#BBC

#BBC


የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሴት ልጅ ሰመሐል መለስ ትግራይ መቀለ ውስጥ ተይዛ እንደታሰረች እናቷ ወይዘሮ አዜብ መሰፍን ለቢቢሲ አረጋገጡ።

ወ/ሮ አዜብ ልጃቸው ሰመሐል በምን ምክንያት ለእስር እንደተዳረገች የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ለቢቢሲ ተናገረው፣ ወደ መቀለ የሄደችው ወታደራዊ ግጭቱ ከመጀመሩ በፊት እንደሆነ ገልጸዋል።

አዲስ አበባ የሚገኙት ወ/ሮ አዜብ ጨምረውም ሰመሐል ወደ መቀለ ያቀናችው በአባቷ የህይወት ታሪክ ላይ የተጻፈ መጽሐፍን ተንተርሶ የተዘጋጀን ቲያትር ለማስመረቅ በርካታ ሰዎች ካሉበት ቡድን ጋር መሆኑን አመልክተዋል።

ሰመሐል "የፖለቲካ አቋም ሊኖራት ይችላል። ነገር ግን የፖለቲካ ፓርቲ አመራርም፣ አባልም፣ ደጋፊም አልነበረችም" ያሉት እናቷ ወ/ሮ አዜብ መስፍን የእስሯ ምክንያት ምን እንደሆነ እንደማያውቁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከሰመሐል በተጨማሪ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ የተገደሉት ጀነራል ኃየሎም አርአያ ልጅ የሆነው ብርሐነመስቀል ኃየሎምም በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል።

ወ/ሮ አዜብ ከቀናት በፊት ልጃቸው ሰመሐል እየተፈለገች እንደሆነ በመስማታቸው አርብ ዕለት ወደ መቀለ ለመሄድ ፈልገው የነበረ ቢሆንም ፈቃድ ባለማግኘታቸው እንደቀሩና እሁድ ዕለት በቁጥጥር ሰር እንደዋለች መስማታቸውን ለቢቢሲ አብራርተዋል።

ሰመሐል በየትኛው አካል እንደተያዘችና ምክንያቱ ምን እንደሆነ ከአንዳንድ አካላት ለማወቅ ጥረት ማድረጋቸውን የሚናገሩት ወ/ሮ አዜብ ነገር ግን ምላሽ ለማግኘት እንዳልቻሉ ጠቅሰዋል።

ቢቢሲ ሰመሐል መለስ በቁጥጥር ስር ስለዋለችበት ምክንያትና ለማወቅ ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፕሬስ ሴክሬታሪያት አወል ሱልጣን እና የፌደራል ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጄይላን አብዲን ቢጠይቅም ስለጉዳዩ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

ሰመሐል መለስ የኢህአዴግ ሊቀ መንበርና ከ20 ዓመታት በላይ አገሪቱን የመሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና የወይዘሮ አዜብ መስፍን የበኩር ልጅ ስትሆን አስከ አባቷ ህልፈት ድረስ ስለእርሷ ብዙም የሚታወቅ ነገር አልነበረም።

የ32 ዓመቷ ወጣት ሰመሐል የተወለደችው አባቷ በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም የሚመራውን መንግሥት ለመጣል ህወሓትን በመምራት የሽምቅ ውጊያ በሚያደርጉበት ጊዜ ሱዳን ካርቱም ውስጥ ነበር።

ሰመሐል ከአባቷ ህልፈት በኋላ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመዘከር በሚካሄዱ እንቅስቃሴዎችና በፖለቲካዊ መድረኮች ላይ አልፎ አልፎ በመቅረብ ሃሰብ ስትሰነዝር ከመታየት ውጪ በፖለቲካው መድረክ ጎልቶ የታየ ተሳትፎ አልነበራትም።

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኘው የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት የሠሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ መንግሥት በህወሓት ኃይሎች ላይ ወታደራዊ ዘመቻ አካሂዶ የህወሓት አመራሮችን ከክልሉ የስልጣን መንበር ላይ ማስወገዱ ይታወሳል።

በትግራይ ክልል ውስጥ ለሦስት ሳምንታት ያህል ከተካሄደ ወታደራዊ ዘመቻ በኋላ ኅዳር 19/2013 ዓ.ም የፌደራል መከላከያ ሠራዊት የክልሉን ዋና ከተማ መቀለን ተቆጣጥሮ ይፈለጋሉ ያላቸውን ከፍተኛ የህወሓት አመራሮችን ለመያዝ ክትትል እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

ከዚህ በኋላም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ግጭቱን ተከትሎ በከተማዋ ተቋርጠው የነበሩ መሠረታዊ አገልግሎቶች ዳግም የጀመሩ ሲሆን፣ የከተማዋን ፀጥታም በማስከበር ረገድም የፌደራልና የመከላከያ ኃይል ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር በጥምረት እየሰሩ እንደሆነ የመቀለ ከተማ ከንቲባ አቶ አታኽልቲ ኃይለሥላሴ ለበቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል።

ምንጭ፦ BBC

Report Page