#BBC

#BBC


ከጥቂት ወራት በፊት በፓርላማ የፀደው የምርጫ አዋጅ በተቃዋሚ ፖለቲከኞች ብዙ ተቃውሞዎች ቀርበውበታል። በተለይም እንደ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስና ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ያሉ አንጋፋ ፖለቲከኞች የተወሰኑት የአዋጁ አንቀፆች ላይ ብርቱ ትችት ሲሰነዝሩ ቆይተዋል።

አዋጁ ፓርቲዎች ለመመዝገብ የአስር ሺህ መስራች አባላት ፊርማ ማሰባሰብ አለባቸው ማለቱ በተለይም እንደ እነሱ ላሉ ነባርና ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ በምርጫ የተሳተፉ ፓርቲዎች ፍትሃዊ አይደለም በማለት ሲተቹና ሲከራከሩ ቆይተዋል።

ፕ/ር መረራና ፕ/ር በየነ ቀደም ባሉት ዓመታት እንደ አቶ መለስ ዜናዊና አቶ በረከት ስምኦን ካሉ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ጋር ተከራክረው ያስቀሯቸው ተገቢ ያልሆኑ አንቀፆች በዚህ አዲስ አዋጅ ተካትተው እንዲፀድቁ መደረጉን ይኮንናሉ።

ቀደም ሲል ፕ/ር መረራ አስር ሺህ የመስራች አባላት ፊርማ ማሰባሰብ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚጠይቃቸው ሲገልፁ፤ ፕ/ር በየነ ደግሞ ነባር ፓርቲ ሆነው ሳሉ እንደ አዲስ ተመዝገቡ መባላቸው ፍትሃዊ ስላልሆነ ጉዳዩን ወደ ህግ ለመውሰድም እያሰቡ እንደሆነ ገልፀውልን ነበር።

እስካሁን እየተባለ ባለው ምርጫው ሊካሄድ አራት ወራት ገደማ ቀርተውታል። በእነዚህ አንጋፋ ፖለቲከኞች የሚመሩት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ( ኦፌኮ) እና የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ የምዝገባቸውን ጉዳይ ከምን አደረሱት?

ምንም እንኳ 70 የሚሆኑ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጁ ላይ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ቢሆንም ምርጫ ቦርድ ነገሮችን በጀመረው መንገድ ማስኬድ ቀጥሏል የሚሉት ፕ/ር በየነ ባለፈው ሳምንት ቦርዱ ቀነ ገደብ ሊያስቀምጥ በመሆኑ ቅድመ ሁኔታዎችን አጠናቅቀው እንዲቀርቡ እንዳስታወቃቸው ይገልፃሉ።

ቀደም ሲል እንዳሉት ነባር ፓርቲዎች ፊርማ ሰብስበው እንደ አዲስ ይመዝገቡ የመባሉን ጉዳይ ወደ ህግ እንወስዳለን ቢሉም እርምጃው ምን ያህል ያዋጣል? በሚል ግምገማና በሰዎችም ምክር ሃሳባቸውን መቀየራቸውን ይናገራሉ።

"ኋላ ቀር በሆነ አገር ከመንግሥት ጋር መካሰስ የትም የሚያደርስ አይደለም። ቂም ይያዝብናል ለቀጣዩ እንቅስቃሴያችን ሁሉ ችግር ይፈጥርብናል" በማለት ውሳኔያቸውን ያብራራሉ።

በተግባር እያደረገ ካለው ነገር በመነሳት ምርጫ ቦርድ ነባር ፓርቲዎችን ከጨዋታ ውጭ የማድረግ ፍላጎት አለው ብለውም ያምናሉ።

አዋጁን አጥብቀው ቢቃወሙም መመዝገባቸው ግድ ስለሆነ በየቅርንጫፎቻቸው የአባሎቻቸውን ፊርማ ለማሰባሰብ መመሪያ ሰጥተው እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ፕ/ር በየነ ጠቁመዋል።

"በህግ አምላክ ብንልም የሚሰማን አጥተናል" የሚሉት ፕ/ር በየነ ምናልባትም እንደሚፈለገው 'አቅም አጥተው ሲያቅታቸው ቤታቸው ገቡ' እንዳይባል የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ ይናገራሉ።

ምን ያህል ይሳካላቸዋል የሚለው ወደ ፊት የሚታይ ነው።

"እንደ ምገምተው በሁለት ወር ውስጥ ጨርሱ የሚል ቀነ ገደብ ይመጣል። ምርጫ ቦርድ አሁን እያሳየ ካለው የማይገመት ባህሪ አንፃር በ15 ቀን ውስጥ ጨርሱ ሊልም ይችላል" ሲሉ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

በሌላ በኩል ፕ/ር መረራም ተገድደው አዲሱ የምርጫ አዋጅ በሚለው መንገድ ለመመዝገብ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ይናገራሉ።

"በውዴታ ሳይሆን በግዴታ ወደዚህ ነገር ውስጥ ገብተናል። ግን ተቃውሟችንን እንቀጥላለን" የሚሉት ፕ/ር መረራ በፀደቀ አዋጅ እንዲሁም ምርጫ ሊካሄድ ከአራት ወር ብዙም የማይበልጥ ጊዜ ተቃውሞ ውጤት ያመጣል ወይ? የሚል ጥያቄ አንስተን ነበር።

"ምናልባትም የታሰበው እኛን ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ ስለሆነ ከምርጫ ውጭ እንዳንሆን ነገሮቻችንን መስራት እንጀምራለን ማለት ነው" የሚል ምላሽ ነበር የሰጡት።

ሁለቱም የፓርቲ መሪዎች ምዝገባን ከሚመለከተው አንቀፅ ባሻገር በምርጫ የሚሳተፉ የመንግሥት ሰራተኞችን የሚመለከተውን አንቀፅም ይኮንናሉ።

ቀደም ሲል ባነጋገርናቸው ወቅት ፕ/ር መረራ "የመንግሥት ሰራተኞች በምርጫ የሚወዳደሩ ከሆነ ስራ ይለቃሉ የሚለው አዋጁ እጅግ ነውር ነው" ብለው ነበር።

(BBC)

Report Page