#BBC

#BBC


ጠቅላይ ሚኒስትሩና የህወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በኢህአዴግ የውህደት ሂደት ላይ በተፈጠረው የአቋም ልዩነት ላይ መወያየታቸውን ለግንባሩ ቅርብ የሆኑ ምንጮቼ አረጋግጠውልኛል ሲል ለቢቢሲ ዘግቧል።

ቢቢሲ ዛሬ ማክሰኞ ከህወሓት ጽሕፈት ቤት አገኘሁት ያለው መረጃ እንደሚያመለክተው የግንባሩን ውህደት በተመለከተ የህወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር እሁድ ዕለት ያደረጉት ውይይት ውጤታማ ሳይሆን እንደቀረ ያመለክታል።

በውይይቱ ላይም በኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ቅዳሜ ዕለት ከተሳተፉት ስምንት አባላት መካከል አንደኛው በሥራ ጉዳይ ወደ መቀሌ በመሄዳቸው ምክንያት ሰባቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደረገው ውይይት ላይ እንደተሳተፉ ተነግሯል።

ምን ተወያዩ፤ ውጤቱስ?

ቢቢሲ ውይይቱን በተመለከተ ከህወሓት ጽህፈት ቤት ያገኘው መረጃ የህወሓት አባላት በጉዳዩ ላይ ደግመው እንዲያስቡበትና ከግንባሩ ጋር አብረው እንዲሰሩ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጥያቄ ቀርቦላቸው እንደነበረ ያመለክታል።

ይሁን እንጂ በቅዳሜው ስብሰባ ላይ የተሳተፉት የህወሓት ሥራ አሰፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ቀደም ሲል በውህደቱ ጉዳይ ላይ ከያዙት አቋም ውጪ የሚቀይሩት ነገር እንደሌለ በመግለጽ በውሳኔያቸው ስለጸኑ ውይይቱ የተጨበጠ ፍሬ ሳይገኝ ማብቃቱ ተገልጿል።

እስከ ትናንት [ሰኞ] ድረስ ለሦስት ቀናት የቀጠለው ኢህአዴግና የአጋር ድርጅቶቹ የግንባሩን ውህደት በተመለከተ ሲያካሂዱት የነበረውን ስብሰባ አጠናቀው ጉዳዩን ለድርጅቱ ምክር ቤት እንዲቀርብ መወሰናቸው ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድም በማህበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ እንዳሰፈሩት በሚዋሃደው ፓርቲ ሕገ ደንብ ላይ እንደተወያዩና እንዳጸደቁት ጠቅሰው ሰንወያይ "ወደ ምክር ቤቱ እንዲመራ ወስነናል" ብለዋል።

አክለውም "የሦስቱም ቀናት ውይይታችን ግልጽና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ተካሂዷል። ውይይቱ ይበልጥ አመራሮቹን ያቀራረበ ሆኖ በመጠናቀቁ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል" ሲሉ ውይይታቸው በመግባባት መጠናቀቁን ጠቅሰዋል።

ከዚህ በኋላ ህወሓት፣ ቀሪዎቹ የግንባሩ አባላትና አጋር ድርጅቶች በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በኩል ሂደቱ ስላለቀ በቀጣይ በሚካሄደው የኢህአዴግ ምክርቤት መድረክ በውህደቱ ላይ ሊወያዩ እንደሚችሉ ይጠበቃል።

ለረዥም ግዜ ሲመከረበትና ሲጠና የቆየው የኢህአዴግ የውህደት ጉዳይ ላይ ሌሎቹ የግንባሩ አባላትና አጋር ድርጅቶች የደገፉት ሲሆን፤ ህወሓት ግን በነበረው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፕሮግራም መቀጠል አለብን በማለቱ ነው ልዩነቱ የተፈጠረው።

ህወሓት ግንባሩን የማዋሃዱ ጥረት "አሃዳዊ ሥርዓት ለመፍጠር እና በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚደረግ መሆኑ ሲናገር" ውህደቱን የሚፈልጉት ደግሞ "ከለውጡ ጋር የሚሄድ አዲስ ፕሮግራም አስፈላጊ" መሆኑን ይጠቅሳል።

ጠቅላይ ሚኒስተር ዐብይ አህመድ እና ሌሎች የውህደቱ ደጋፊ የደርጅቶች አመራሮች በበኩላቸው ውህደቱ አሀዳዊ ሥርዓትን የማያመጣና ሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝሙን የሚያስቀጥል እንደሚሆን በመጥቀስ የውህደቱ ጠቀሜታ ይጠቅሳሉ።

ቢቢሲ የኢህአዴግ ሊቀመንበር በሆኑት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድና በህወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት መካከል የነበረውን ውይይት በተመለከተ መረጃ ለማግኘት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤትን ብጠይቅም ጉዳዩ የግንባሩ ጽህፈት ቤት መሆኑ ተገልጾልኛል ብሏል። ከኢህአዴግ ጽህፈት ቤት መረጃ ለማግኘት ያደረኩትም ሙከራ አልተሳካልንም ሲል ገልጿል።

(BBC)

Report Page