#BBC

#BBC


በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች በፌደራል ፖሊስ እንዲጠበቁ መወሰኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ለቢቢሲ ገልጿል።

በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ደቻሳ ጉርሙ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ዩኒቨርስቲዎች ወደ ሰላማዊ የመማር ማስተማር መመለስ የሚቻለው ጥበቃዎቹን ማጠናከር ሲቻል መሆኑ በመታመኑና ተቋማቱ የፌደራል ተቋማት በመሆናቸው በፌደራል ፖሊስ እንዲጠበቁ መወሰኑን ተናግረዋል።

አቶ ደቻሳ አክለውም "ከተማሪዎች ጋር በተደጋጋሚ በተደረገ ውይይት የቀረበው ቅሬታ የግቢው የጥበቃ አካላት ላይ መሆኑን በማንሳት በተጨማሪም ተማሪዎች የፌደራል ፖሊስ በገለልተኝነት እያገለገሉን ነው" በማለታቸው እዚህ ውሳኔ ላይ መደረሱን አብራርተዋል።

በትናንትናው ዕለት በወልዲያ ዩኒቨርስቲ ዛሬ ደግሞ በጎንደር ዩኒቨርስቲ ሁለት ተማሪዎች መሞታቸውን የየዩኒቨርስቲዎቹ አስተዳደሮች በፌስቡክ ገጻቸው ላይ አስታውቀዋል።

በወልዲያ ዩኒቨርስቲ የፔዳጎጂ ትምህርት ክፍል ተማሪ የነበረው አዲ ዋቆ የሞተው በወልዲያ ሆስፒታል በሕክምና ሲረዳ ከቆየ በኋላ እንደሆነም ታውቋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ጓደኞቹ እንደተናገሩት ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕለት አዲናን ጨምሮ ሌሎች ተማሪዎች በዩኒቨርስቲው የጥበቃ አካላት ድብደባ ደርሶባቸው እንደነበር ገልጸው ከዚህ ድብደባ በኋላ አዲ ወደ ሆስፒታል መወሰዱን ተናግረዋል።

በዛሬው ዕለት የጎንደር ዩኒቨርስቲ በፌስቡክ ገፁ ላይ እንዳሰፈረው ማሾ ዑመር የተባለ የእንስሳት ህክምና ተማሪ ትናንት ማታ ባልታወቁ ሰዎች በደረሰበት ጥቃት ጉዳት ደርሶበት ሆስፒታል ቢወሰድም ሊተርፍ አልቻለም።

ጉዳቱን በማድረስ የተጠረጠሩት ከሟቹ ዶርም ፊት ለፊት የሚገኙ ተማሪዎች ናቸው ያለው ዩኒቨርስቲው፣ ፖሊስ ምርመራ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን የምርመራ ውጤቱም እንደ ተጠናቀቀ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።

በአንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎች ዛቻ እንደሚደርስባቸው የማስፈራሪያ ወረቀቶችም እንደሚለጠፉ መረጃ እንዳላቸው አቶ ደቻሳ ጉርሙ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ለዚህም መፍትሔ ነው ያሉት የግቢዎቹ ጥበቃ እንዲጠናከር ማድረግ በመሆኑ በፌደራል ፖሊስ ይጠበቁ መባሉን አቶ ደቻሳ ተናግረዋል።

ተቋማቱን ወደ ሰላማዊ መማር ማስተማር ለመመለስ የዩኒቨርስቲዎቹ አስተዳደሮች የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው ያሉት አቶ ደቻሳ፣ ዩኒቨርስቲዎች የፌደራል ተቋማት ስለሆኑ ጥበቃዎቻቸውንና ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ለማጠናከር "በፌደራል ፖሊስ እንዲጠበቁ እያመቻቸን ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህ መቼ ይሆናል የሚለውን ሲያብራሩም ጠንከር ያለ የጥበቃ ሁኔታ እንዲኖር ፤ በሚቀጥለው አንድ ሳምንት ውስጥ ፌደራል ፖሊስ ይገባል ሲሉ አረጋግጠዋል።

በአማራም ሆነ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ባለው የደህንነት ሁኔታ፣ ስጋት የገባቸው ተማሪዎች ለቅቀው የሄዱ ተማሪዎች መኖራቸው ይታወቃል።

ይህንንም አስመልክተው ሲናገሩ፣ ከየክልሎቹ ጋር በመነጋገር፣ ትራንስፖርት አመቻችተው ለመመለስ ግብረ ኃይል አቋቁመው እየሰሩም እንደሆነ ተናግረዋል።

በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ በአንጻራዊነት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት አለ የሚሉት አቶ ደቻሳ፣ ክፍተት ሆኖ የሚታየው ለቅቀው የሄዱ ተማሪዎች ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ማካካሻ ትምህርት በመስጠት ያመለጣቸውን ለማስተማር ወደ መደበኛ የመማር ማስተማሩ ስርዓት እንዲገቡ ከክልሎች ጋር እየሰሩም መሆኑን አክለው ገልፀዋል።

አቶ ደቻሳ በመላው አገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች በፌደራል የጸጥታ አካላት የማጠናከር ስራ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

(BBC)

Report Page