#BBC

#BBC


በገብረ ጉራቻ ከተማ በታጣቂዎች በተከፈተ ተኩስ አራት የመንግሥት ጸጥታ አስከባሪ አባላት ላይ ጉዳት ደረሰ።

ትናንት (ሃሙስ) ምሽት 2፡30 ገደማ በሰሜን ሸዋ ዞን ኩዩ ወረዳ ገብረ ጉራቻ ከተማ የተፈጸመው ጥቃት ፖሊስ ጣቢያ ፊት ለፊት መሆኑን የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ደረጄ ደንደዓ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጥቃቱ የመንግሥት የጸጥታ አስከባሪ አካላትን ለመግደል ያለመ መሆኑን አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

የግድያ ሙከራው ኢላማ ከነበሩት መካከል የኩዩ ወረዳ ፖሊስ ኃላፊ ዋና ሳጅን አዱኛ ደቀባ እና አብረዋቸው የነበሩ ሌላ የወረዳው ፖሊስ አባል እንደሚገኙበት አስተዳዳሪው ይናገራሉ።

ጥቃቱ የተፈጸመው የፖሊስ አባላቱ እራት በልተው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ግቢ እየገቡ ሳለ እንደነበር የሚናገሩት የኩዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደረጄ፤ በፖሊስ አባላቱ ላይ በሁለት አቅጣጫ ተኩስ እንደተከፈተባቸው ያስረዳሉ።

"ዋና ሳጅን አዱኛ እግራቸውን ነው የተመቱት። አብሯቸው የነበረው የፖሊስ አባል ደግሞ እጁን ነው የተመታው" የሚሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ የተኩስ ድምጽ ሰምተው ወደ በስፍራው የተገኙ ሌሎች ሁለት የቀበሌ ሚሊሻዎች ላይም ተኩስ ተከፍቶ ጉዳት ደርሶባቸዋል" በማለት ትናንት ምሽት በገብረ ጉራቻ ከተማ የተፈጠረውን ክስተት ያስረዳሉ።

አቶ ደረጄ በአራቱም የጸጥታ አስከባሪ አካላት ላይ የደረሰው ጉዳት ለህይወት የሚያስጋ አለመሆኑን የተናገሩ ሲሆን፤ ሶስቱ እግራቸው ላይ አንዱ ደግሞ እጁ ላይ ጉዳት ማጋጠሙን አስረድተዋል።

"ሁለቱ በከተማችን በሚገኘው ሆስፒታል የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ሲሆን፤ ሁለቱ ደግሞ ለተጨማሪ ህክምና ወደ አዲስ አበባ ተልከዋል" ብለዋል።

በኩዩ ወረዳ ጸጥታ አከባሪዎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። የቀድሞ የወረዳው ፖሊስ ኃላፊ ጨምሮ ሁለት የፖሊስ አባላት ከወራት በፊት በታጣቂዎች በተተኮሰ ጥይት ተገድለዋል።

በተጨማሪም በወረዳው ቆላማ ቀበሌ ውስጥ ሁለት የቀበሌ ሚሊሻዎች ከሁለት ልጆቻቸው ጋር ተገድለው እንደነበር አስተዳዳሪው ያስታውሳሉ።

የኩዩ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ደረጄ ለዚህ ሁሉ ወንጀል ተጠያቂ የሚያደርጉት "በቀድሞ የኦነግ ጦር ስር የነበሩ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን" ነው።

ትናንት ጥቃት ያደረሱት ታጣቂዎች ተከታትሎ መያዝ አለመቻሉትን የተናገሩት አስተዳዳሪው ፖሊስ የግድያ ሙከራውን እየመረመረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

(BBC)

Report Page