Che Guevara

Che Guevara

Abrish

ጎቬራ - የአብዮቱ አውራ!

* * *

🏁በ60ዎቹ የነበረው የኛ ሃገር ትውልድ ስሙን ስንኝ መሀል ሰድሮ <ፋኖ ተሰማራ ፣ ፋኖ ተሰማራ እንደ ሆቺሚኒ እንደ ቼጎቬራ> ብሎለታል ፣ ብሎበታል።


ኤርኔስቶ ቼ ጎቬራ!


🏁ወላጆቹ ያወጡለት ስም ኤርኔስቶ ጎቬራ ነው ፦ የወደዱት ኩባዎች ግን ስሙ መሀል <ቼ> ብለው ጨመሩለት። <ቼ> ማለት የእኛ እንደ ማለት ነው። ቼ ጎቬራ ለአንዳንዶች ጀግና ለሌሎች ደግሞ የክፋት ምሳሌ ነው። የብዙ ወጣቶች ጣኦት፣ የብዙ አብዮተኞችም መንገድ ነበር ቼጎቬራ።


🏁ቼ ሰኔ 14 ፣ 1928(እ.ኤ.አ) በአርጀንቲና ተወለደ። ቤተሰቦቹ ልጥጥ ያሉ ሃብታሞች ባይሆኑም ያላቸው የሚባሉ ናቸው። ቼ ግን ገና በማለዳው ጭቁኑ ማህበረሰብ፣ ተበዝባዡ ሰርቶ አደር ወደ ሚለው የግራ ዘመም ርእዮተ አለም ዘመም አለ።


🏁በ1948(እ.ኤ.አ) ወደ ቦነስ አይረስ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ የህክምና ትምህርቱን ተምሮ ዶክትሯል! ዶክተር ጉቬራ ተባለ። ቼ ግን ብዙም ሳይሰነብት ፣ የዱክትርና ስራውን ትቶ፣ መርፌውን አስቀምጦ ልቡ ላይ ያበበውን አብዮተኝነት አቅፎ ወደ ኩባ አቀና፤ ዶክተሩ አብዮተኛ ሆነ። በመቀጠል ቼ ወደ ኩባ አቀና. . .


🏁ቼ ጎቬራ ወደ ኩባ ሲያቀና ፊደል ካስትሮ የኩባ መሪ አልሆነም፡፡ እሱም ገና አብዮተኛ ነው፡፡ እኚህ ሁለቱ አብዮተኞች ግን በ1955 (እ.ኤ.አ) በሜክሲኮ ተገናኝተዋል፤ ልብ ለልብ ተናበዋል፡፡ ቼ ወደ ኩባ ሲያቀና ይሄ ከካስትሮ ጋር የፈጠረው ወዳጅነት መንገድ ጠርጓል፡፡ በኩባ ፊደል ካስትሮ የባስቲታን መንግስት በቂጡ ቁጭ ለማድረግ እየለፋ ነው፡፡ ቼ እኔም አለሁበት ብሎ ገባ፡፡ ዓለም ሁሉ ዜጋዬ፣ ጭቁን ሁሉ ወገኔ ብሎ ከኩባዊያኑ ጋር ተሰለፈ፡፡ ለአብዮቱም ድንቅ ግብዓት ሆነ፡፡ ጠዋት ሲተኩስ ውሎ ከሰዓት በህክምና ሙያ በጦርነቱ ለተጎዱ ደረሰ፡፡ ሁሉን እንደወደደ እንዲሁ ሁሉ ወደደው፡፡ የነፊደል ካስትሮ አብዮት በ1959 (እ.ኤ.አ) ተሳካ። እነ ፊደል ካስትሮ ባቲስታን ከወንበሩ ጣሉት፡፡ ከአብዩቱ ስኬት በኋላ ቼ ጉቫራ የኩባ ብሔራዊ ባንክ ፕሬዘደንት እና የኢንደስትሪ ሚኒስትር ሆኖ ተሸመ፡፡ የአገሪቱ አምባሳደር ሆኖም ከሀገር ሀገር ተዘዋወረ፡፡ ይሄን አብዮተኛ ዓለም ሁሉ አወቀው፡፡ የኮሚኒስቱ ዓለም ከልቡ ሲወደው፣ ካፒታሊስቶቹ ከልባቸው ጠሉት፡፡


🏁የአብዮተኞች አርማ፤ የዜማቸው ግርማ ሆነ፡፡ ፎቶዎቹ የቲሸርቶች አካል ሆኑ፡፡ አሜሪካ ፈራችው፡፡ CIA ጥርሱ አስገባው፡፡ ለነገሩ ቼም አሜሪካን አምርሮ ነው የሚጠላት፡፡ አሜሪካን በመጥላቱ ኩባን ከሶቪየት ዩኒየን አወዳጃት፡፡


🏁የቼ ልብ ውስጥ ያሉት የዓለም ጭቁኖች ናቸው፡፡ ዜግነቴ ሰዎች፣ ከሰዎችም ጭቁን ሰዎች ናቸው ብሏል፡፡ የኩባ አብዮት በተሳካ በስድስት ዓመት ውስጥ እስቲ ደሞ ሌላ ቦታ ማርክዚዝምን ላስተምር ብሎ ኩባን ጥሎ ወጣ፡፡ ወደ አፍሪካ በተለይም ወደ ኮንጎ መጣ። በኮንጎ ማዕከላዊ መንግስቱን ለመጣል ከተሰለፉ ሰዎች ጋር አብሮ ነፍጥ አነሳ! ቢሆንም ኮንጎ ላይ እንደ ኩባ አልተሳካም፡፡ ጎበዝ፣ የአፍሪካ መሪ ስልጣን ከያዘ ያዘ ነው፤ በቀላሉ ፍንክች አይልም፡፡


🏁በ1966 (እ.ኤ.አ) ወደ ቢሊቪያ አቀና፡፡ በቦሊቪያ ያለው መንግስት ጨቋኝ መሆኑን ተረድቷል፡፡ ከስልጣን መውረድ አለበት፤ ሊያወርዱት የሚጥሩትም መታገዝ አለባቸው ብሎ አብዮት መዝሙሩን እየዘፈነ ወደዛ ሄደ፡፡ በቦሊቪያ ከታጣቂዎቹ ጋር ታጠቀ፡፡ ጥያቄያችሁ ጥያቄዬ ብሎ ነፍጥ ይዞ ተሰለፈ፡፡ ግን በቦሊቪያ ዓመትም ሳይቆይ በCIA በሚታገዙ የቢሊቪያ ወታደሮች ተያዘ፡፡ በተያዘ በቀጣዩ ቀን ተገደለ፡፡ የሰው ፍቅር ሀገሬ ያለው ቼ በ39 ዓመቱ ከብዙ ትልሙ ብዙ ሳያሳካ ምድርን ተሰናበተ፡፡


🏁የሚጠሉት፣ ኮሚኒዝምን የሃይማኖት ያህል አጥብቆ ይዞ በኮሚኒዝም ስም የሚፈፀም ጭቆናን አብርዶ ያየ፣ ለጭቆና መሳሪያ የሆነ ይሉታል፡፡ የሚወዱት ለሚያምንበት ኖሮ፣ ለሚያምንበት የሞተ፤ ለነፃነት የታገለ የዓለም ዜጋ ይሉታል፡፡


🏁ሰውየው ደግሞ እንዲህ ይላል ‹‹በኢፍትሐዊነት ንዴት ውስጥህ ክፉኛ ከተቆጣ አንተ የኔ ጓድ ነህ!›› እንዲህም ብሏል፣ ‹‹ ጠመንጃዬን ሌላ ሰው አንስቶ ትግሉን እስከቀጠለ ድረስ ለሞቴ ግድ፤ ነፃ አውጪ አይደለሁም፡፡ ነፃ አውጪ ብሎ ነገር የለም፡፡ ነፃ መውጣት የሚኖረው ሕዝቦች እራሳቸውን ነፃ ሲያወጡ ነው›› አለም!


🏁.....‹‹አትተኩሱ፡፡ ጉቬራ ነኝ፡፡ ከመሞቴ በላይ ቆሜ እጠቅማችኋለሁ›› ብሎም ነበር። መኖሩ እንቅልፍ የነሳቸው የCIA ሰዎች ግን ለሞቱ ተጣደፉ፡፡ ተያዘ፡፡ ተገደለም! ሬሳው ሚዲያዎች እንዲያዩትም፣ ፎቶ እንዲያነሱትም ተደረገ፡፡ በጊዜው የትነቱ ያልታወቀ ቦታ ተቀበረም፡፡ በ1997 (እ.ኤ.አ) የተቀበረበት ቦታ እና አስክሬኑ ተገኘ፡፡ ወደ ኩባ ተወስዶ ዳግም ተቀበረ፡፡ ቼ ግን ዛሬ ድረስ ግን ለብዙዎች አልሞተም! ዛሬም ቼ የእኛ፣ ቼ ጀግናችን የሚሉት አሉ!

https://telegram.me/EAblogging

Report Page