#BC

#BC


ሁሉም ኢትዮጵያዊ በነፃነት የሚኖርባት ኢትዮጵያን ለመገንባት እንደሚሰሩ በባሕር ዳር የሚገኙት የሶማሌ ክልል ልዑክ አባላት ተናግረዋል፡፡

ለሕዝብ ለሕዝብ ትስስርና ለሥራ ጉብኝት በአማራ ክልል የሚገኙት የሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጦፋ ሙሐመድ ከልዑካቸው ጋር ጣና ሀይቅ እና ቤዛዊት ተራራን ጎብኝተዋል፡፡

አስተያዬታቸውን ለአብመድ የሰጡት አቶ ሙስጦፋ ‹‹በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመዘዋወር ኢትዮጵያውያን በሰላም እንዴት መኖር እንደምንችል እና በሕዝብ መካከል ምንም አይነት ጥላቻ እንደሌለ እያሳየን በግንባር ቀደምነት እንጓዛለን›› ብለዋል። የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩ የተዘራውን የውሸት ትርክት ማርከሻ መድኃኒት እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡ ሕዝቡ በተደጋጋሚ እየተገናኘ አንድነቱን ማጠናከር፣ የስህተት ትርክቱንም ማረም ይገባዋል ብለዋል ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ።

በተለይም በአሁኑ ትውልድ በሀገራችን ታሪክ ላይ የተለያዩ ንትርኮች አሉ ያሉት አቶ ሙስጦፋ ለፖለቲካ ትርፍ ሲባል የሚነገረው ታሪክ ሕዝቡን የተለየ አመለካከት እንዲይዝ እንደሚያደርገው አስገንዝበዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ጨቋኝ እንደነበር ተደርጎ በሶማሌ ክልል የውሸት ትርክት ሲነገር እንደነበር ያነሱት አቶ ሙስጦፋ ‹‹ትርክቱ ለመጨረሻ ጊዜ ያበቃለታል፤ ለሕዝቡም ይሰራጭ የነበረው ታሪክ ውሸት እንደነበር እያስተማርን ነው›› ብለዋል። ይህም ከፍተኛ መስተካከል እና የሀሳብ ለውጥ እንዳመጣ ነው የተናገሩት።

አቶ ሙስጦፋ ‹‹የአማራን ሕዝብ እና የአማራን መንግስት ጅግጅጋ እንዲመጡ እንጋብዛቸዋለን፤ ሰፊ ውይይትም እናደርጋለን›› ብለዋል። የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩን በመላው ኢትዮጵያ ለማጠናከር እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡

የሚያስደንቅ ውበት እና የተከበረ አካባቢ የሆነውን ጣናን መጎብኘት ያለበት የውጭ ዜጋ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ አስደናቂ መሆኑን አውቆ ወደ ስፍራው መምጣት እንዳለበትም ነው የተናገሩት፡፡ ‹‹ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም ክልል እና አካባቢ በሰላም የመኖር ሙሉ መብት አለው፤ ይህን ደግሞ መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ዜጋ ሊያውቀው ይገባል›› ብለዋል። አይደለም ኢትዮጵያዊ፣ ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ዜጋ በሰውነቱ ብቻ በሰላም መኖር እና መስራት መቻል እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡት፡፡

‹‹እኛ በሰብዓዊነት እና በአንድነት የምናምን ሕዝቦች ነን›› ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በሚያስተዳድሩት ክልል ማንኛውም ዜጋ በነፃነት፣ በፍቅር እና በሰላም እንዲኖር በተግባር እያሳዩ እንደሆነም አንስተዋል። ከአቶ ሙስጦፋ ሙሐመድ ጋር የመጡት ልዑካንም በጣና ሀይቅ ገጽታ እና በተደረገላቸው አቀባበል ተደንቀው ሁሉም ኢትዮጵያዊ በነፃነት የሚኖርባት ኢትዮጵያን ለመገንባት እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

Via #AMMA

@tsegabwolde @tikvahethiopia

Report Page