#BBC

#BBC



የወላይታ ዞን በክልል የመደራጀት ጥያቄን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከሕዝብ ተወካዮች ጋር ለመነጋገር ነገ ማለዳ በጽህፈት ቤታቸው እንደጠሯቸው BBC ያነጋገርናቸው የተወካዮች አባላት አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የክልሉ ሕዝብ ተወካዮችን በዞኑ አስተዳደር በኩል ለስብሰባ እንደጠሯቸው ቢነገርም በምን ጉዳይ ላይ እንደሚወያዩ ግን የተገለፀ ነገር የለም።

አቶ አሸናፊ ከበደ የወላይታ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር የወጣቶች ክንፍ አመራር ሲሆኑ፤ በስብሰባው ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ካቀኑት አባላት መካከል ይገኙበታል።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ የወላይታ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄውን ካቀረበ ታሕሳስ 10 አንድ ዓመት የሚሆነው ሲሆን፣ ከዚያ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚሁ ዙሪያ ሊያነጋግሯቸው እንደጠሯቸው እንደሚገምት ተናግረዋል።

ጥያቄው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበው አርብ ዕለት መሆኑን በመግለጽም በዞኑ አመራሮች በኩል ጥሪው ደርሶናል ብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከዚህ በፊት ወደ ዞኑ በማምራት ከሕዝብ ተወካዮችና ከዞኑ አመራሮች ጋር በተወያዩበት ወቅት የክልል መሆን ጥያቄው መነሳቱን የሚያስታውሱት የሀገር ሽማግሌዎችን ወክለው ስብሰባው ላይ የሚገኙት አቶ ነጋ አንጎሬ በወቅቱ ከሕዝባችሁ ጋር ተወያዩ መባላቸውን በማንሳት፣ እነርሱ ግን ተወያይተው መጨረሳቸውን መናገራቸውን ያስታውሳሉ።

አቶ አሸናፊም በበኩላቸው ይህንኑ ስብሰባ በመጥቀስ ይህ የዘመናት የወላይታ ሕዝብ ጥያቄ የሚወሰንበትን ቀን አስታውቁ በተባልነው መሰረት አሳውቀናል ሲሉ ታሕሳስ 10፣ 2011 ዓ. ም. ጥያቄያቸውን ማቅረባቸውን ይናገራሉ።

አቶ ነጋ በበኩላቸው ክልሉ በኮማንድ ፖስት ስር መሆኑን በማስታወስ የወጣቶች ሕይወት ሳይቀጠፍና አካል ሳይጎዳ በመነጋገር የሚሆነውን ለመወሰን መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ለሚደረገው ስብሰባ ወደ አዲስ አበባ እያመሩ ያሉት እነማን መሆናቸውን ሲናገሩም፤ የሀይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የተቃዋሚ መሪ ተወካዮች፣ የክልሉን ወጣት አደረጃጀት የሚመሩ አካላትና የዞኑ አመራሮች እንደሚገኙበት አቶ ነጋም ሆኑ አቶ አሸናፊ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

አቶ አሸናፊ ታሕሳስ 10 የወላይታ ሕዝብ የክልልነት ጥያቄውን የሚያውጅበት መሆኑን በማስታወስ፣ "መንግሥት ሪፍረንደም የሚካሄድበትን ቀን የማያሳውቅ ከሆነ፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ የማይቀለበስ ቀን ነው" በማለት ለዚህም ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

(BBC)

Report Page