BIBLE

BIBLE

Henok Tsegaye

በቤታችሁ ለተቀመጣችሁ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ያመቻችሁ ዘንድ ይህን መግቢያ አዘጋጅቸላችኋለሁ።


✝የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መግቢያ ✝ 

መጽሐፍ ቅዱስ ምንድነው? 🗝

መጽሐፍ ቅዱስ ቃሉ እንደሚያመለክተው መጽሐፍ እና ቅዱስ የሚሉ የሁለት ቃላት ጥምረት ነው ፡፡ 

★“መጽሐፍ” ለሚለው ምንጭ በግሪክ ቋንቋ ቢብሎስ (byblos) ከደንገል በተሠራ ወረቀት ወይም በብራና ከተጻፈ በኋላ በሁለት በትሮች የሚጠቀለል መጽሐፍ ያመለክታል፡፡ ይህ ስም ቢብሎስ (byblos) ከተባለ ከተማ ስም የተገኘ ነው ፤ እርሱም ከኒቂያ ወደቦች መካከል በቤይሩት 25 ማይል ያህል ርቆ የሚገኝ አገር ነው ፡፡ ለመጽሐፍ ያገለግል ዘንድ ፓፒረስ (ደንገል) የተባለውን ተክል እንደ ወረቀት አድርገው ይሠሩበት የነበረ ቦታ ነው ፡፡ቢብሎስ በእንግሊዘኛው ባይብል ተብሎ ሲተረጎም በአማርኛው ደግሞ መጽሐፍ በሚለው የግብር ስም ቃል ተተረጐመ ፡፡ 

★“ቅዱስ” (holy)የሚለውን ስናይ ደግሞ ልዩ፣ክቡር ለእግዚአብሔር የተለየ ማንኛውንም ነገርን ያመለክታል፡፡እግዚአብሔር በራሱ የተለየ ነው መንፈሱም(ሐሳቡም) ከክፋት ሐሳብ የተለየ ስለሆነ ቅዱስ ነው፡፡ጠቅለል አድርገን ስናየው ስለ ቅዱሱ እግዚአብሔር ያለፈውም መጪውም ስራ፣በመረጣቸውና ባመኑበት ሰው ልጆች ላይ ያደረገውንና ያለው ሐሳቡ ፈቃዱ ወዘተ ላይ የሚያወራ መጽሐፍ ስለሆነ ቅዱስ መጽሐፍ ተብሏል፡፡በእንግሊዘኛውም “holy bible” በማለት ይጠራል፡፡

☞ መጽሐፍ ቅዱስ ሁለት ክፍሎችን የያዘ ነው::የመጀመርያው ክፍል #ብሉይ_ኪዳን ሲሆን የእግዚአብሔር የድሮው መሐላ(የአብርሐም ዘር እንደሚበዛና ከንአን ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያለው ምድር እንደሚሰጠው በዘሩም አለሙ ሁሉ እንደሚባረክ)የሚገልጽ ሲሆን

✡ እግዚአብሔር ፍጥረታትን ከመፍጠሩ ጀምሮ ስለ ሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ክብር መለየት አወዳደቅና በምድር ላይ መብዛት

✡በእግዚአብሔር ስለ ተወደደ አብርሐምና በዘሩ ዓለም እንደሚባረክ መሐላ

✡ስለ የያእቆብ ልጆች ወደ ግብጽ መሰደድና ከባርነት በእግዚአብሔር ድንቅ ረዲኤት መመለስ

✡ስለ እስራኤል መንግስት መመስረት መስፋትና የነገሥታቱ ታሪክ

✡መዝሙራትና ምሳሌያዊ የጥበብ ትምህርቶችን

✡ስለ ሰው ልጅ ወደ እግዚአብሔር ክብርና ፍቅር መመለስ ትንቢት ማለትም እግዚአብሔር ዓለሙን እንደሚያድንና ስለ እስራኤል ህዝብ ትንቢቶችን ይዟል::

☞ሁለተኛው ክፍል ደግሞ #ሐዲስ_ኪዳን ሲሆን ለአብርሐም በዘርህ አሕዛብ ይባረካሉ ያለውን ያ ዘር ክርስቶስ በስጋ ተገልጦ አለሙን በደሙ መስዋዕትነት ቀድሶ የሰውን ልጅ እንዳዳነ ያመኑበትም የእግዚአብሔር ልጆች የቅዱስ መንፈሱም ማደርያ ማድረጉን ለዓለሙ ሁሉ በደሙ በኩል አዲስ መሐላን ማድረጉ የሚገልጽ ሲሆን

❖ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ጀምሮ ስላስተማራቸው ትምህርቶች ስላደረጋቸው ተአምራት ስለ ሰው ልጆች ሐጢአት ዋጋ ካሳ እንዲሆን መከራ መቀበሉ መሞቱ ሞትን ድል አድርጎ መነሳቱ ለብዙዎች መታየቱን ማረጉን #በወንጌላት

❖ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ እንደተቀበሉና በጌታችን ኢየሱስ ስም የሐጢአት ስርየት መስበካቸውን ብዙ መከራ መቀበላቸውንና ብዙዎችን ማጥመቃቸውን #በሐዋርያት ሥራ

❖ስለ ጌታችን ኢየሱስ ማንነት፣ስለ አዲሱ መሐላ፣ስለ አማኞች ስነ ምግባር በእምነትም ስለመጽናት ፣በክርስቲያኖች መኖር ያለበት ፍቅር #በመልእክታት

❖ስለ መጪዋ ቤተ ክርስቲያን፣ ዲያብሎስ በዚህ ምድር ስለሚኖረው የክፋት አሰራርና ስለ ቤተ ክርስቲያን ፈተናዎች፣ስለ ሐሳዊው ክርስቶስና ስለ አዲሱ የአለም መንግስት አሰራር፣ ስለ ጌታችን ክርስቶስ ዳግም መምጣትና ስለዚህ አለም ማለፍ፣ስለ ክርስቲያኖች ተስፋ በአዲሲቷ ምድርና ሰማይ ከክርስቶስ ጋር ያለው ኑሮ #በራእይ ይዟል፡፡ 


✞❀✞❀✞❀✞❀✞❀✞❀✞

"የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።"

(ወደ ኤፌሶን ሰዎች 6:17፤)

✞❀✞❀✞❀✞❀✞❀✞❀✞

"የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።"

(2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13:14፤)


ሰፋ ያለ የአጠናን ዘዴን ለምትፈልጉ ይህን ሊንክ @henyrfcm ሰርች በማድረግ ልታናግሩኝ ትችላላችሁ።

ሔኖክ ጸጋየ ተክሉ

Report Page