BBC

BBC

ገራዶ - Media

"የጥላቻና የሐሰተኛ መረጃ ረቂቅ ሕጉ የመናገር ነጻነትን አደጋ ላይ ይጥላል" - ሂይውመን ራይትስ ዎች

የኢትዮጵያ ሕግ አውጪዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ የተመራውን የጥላቻና ሐሰተኛ መረጃን የሚመለከተው ረቂቅ ሕግ ዳግመኛ በሚገባ እንዲያጤኑት ሲል ሂይውመን ራይትስ ዎች አሳሰበ።

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቆርቆሪው ድርጅት ሕጉ ከጸደቀ የመናገር ነጻነትን ይገድባል ሲል ያለውን ስጋት አስቀምጧል።

እኤአ ከ2018 አጋማሽ ጀምሮ ኢትዮጵያ በማህበራዊ መገናኛ ብዙኀን ላይ በሚለቀቁ ሐሰተኛና የጥላቻ መልዕክቶች የተነሳ በርካታ የብሔር ውጥረቶችና ግጭቶች ተከስተዋል ያለው መግለጫው መንግሥት ይህንን ተከትሎ ሕጉን ማስተዋወቁን ጠቅሷል።

ሂይውመን ራይትስ ዎች እኤአ በ2019 ሕዳር ወር በፌስ ቡክ ላይ በተለቀቀ መልዕክት የተነሳ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች በተደረገ ሰልፍና እርሱን ተከትሎ በተከሰተ ግጭት የ86 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ጠቅሶ መንግሥት ሕጉን ወደ ፓርላማ መርቶታል ብሏል።

"የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ የሚከሰቱ የብሔር ግጭቶች፣ አንዳንዴ በማህበራዊ መገናኛ ብዙኀን በሚሰራጩ የጥላቻ መልዕክቶች የተነሳ ለሚከሰቱት ግጭቶች ምላሽ ለመስጠት ከፍተኛ ግፊት ላይ ነው" ያሉት የድርጅቱ የአፍሪካ ተመራማሪ ላቲቲያ ባደር "ነገር ግን ይህ በአግባቡ ባልተጠና ሁኔታ የተረቀቀ ሕግ የመንግሥት ኃላፊዎች የመናገር ነጻነት መብትን ለመገደብ ሊጠቀሙበት ይችላሉ" በማለት ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

እንደ ሂይውመን ራይትስ ዎች ከሆነ የጥላቻ ንግግር ሕግ ያላቸው የዓለማችን ሀገራት ባለስልጣናት ለፖለቲካዊ ጥቅማቸው ሲሉ አለአግባብ ሲጠቀሙበት ይታያሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ሕግ ይልቅ ግጭትን፣ አለመረጋጋትንና ማገለልን የሚቀሰሰቅሱ ጥላቻ ንግግሮችን የሚከላከሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ ስልት መቀየስ አለበት ብሏል።

ከእነዚህም መካከል በጠቅላይ ሚኒስትሩ በየወቅቱ በሚተላለፍ መልዕክቶች እንዲሁም ሌሎች ታዋቂ ሰዎች ስለ ጥላቻ ንግግር አስከፊነት እንዲሁም ሌሎች የማህበረሰቡን እውቀት ከፍ የሚያደርጉ ሥራዎች መሰራት ይኖርባቸዋል ሲል ይመክራል።

መግለጫው አክሎም በረቂቅ ሕጉ ላይ የጥላቻ ንግግር ብያኔ የተበየነበት መንገድ በዓለም አቀፍ ህግ ላይ እንደተቀመጠው አለመሆኑን በመጥቀስ ይህም ለትርጉም ሰፊ መሆኑን ይገልጻል።

ረቂቅ ህጉ አሻሚ አገላለጾችን፣ ብያኔዎችን እንዲሁም አንቀጾችን መያዙን በማንሳትም ኢትዮጵያውያንና ዓለም አቀፍ የንግግር ነፃነት መብት ተሟጋቾች ያላቸውን ስጋት በማንሳት መተቸታቸውን ያስረዳል።

ለዚህም የተባበሩት መንግሥታት የንግግር ነጻነት ከፍተኛ ባለሙያ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት ያሉትን በማስታወስ ሕጉ የዓለም አቀፍ መስፈርቶችን የማያሟላ እና በጥላቻ ንግግር ላይ የተቀመጠው ብያኔ አሻሚ መሆኑን መጥቀሳቸውን ያስታውሳል።

"የኢትዮጵያ መንግሥት የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል በሥራ ላይ ያሉ በርካታ ሕጎች አሉት" ያሉት ባደር "የብሔር ግጭትን የሚያነሳሱትን በመኮነን፣ የመንግሥት ኃላፊዎች መቻቻልን የሚያበረታታ ውይይት በማድረግ መጀመር ይቻላል" ብሏል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህንን የጥላቻ እና ሐሰተኛ መረጃ ረቂቅ ሕግ ከማጽደቁ በፊት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ከሚገኘው ከሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ምክር ቤት ጋር፣ የኢትዯጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ኢትዮጵያውያን ድርጅቶች እንዲሁም በንግግር ነጻነት ባለሙያ ከሆኑ አካላት ጋር አብሮ ቢሰራ መልካም ነው ሲል ይመክራል።

በስተመጨረሻም "ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህ ረቂቅ ሕግ ተጨማሪ የጭቆና መሳሪያ እንዳይሆን ሚናውን ሊወጣ ይገባል" ብሏል።

(BBC)

Report Page