ሳይዘናጋ የበለጠ ጥንቃቄ ኢንዲያደርግ ኢንስቲትዩቱ ያሳስባል፡፡

ለተጨማሪ መረጃ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም በመደበኛ የስልክ ቁጥር 0118276796 ወይም በኢሜል አድራሻችን ephieoc@gmail.com በመጠቀም ማግኘት ይቻላል፡፡

Report Page