#BBC

#BBC

gerado media

መንግሥት አደገኛ የሆነውን የትግራይን መገለል መለስ ብሎ ሊያጤነው ይገባል! - ክራይስስ ግሩፕ

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ሽግግር ሃዲዱን እንዳይስት መንግሥት፣ የፖለቲካ አመራሮችና ዓለም አቀፍ አጋሮች አስፈላጊ ነገሮችን እንዲያደርጉ ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ዛሬ ባወጣው ሪፖርት ጠየቀ።

በዓለም ዙሪያ የሚከሰቱና ሊከሰቱ የሚችሉ ቀውሶችን የሚከታተለው ይህ ቡድን ኢትዮጵያን በተመለከተ ባወጣው ዘገባ ላይ በተለይ ከመጪው ምርጫ በፊት ሊደረጉ ይገባሉ ያላቸውን ነገሮች በዝርዝር አመልክቷል።

ሪፖርቱ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ለውጥ በአገር ውስጥና በውጪ ተስፋን የፈነጠቀ ቢሆንም አደገኛና ከፋፋይ ሁኔታንም ደቅኗል ይላል።

ቡድኑ እንዳለው በቅርቡ ጥቅምት ወር ላይ ኦሮሚያ ውስጥ የተቀሰቀስው ተቃውሞ የደም መፋሰስን ማስከተሉን ጠቅሶ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የተከሰቱ ግጭቶች በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞትና በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩት ደግሞ መፈናቀል ምክንያት መሆናቸውን አመልክቷል።

ሪፖርቱ አክሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ለሦስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በብቸኝነት አገሪቱን ሲመራ የነበረውን ኢህአዴግን ለመለወጥ የወሰዱት እርምጃ ያለውን መከፋፈል የበለጠ ሊያሰፋው እንደሚችል አመልክቷል።

ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩና አጋሮቻቸው እያካሄዱ ካለው የለውጥ እርምጃ አንጻር በኦሮሞ ቡድኖች መካከል እንዲሁም በአማራና በትግራይ ክልል አመራሮች መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ ጥረት ማድርግ እንዳለባቸው በመምከር፤ "ነገር ግን ውጥረቶቹ እየተባባሱ የሚሄዱ ከሆነ ይደረጋል የተባለው ምርጫ ማዘግየት ሊያስፈልግ እንደሚችል" ጠቁሟል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደስልጣን ከመጡ በኋላ የወሰዷቸው ተከታታይ የለውጥ እርምጃዎች በአገር ውስጥና በውጪ ትልቅ ተቀባይነትን እንዳስገኘላቸው የጠቀሰው የክራይስስ ግሩፕ ሪፖርት፣ ነገር ግን እርምጃዎቹ የነበረውን ሥርዓት በማስወገድ የመንግሥትን አቅም እንዳዳከመው ጠቅሷል።

ይህም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ ስልጣን ያመጣው ሕዝባዊ ተቃውሞን ያንቀሳቀሰው የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ "አዲስ ጉልበት እንዲያገኝ አድርጎታል" ይላል።

አክሎም በግንቦት ወር እንደሚካሄድ በሚጠበቀው ምርጫ እጩዎች ከየመጡበት የብሔር ቡድን ድምጽ ለማግኘት ፉክክር ስለሚያደርጉ ግጭቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ስጋቱን ገልጿል።

ክራይስስ ግሩፕ በሪፖርቱ በአገሪቱ ውስጥ በተለይ ስጋትን የሚፈጥሩ ያላቸውን አራት ሁኔታዎችን አመልክቷል።

የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጡበትን የኦሮሚያ ክልልን የሚመለከት ሲሆን ተቀናቃኞቻቸው እንዲሁም አንዳንድ የቀድሞ አጋሮቻቸው ሳይቀሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የክልሉን ጥቅም በማስከበር በኩል የበለጠ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ያምናሉ።

ሁለተኛው ተግዳሮት ደግሞ በኦሮሞና በአማራ ፖለቲከኞች መካከል በአዲስ አበባና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ያለው የተጽእኖ ፉክክር ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ ከአማራ ክልል ወደ ትግራይ ተካልለዋል በሚባሉ የድንበር አካባቢዎች ያለው የመረረ ውዝግብ እንዲሁም አራተኛው ያቋቋሙትና በበላይነት ሲመሩት የነበረው ሥርዓት እየፈረሰ ነው በማለት ቅሬታቸውን የሚያቀርቡት የትግራይ አመራሮች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ያላቸው ተቃውሞ ዋነኛ ፈተናዎች እንደሆኑ በሪፖርቱ ተመልክቷል።

ከዚህ በተጨማሪም በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ እየጨመረ የመጣው በአብያተ ክርስቲያናትና በመስጊዶች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት በእምነቶች መካከል ያለው ውጥረት እየጨመረ መምጣቱን ከመጠቆሙ ባሻገር አገሪቱ ባለባት ችግር ላይ ሌላ ፈተናን የሚጨምር ነው ብሏል ሪፖርቱ።

ሌላኛው የውጥረት ምንጭ ብሎ ሪፖርቱ ያስቀመጠው ጉዳይ ደግሞ አገሪቱ የምትከተለው የብሔር ፌደራላዊ ሥርዓት ጉዳይ ነው። ይህንን በሚደግፉና በሚቃወሙ ወገኖች መካከል ያለው ክርክር በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ "ዋነኛ የመፋለሚያ ምክንያት" መሆኑን ጠቅሷል።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት ግንባር ሌሎች አጋር ድርጅቶችን አካትቶ አንድ ወጥ አገር አቀፍ ፓርቲ ለመሆን ከወሰነ በኋላ ድጋፍና ተቃውሞ እንዳጋጠመው ሪፖርቱ ጠቅሶ፣ ውህደቱ ከላይ በኢህአዴግ የተያዘው የመንግሥት ቢሮክራሲ ውስጥ ተጨማሪ ውጥረት ሊፈጥር እንደሚችል ሪፖርቱ አመልክቷል።

እርምጃው የብሔር ፌደራሊዝምን ሊያስቀር ይችላል በሚል የትግራይ አመራሮችና የኦሮሞ ቡድኖች መቃወማቸው የሚታወስ ሲሆን ህወሓትም አዲሱን ፖርቲ እስካሁን ድረስ አልተቀላቀለም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉንም የሚያቀራርብ አስማሚ እርምጃዎች በመውሰድ አገሪቱን አንድ ለማድረግ ጥረት ቢያደርጉም ከባድ ተግዳሮቶች እንደገጠማቸው የክራይስስ ግሩፕ ሪፖርት ያመለክታል።

ኢትዮጵያ ውስጥ እየታየ ያለውን ውጥረት ለማርገብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግሥታቸውና ዓለም አቀፍ አጋሮች ሊወስዷቸው ይገባል ያላቸውን እርምጃዎች ሪፖርቱ ጠቁሟል።

በዚህም መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የአማራና የትግራይ አመራሮች ግንኙነታቸውን የሚያሻሸል ውይይት እንዲያደርጉ ግፊት ማድርግና በኦዲፒ ውስጥም ሆነ ከሌሎች የኦሮሞ ተቃዋሚ አባላት ጋር በመነጋገር ልዩነቶች ከኃይል ይልቅ በምርጫ ውጤት መፍትሄ እንደሚያገኙ መተማመን ላይ መድረስ ይጠበቅባቸዋል ሲል ይመክራል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራና በኦሮሞ አመራሮች መካከል የሚካሄዱ ውይይቶች እንዲቀጥሉ በማድረግ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች የሚስተዋሉ ውጥረቶችን ማርገብ ይጠበቅባቸዋል ይላል ሪፖርቱ።

መንግሥት ከትግራይ አንጻር እርቅ የሚያወርድ እርምጃን በመውሰድ ከቀድሞ ባለስልጣናት አንጻር የሚነሱ ክሶችን ተመልሰው እንዲያጤኑ ሊያደርግ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም ሽግግሩን ተከትሎ የተፈጠረውን አደገኛ የሆነውን የትግራይ መገለል መንግሥት ሊያጤነው ይገባል። የትግራይ አመራሮችም በበኩላቸው እንደማይቀበሉት ያሳወቁትን ከአማራ ክልል ጋር የሚወዛገቡበትን የይገባኛል ጥያቄዎች ለመመለስ የተቋቋመውን የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽንን በተመለከተ ውሳኔያቸውን መለስ ብለው ማስተካከል ይኖርባቸዋል ይላል ሪፖርቱ::

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩና አጋሮቻቸው ውህድ ፓርቲ በሚመስርቱበት ሂደት ውስጥ የብሔር ፌደራሊዝሙ ሊቀር ይችላል በሚል የተፈጠረውን ስጋት በጥንቃቄ ማስወገድ ይጠበቅባቸዋል የሚለው ክራይስስ ግሩፕ፣ በሕገ መንግሥቱ ላይ ማንኛውም አይነት ማሻሻያ የሚደረግ ከሆነ የሚመለከታቸው ወገኖች በሙሉ የሚሳተፉበት እንደሚሆን በግልጽ ማስቀመጥ ያስፈልጋል ብሏል።

ሪፖርቱ እንደሚለው ምርጫው በተያዘለት ጊዜ የሚካሄድ ከሆነ ቀደም ብሎ ቁልፍ ተቃዋሚ ኃይሎችንና ሲቪል ማህበራትን በማሳተፍ ከምርጫው በፊትና በኋላ ሊከሰቱ የሚችሉ ግጭቶችን ለማስወገድ ተከታታይ ውይይቶችን ማድረግ ያስፈልጋል።

ነገር ግን መከፋፈልና ግጭትን የሚያስከትል የምርጫ ዘመቻ የሚያይል ከሆነ መንግሥት ከዋነኛ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ድጋፍ በመጠየቅ ምርጫው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍና ብሔራዊ ውይይት እንዲካሄድ ሊጠይቅ ይችላል።

ሪፖርቱ ለኢትዮጵያ መንግሥት ካቀረበው ሃሳብ በተጨማሪ ለአገሪቱ ዓለም አቀፍ አጋሮችም ጥሪ አቅርቧል።

በዚህም መሰረት አጋሮች የሚይዙት አቋም በመሬት ላይ ያለውን አሳሳቢ ሁኔታን መሰረት ያደረገ መሆን አለበት ብሏል። ስለዚህም ለሽግግሩ በይፋ ድጋፋቸውን በመግለጽ በዝግ ደግሞ ሁሉም ወገኖች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማግባባት ይጥበቅባቸዋል ብሏል።

ከዚህ ባሻገርም በመጪዎቹ ወራት የፖለቲካውና የደህንነቱ ሁኔታ የማይረጋጋ ከሆነ ምርጫው እንዲዘገይ ሃሳብ ሊያቀርቡ ይችላሉ።

የውጪ አጋሮች የሚሰጡት ተከታታይ የገንዘብ ድጋፍ እስፈላጊነትን የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ የተዳከሙ ተቋማትን ለማጠናከር፣ የኢኮኖሚ መዋቅር ለውጥ ለማምጣት እንዲሁም በለውጡ ወቅት የሚከሰትን የወጣቱን ቅሬታና ተቃውሞ ለመቀነስ ይረዳል።

ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ለውጥ ለብዙዎች ተስፋን የሰጠ እንደሆነ የጠቀሰው ሪፖርቱ የሚታዩ ምልክቶች ግን ለቀድሞ ከፍተኛ ባለስልጣናት አሳሳቢ ናቸው ብሏል። የእንዳንዶች ስጋት የተጋነነ ቢሆንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጀመሩት የለውጥ ሂደት ላይ ጥንቃቄን በማከል ወሳኝ የሆኑ ደጋፊዎችን አሳትፈው መጓዝ እንደሚያስፈልጋቸው አመልክቷል።

በተጨማሪም ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለማሳተፍ የሚያደርጉትን ጥረት በማጠናከር፣ በሚወዛገቡ የክልል ልሂቃን መካከል ውይይቶች እንዲቀጥሉ በማድረግ፣ የገዢው ግንባር ውህደት አገሪቱን እንደማያናጋ የሚያረጋግጡ እርምጃዎችን መውሰድና ለአሁን በሕገ መንግሥቱና በብሔር ፌደራሊዝም ላይ የሚደረጉ መደበኛ ድርድሮችን ለሌላ ጊዜ ማቆየት እንደሚያስፈልግ የክራይስስ ግሩፕ ሪፖርት ይመክራል።

via BBC Amharic

@gashaw01 @geradomedia

Report Page