#BBC

#BBC


በኮንሶ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ በተከሰቱ ግጭቶች ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው እንደሚገኙ የዞኑ ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሀሰን ወላሎ ለቢቢሲ ተናገሩ።

በኮንሶ ዞን የሰገን ዙሪያ ወረዳ አካባቢ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ዳግም ባገረሸ ግጭት ምክንያት የሰዎች ህይወት ማለፉን፣ የቆሰሉ እና በሰገን ሆስፒታል ገብተው ሕክምና ያገኙ ሰዎች መኖራቸውን፣ ቤቶች ላይ ቃጠሎ መድረሱንም የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ከተማ ገለቦ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በዞኑ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በተቀሰቀሰ ግጭት በርካታ ነዋሪዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ያስረዳሉ።

ከዚህ ቀደም በአካባቢው 290 ቤቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን በአደጋ ስጋት ሥራ አመራር መለየቱን የሚገልፁት አቶ ከተማ፤ በአሁኑ ግጭት ምን ያህል ቤት እንደተቃጠለ ለማወቅ አልተቻለም ብለዋል።

በሰገን ወረዳ የሚገኙ እና ተደጋጋሚ ጥቃት እና የቤት ማቃተል የሚደርስባቸው ቀበሌዎች በማለትም ገርጬ፣ አዲስ ገበሬ፣ ሃይሎታ ዱካቱና መለጌ ዱጋያ ጠቅሰው በአሁኑ ሰዓትም ከሰገን ከተማ በተጨማሪ በእነዚህ ቀበሌዎች ላይ ጥቃት መድረሱን ይናገራሉ።

የኮንሶ ዞን ከሰገን አካባቢ ሕዝቦች ዞን ወጥቶ ለብቻው ከተደራጀ በኋላ የመዋቅርና አስተዳደር ጥያቄ አለን የሚሉ ወገኖች ጥቃቱን በመፈፀም እንደሚጠረጠሩም ጨምረው ይናገራሉ።

አቶ ዴርሻ ኦለታ የኮንሶ ዞን ኢንተርፕራይዝና ኢንደስትሪ ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ ሲሆኑ ወደ ሰገን ከተማ ለድጋፍና ክትትል ሥራ ከባልደረቦቻቸው ጋር ያመሩት ባለፈው ሳምንት እንደነበር ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በአሁኑ ሰዓት በሰገን ከተማ አስተዳደር ቅጽር ግቢ ውስጥ ወደ 400 የሚሆኑ ሰዎች መንገድ ተዘግቶባቸው ታግተው እንደሚገኙም ያስረዳሉ።

ረቡዕ ዕለት ከአካባቢው ለመውጣት ሙከራ ማድረጋቸውን ያስታወሱት ኃላፊው፤ ነገር ግን የፀጥታ ኃይሎች መኪና ተመትቶ አንድ የፖሊስ አባል በመሞቱ ምክንያት መንቀሳቀስ አለመቻላቸውን ይገልፃሉ።

እነዚህ 400 ሰዎች የሰገን ከተማ አስተዳደር ሠራተኞች፣ ተፈናቅለው ወደ አስተዳደሩ መጥተው የተጠለሉና አራት የዞኑ አስተዳደር ሠራተኞች መሆናቸውን ተናግረዋል።

የተፈናቀሉት ሰዎች ከሰገን ከተማ አዲስ ገበሬ እንዲሁም ሰገን ገነት ከሚባል መንደሮች ያለውን ግጭት ሸሽተው የመጡ መሆናቸውን ይገልጻሉ።

እነዚህ የተፈናቀሉ ሰዎች በአሁኑ ሰዓት በልዩ ኃይል ጥበቃ እየተደረገላቸው እንደሚገኙም ይገልፃሉ።

ውሎና አዳራችን ቢሯችን ውስጥ ነው

የሰገን ከተማ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ከተማ ገለቦም እርሳቸውም ሆኑ ሌሎች የወረዳው አስተዳዳሪዎች በደኅንነት ስጋት ምክንያት ከቢሯቸው ርቀው መሄድ እንደማይችሉ ይናገራሉ።

የኮንሶ ዞን ከሰገን አካባቢ ሕዝቦች ወጥቶ ከተደራጀ እና በአካባቢው የሰገን ወረዳን ካደራጀ በኋላ እስከ አሁን ድረስ ባለሙያዎችና አመራሮች ውሎና አዳራቸው በቢሯቸው ውስጥ መሆኑን ይናገራሉ።

"ከቢሮ 50 ሜትር ርቀው መሄድ አይችሉም" በማለት "ያለው ነገር ፈር የለቀቀ ይመስለኛል" ሲሉ ሁኔታውን ይገልጹታል።

እርሳቸውም ቢሆኑ ውሎ እና አዳራችን ቢሯቸ ውስጥ መሆኑን የተናገሩት አስተዳዳሪው "ቀን ቀን የተኛሁበትን ፍራሸ ከምቀመጥበት ወንበር ጀርባ በማቆም ነው ባለጉዳዮችን የማስተናግደው" በማለት የፀጥታ ስጋቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እና የትም ርቀው መሄድ እንደማይችሉ ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ግጭቱ በድጋሚ ሲያገረሽ የአካባቢ ሽማግሌዎች ላይ ጥቃት ተፈጽሞ ሰዎች መሞታቸውንም ይናገራሉ።

በአካባቢው የክልሉ ልዩ ኃይል፣ የፌደራል ፖሊሰ እንዲሁም የዞኑ ፖሊስ አባላት ቢኖሩም ጥቃቱ በቀጥታ እነሱም ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ መቆጣጠር ማስቸገሩን ገልፀዋል።

ነዋሪዎች ምን ይላሉ?

በግጭቱ አባታቸውን ያጡት አቶ ኡርማሌ ኡጋንዴ "አባቴን እንኳ አፈር ማልበስ አልቻልኩም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በግጭቱ ቅዳሜ ዕለት ዘጠኝ ሰዓት ላይ የሰገን ከተማ ላይ ነዋሪ የነበሩት የ58 ዓመት ጎልማሳ እና የ11 ልጆች አባት የሆኑት አቶ ኡጋንዴ አንጋሬ በጥይት ተመትተው ሕይወታቸው እንዳለፈ ልጃቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ኡርማሌ እንደሚሉት አባታቸው የቤተ ክርስትያን አገልጋይና የአገር ሽማግሌ የነበሩ ሲሆን በአካባቢው "ሰላምን የማይፈልጉ ኃይሎች እና 'የጉማይዴ ልዩ ወረዳ አስመላሽ' ነን የሚሉ ታጣቂዎ" አባታቸው ላይ ትኩረት አድርገው ጥቃቱን መፈፀማቸውን ገልፀዋል።

እነዚህ ታጣቂዎች አባታቸው ላይ ትኩረት ማድረግ የጀመሩት በመንግሥት አስታራቂ ሽማግሌ ተብለው ከተመረጡ በኋላ መሆኑንም ያስታውሳሉ።

አቶ ኡጋንዴ አንጋሬ በተገደሉበት ወቅት በቤታቸው እንደነበሩ የተናገሩት አቶ ኡርማሌ፣ ቤታቸው በጥይት ተደብድቦ፣ አብረዋቸው ከነበሩት ሰዎች መካከል አንድ ልጃቸው እግሯን በጥይት ተመትታ በሰገን ሆስፒታል መታከሟን ነግረውናል።

እናታቸው እና ሌሎች በቤት ውስጥ የነበሩ ሴቶች ግን በታጣቂዎች ታግተው መወሰዳቸውን እና ያሉበትን ቦታ እስካሁን እንደማያውቁ ገልፀዋል።

"ከዚህ በፊት እነዚህ ታጣቂዎች ሌሊት ሌሊት ተደብቀው በመምጣት ጥቃት ይፈፅሙ ነበር" የሚሉት ነዋሪዎቹ አሁን ግን በቀን ጥቃት መሰንዘር መጀመራቸውን ያስረዳሉ።

አቶ ኡርማሌ አባታቸው በሰላሙ ጊዜ ቢሆን መቀበር የነበረባቸው በአቅራቢያቸው በሚገኘው የመካነ ኢየሱስ ቅጽር ግቢ ውስጥ መሆኑን አስታውሰው፤ አሁን ግን በሰላም እጦት ምክንያት ካረፉ ከሦስት ቀናት በኋላ በአካባቢው አስተዳደር ግቢ ውስጥ መቀበራቸውን ገልፀዋል።

እርሳቸውም መንገድ ዝግ በመሆኑ ወደስፍራው ሄደው "አባታቸውን አፈር ማልበስ" አለመቻላቸውን ይናገራሉ።

በሃይሎታ ዱጋቱ የመገርሳ መንደር ነዋሪ የሆኑ እና ስማቸው ለደኅንነታቸው ሲባል እንዳይገለጽ የየጠየቁ ግለሰብ በበኩላቸው ከአካባቢያቸው ሴቶችና ህጻናት ሸሽተው ወደ ሌላ ስፍራ መሄዳቸውን ነግረውናል።

እርሳቸውም ማሳላይ የነበረ ጤፍ እና አንድ ቤታቸው ተቃጥሎ ከሌሎች የአካባቢው ወንዶች ጋር በመንደራቸው ተጨማሪ ጥቃት እንዳይፈፀም ለመከላከል መቅረታቸውን ይናገራሉ።

"የቻሉ ወደ ካራት ቀበሌ ያልቻሉ ደግሞ ሰላም ወደ ሆኑ ቀበሌዎች ሸሽተዋል" የሚሉት ግለሰቡ እንዲህ አይነት ጥቃት ኮንሶ ዞን ከተመሰረተ ለሦስተኛ ጊዜ እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።

"ከዚህ በፊት 2011 ዓ.ም ሚያዚያ ወር ላይ፣ 2012 ዓ.ም ነሐሴ ወር ላይ አሁን ደግሞ 2013 ኅዳር ወር ላጥ ጥቃት ደርሶብናል" በማለት የመንደራቸው ሊቀመንበርን ጨምሮ በርካቶች በታጣቂዎች መገደላቸውን ያስታውሳሉ።

የኮንሶ ዞን ኃላፊዎች ምን ይላሉ?

የኮንሶ ዞን ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ በዞኑ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳና ቀበሌዎች ላይ ታጣቂዎች የሚያደርሱት ጥቃት "ወረራ የሚመስል ነው" ሲሉ ይናገራሉ።

በርካታ መንደሮች በእሳት መጋየታቸውን፣ በመሳሪያ የታገዘ ጥቃት እንደሚደርስ እና የፀጥታ ኃይልን እየከበቡ ማጥቃት እንደሚፈጽሙ ይናገራሉ።

በዚህም የሰው ህይወት ማለፉን አካል ጉዳት መድረሱንና ለጊዜው ግምቱ ያልታወቀ ንብረት መውደሙን ይናገራሉ።

በዞኑ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የዞኑ፣ የፌደራልና የክልሉ ልዩ ኃይል ቢኖሩም ታጣቂዎቹ እነዚህን ፀጥታ አካላት በቀጥታ ኢላማ በማድረግ እንደሚያጠቁ ተናግረዋል።

እንደ ኃላፊው ከሆነ በዞኑ በተፈፀመ ጥቃትም ከ70 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል።

በአሁኑ ጊዜ የኮንሶ ዋና ከተማ በሆነችው ካራት ከተማ ጭምር የሚኖሩ ሰዎች ስጋት ላይ እንደሚገኙ በመናገር ያለውን ሁኔታ ለክልሉ ማሳወቃቸውን ገልፀዋል።

በኮንሶ ዞን የሰገን ዙሪያ አካባቢ በተደጋጋሚ ስለሚከሰተው ግጭት እንዲሁም ስለደረሰው የጉዳት መጠን ለማወቅ ለዞኑ ዋና እና ምክትል አስተዳዳሪዎች፣ ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ለሰላምና ፀጥታ እንዲሁም የብልጽግና ፓርቲ ኃላፊዎች በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ስልካቸውን ባለማንሳታቸው ምላሻቸውን ማካተት አልቻልንም።

የሰገን ሕዝቦች አስተዳደር ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ለረጅም ጊዜ የቆየ የወሰንና የአስተዳደር መዋቅር ጥያቄዎች ሲነሱ የነበረ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ በተደጋጋሚ በአካባቢው ባሉ ማኅበረሰቦች ዘንድ ግጭት ሲከሰት ቆይቷል።

በእነዚህ ግጭቶች ውስጥ የተደራጁና የታጠቁ ቡድኖች በሚፈጽሟቸው ጥቃቶችም በተለያዩ ጊዜያት በአከባቢው ባሉ ነዋሪዎች ህይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲደርስ ቆይቷል።

ሰሞኑን የተከሰተው ጥቃትም ከዚሁ ጋር የተያያዘ እንደሆነ የአካባቢው አስተዳዳሪዎችና ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ምንጭ፦ BBC

Report Page