#CMD

#CMD


በጌዴኦ ዞን ሰላምና መረጋጋትን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን በዞኑ የተቋቋመው ንዑስ ኮማንድ ፖስት ገለጸ፡፡

ንዑስ ኮማንድ ፖስቱ በዞኑ ነባራዊ ሁኔታ ላይ ከባለ ድርሻዎች ጋር ትናንት በዲላ ውይይት አካሂዷል።

የንዑስ ኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ ኮሎኔል መስፍን በየነ የዞኑን ሰላም ወደ ቀደመው ደረጃ ለመመለስ በመሰራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ንዑስ ኮማንድ ፖስቱ ሥራ በጀመረበት በአጭር ጊዜ መደበኛ ሰላም የማስከበር ተግባሩን የሚደግፍ ውጤት መመዝገባቸውን አስታውቀዋል፡፡

በተለይም ከሲዳማ ዞን ወንጀል ሰርተው በዞኑ የተሸሸጉና በምዕራብ ጉጂ ዞን በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ላይ የሚወሰደውን እርምጃ የሚያደናቅፉ ኃይሎችን ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጸጥታ አከላት መካከል ተናቦና ተቀናጅቶ ለመሥራት የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት እንደሚያስፈልግም ሰብሳቢው አመልክተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በክልሉ የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ወደ ነበረበት ለመመለሰ እየተከናወኑ ያሉት ተግባራት ተገቢነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

በተለይ በዞኑ ገጥሞ የነበረው የጸጥታ ችግር ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመትና የዜጎች የመዘዋወር መብት መከበር እንዳለበት በአጽንኦት ተናግረዋል።

የዞኑ ዐቃቤ ህግ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ቦኮ እንደገለጹት የአጎራባች አካባቢዎች የጸጥታ ስጋትን የሚያባብሱ አዝማሚያዎችን በመቆጣጠር ረገድ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡

የተቀመጡ ክልከላዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማስጨበጥ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የዞኑ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ስዩም በበኩላቸው ለአከባቢው የጸጥታ ስጋት መፈጠር ምክንያት ለሚሆኑ ጉዳዮች በተለይም በኮንትሮባንድ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡

ከአጎራባች ወረዳዎች የጋራ ጥምር ኃይል ለማቋቋም ጥረት በመደረግ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

በዞኑ ኮማንድ ፖስት የተቋቋመው ሰላምና መረጋጋትን በማስጠበቅ ሕዝቡ ሰላማዊ ሕይወቱን ለመምራት እንደሚያስችል ይታወቃል።

Via #ENA

Report Page