#BG

#BG


በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል፤ መተከል ዞን፤ ማንዱራ ወረዳ ከዕሁድ ሌሊት ጀምሮ በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉንና በ13 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የመተከል ዞን አስተዳዳሪ አቶ ግርማ ታደሰ ለቢቢሲ ገለፁ።

ስለታም በሆኑ ቁሶችና በጦር መሳሪያ ጥቃቱ እንደተፈፀመ የሚናገሩት አቶ ግርማ ጉዳት ያጋጠማቸው ግለሰቦች በፓዊና ቻግኒ ሆስፒታሎች ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ገልጸዋል።

አስተዳዳሪው እንዳሉት በቀበሌው ውስጥ አንድ ቤት ተቃጥሏል፤ ሁኔታውን በማረጋጋት ላይ የነበረ አንድ የመከላከያ ሠራዊትም ላይ ጉዳት ደርሷል።

ጥቃቱ ሰኔ 29 ቀን 2011 ዓ.ም ሌሊት ላይ ያልታወቁ ሰዎች በወረዳው ገነተ ማሪያም ቀበሌ ሊቀመንበር ቤት ውስጥ በመግባት መሳሪያውን ቀምተው፤ በጩቤ ጉዳት አድርሰውበት ከሄዱ በኋላ ግጭቱ እንደተከሰተ አቶ ግርማ ያስረዳሉ።

በዚህም ምክንያት የሊቀመንበሩ ቤተሰቦች ከተለያዩ ጎጦች ተውጣጥተው በመምጣት ቀበሌዋን ከበው ባገኗቸው በሰዎች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ይናገራሉ።

"ከዚህ ቀደም በአካባቢው በተፈጠረው ችግር ማህበረሰቡ እርስ በርሱ እየተማመነ ስላልሆነ፤ ከዚያ ጋር የተያያዘ ይመስላል" ብለዋል- አቶ ግርማ።

ከዚህ በፊት ጃዊ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት የሚያስታውሱት አቶ ግርማ አሁን ላይ የበቀልና የአፀፋ ስሜት በተለያዩ አካባቢዎች በስፋት እየታየ እንደሆነ አስረድተዋል።

ጥቃቱ ከተከሰተ በኋላ አካባቢውን ለማረጋጋት ጥረት እየተደረገ እንደሆ የመተከል ዞን አስተዳዳሪ ተናግረዋል።

ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ የማንዱራ፤ ገነተማሪያም ቀበሌ ነዋሪም የግጭቱን መነሻ ምክንያት የገነተ ማሪያም የቀበሌ ጥበቃ ላይ ባልታወቁ ሰዎች ጥቃት መፈፀሙ እንደሆነ ይናገራሉ።

ነዋሪው እንደሚሉት በግለሰቡ ላይ ጥቃት የፈፀሙት ሰዎች ያልታወቁ ቢሆንም፤ ይህ እንደምክንያት ተደርጎ 'ቱራ'[የድግስና የዘፈን መሳሪያ] እርሱን በመንፋት በሁሉም አቅጣጫ የሚኖሩ የጉምዝ ነዋሪዎች እንዲሰባሰቡ ተደረገ ይላሉ።

ከዚያም በእርሻ ሥራ ላይ የነበሩ ሰዎች ላይ ጥቃት እንደሰነዘሩና ወደ ከተማ በመግባትም ቤት እንዳቃጠሉ ነዋሪው ነግረውናል።

"እስካሁን ያልተሰበሰበ አስክሬን አለ፤ በርካታ ሰዎችም ሕይወታቸውን አጥተዋል" ሲሉም ያክላሉ።

ትናንት መከላከያ ከገባ በኋላ በአንፃሩ የተረጋጋ ቢሆንም ዛሬም ተመሳሳይ ስጋትና ፍርሃት እንዳለ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

Via #BBC

@tsegabwolde @tikvahethiopia

Report Page