#BG

#BG


በቤኔሻጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን የፀጥታ መደፍረስ መከሰቱና ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በቤኔሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ በደረሰ ግጭት የሰው ሕይወት ማለፉን ነዋሪዎችና የክልሉ የሠላም ግንባታና ፀጥታ ጉዳይ ቢሮ ለአብመድ ተናግረዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ለግጭቱ ምክንያት ያሉትንም ገልጸዋል፡፡ ‹‹ቅዳሜ አመሻሽ ላይ የጉምዝ ማኅበረሰብ አባል የሆኑ አንዲት ሴት በመኪና ተገጭተው ጉዳት ደረሰባቸው፡፡ ሌላ አንድ የጉምዝ ማኅበረሰብ አባትም በቤታቸው ጥቃት ደረሰባቸው፡፡ በዚህ ሰበብ ግጭቱ የብሔር መልክ ይዞ ተነሳ›› ብለዋል ነዋሪዎቹ ለአብመድ በሰጡት አስተያዬት፡፡ በአንድ የኢትዩ-ቴሌኮም የጥበቃ ሠራተኛ ላይ ጉዳት በመድረሱ ግጭቱ እንደተነሳ የተናገሩ ነዋሪዎችም አሉ፡፡

ከግጭቶቹ መነሳት በኋላ የተደራጀ እና የታጠቀ ቡድን በገነተ ማሪያም ቀበሌ በአራቱም አቅጣጫ በመግባት ጉዳት ማድረሱንም ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት፡፡ የታጠቀው ቡድን በተደጋጋሚ ጥቃት ለማድረስ ጥረት ሲያደርግ መቆዬቱን እና ትናንት ጥቃቱን እንደፈጸመም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡

ይህን ምክንያት አድርጎ በተነሳው ግጭትም የሰው ሕይወት ማለፉን፣ ንብረት መውደሙን እና በአካል ላይ ጉዳት መድረሱን ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት፡፡ ግጭቱን ለማብረድ ወደስፍራው የገባው የፀጥታ አካል ‹‹ትዕዛዝ አልተሰጠኝም›› በማለት ችግሩን እያበረደው እንዳልሆነም ነው ነዋሪዎቹ አስተያየዬታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ለፀጥታ አካሉ በአፋጣኝ ትዕዛዝ ተሰጥቶ ችግሩን ካልተቆጣጠረው ቀያቸውን ለቀው ለመውጣት በቋፍ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡ በተለይም በገነተ ማሪያም ቀበሌ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደተቋረጠም ነው የተናገሩት፡፡ ከተለያዩ አካባቢዎች በቡድን ተደራጅተው የሚመጡ ቡድኖች እንዳሉ እየተወራ በመሆኑ ስጋት ውስጥ እንደገቡም ገልጸዋል፡፡

የቤኔሻንጉል ጉምዝ ክልል የሠላም ግንባታና ፀጥታ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ አበራ ባታዬ በተነሳው ግጭት የሰው ሕይወት መጥፋቱን፣ ንብረት መውደሙን እና አካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች መኖራቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች በፓዊ ሆስፒታል የሕክምና ዕርዳታ እየተደረገላቸው እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ኃላፊው ለችግሩ መነሻ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ለአብመድ የገለጹ ሲሆን እርሳቸው የጠቀሱት ምክንያት ከነዋሪዎቹ የተለዬ ነው፡፡ ‹‹በገነተ ማርያም ቀበሌ ምክትል አስተዳደሪ ላይ ጥቃት በማድረስ የመሳሪያ ዝርፊያ መፈጸሙ ለግጭቱ መነሻ ነው›› ብለዋል አቶ አበራ፡፡

ችግሩን ለማብረድ የክልል የፀጥታ ኃይል፣ የፌደራል ፖሊስ እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት ወደስፍራው እንደገቡም ገልጸዋል፡፡ የፀጥታ ኃይሉ ወደ ስፍራው የገባው ችግሩን ለማብረድ እስከሆነ ድረስ ‹ትዕዛዝ አልተሰጠኝም› የሚል ኃይል እንደማይኖርም ተናግረዋል፡፡ በስፍራውም ችግሩን ሊያበርድ የሚችል በቂ የፀጥታ ኃይል እንዳለ ገልጸው ችግሩን ለማረጋጋት ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች በቅንጅት እየሠሩ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ከፌዴራል የሠላም ሚኒስቴር መረጃ ለማግኘት ጥረት እያደረግን ነው፤ መረጃዎችን እንዳገኘን የምናደርስ ይሆናል፡፡

Via #AMMA

@tsegabwolde @tikvahethiopia

Report Page