BBC

BBC



በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሉ መካከል ግጭት ከተከሰተ ዛሬ ሰባተኛ ቀኑን አስቆጥሯል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የትግራይ ልዩ ኃይል በክልሉ በሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት የሠሜን እዝ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን በመጥቀስ ወታደራዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ ማዘዛቸው ይታወሳል።
የክልሉ መንግሥት በበኩሉ ጦርነቱን የከፈተብን የፌደራሉ መንግሥት ነው ይላል።
ለመሆኑ ዕለታዊ ሕይወት በጦርነት ቀጠና ውስጥ ምን ይመስላል? ሪፖርተራችን ከስፍራው የሚከተለውን ዘገባ ልኮልናል።
የስልክ እና ኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ ፦
ማክሰኞ ጥቅምት 24 ምሽት ላይ ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ በመቀለ ከተማ ተሰማ። ከዚያም ብዙም ሳይቆይ የስልክ እና ኢንተርኔት አገልግሎቶች ተቋረጡ።
ነዋሪዎች በክልሉ እና ከክልሉ ውጪ ካሉ ዘመድ ወዳጆቻቸው ጋር የነበራቸው ግንኙነት ሙሉ በሙሉ መቋረጡን ይናገራሉ።
መምህሯ ንግሥቲ አበራ አራት ልጆች እንዳሏት ትናገራለች። አራቱም ልጆቿ ኑሯቸው በአዲስ አበባ ነው። ስለ ልጆቿ ትጨነቃለች። "ላለፉት ሦስት ቀናት መብላትም መተኛትም አቃተኝ። ልጆቼን ድምጽ ከሰማሁ ቆየሁ" ብላለች ለቢቢሲ።
ኤሌክትሪክ ፦
ጦርነቱ እንደተጀመረ፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ ተቋርጦ ነበር።
ይሁን እንጂ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ከሁለት ቀናት በኋላ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲመለስ ተደርጓል። ይሁን እንጂ በመቀለ ከተማ በተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ እያጋጠመ እንደሆነ ሪፖርተራችን አስተውሏል።
ትግራይን የሚያስተዳድረው ህወሓት የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲቋረጥ ያደረገው የፌደራል መንግሥቱ ነው ይላል። ጠቅላይ ሚንስትሩ በበኩላቸው የአሌክትሪክ አገልግሎቱ እንዲቋረጥ ያደረገው የህወሓት ኃይል መሆኑን ተናግረዋል።

የውሃ ችግር ፦
ወትሮም የመጠጥ ውሃ ችግር የነበረባት የመቀለ ከተማ አሁን ችግሩ በርትቷል። ከዚህ ቀደም በተንቀሳቃሽ ቦቴ መኪናዎች እና በሌሎች ዘዴዎች ውሃ ያገኙ የነበሩ ነዋሪዎቸ አሁን ላይ የግንኙት መስመሮች በመቋረጣቸው ውሃ ለማግኘት መቸገራቸው ይናገራሉ።

በመቀለ ከተማ በስልክ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው ውሃ ያቀርቡ የነበሩ ድርጅቶች አሉ። በአሁኑ ወቅት ግን የስልክ ግንኙነት ባለመኖሩ ውሃ በትዕዛዝ ማግኘት ከባድ ነው ሲል ሪፖርተራችን ይናገራል።

በሳምንት አንድ ጊዜ ትመጣ የነበረው የቧንቧ ውሃ ሳትመጣ መቅረቷ ችግሩን አባብሶታል ይላል ሪፖርተራችን።
በመቀለ ከተማ በተለያዩ ስፍራዎች ውሃ ማከፋፈያ ስፍራዎች አሉ። ከእነዚህ ማከፋፈያ ስፍራዎች በአሌክትሪክ ኃይል ተስበው በውሃ መጫኛ ቦቴዎች ነበር የሚጓጓዙት።
በአሁኑ ወቅት የአሌክትሪክ አገልግሎት በመቋረጡ የውሃ እደላ የማካሄድ ሥራውን ከባድ ማድረጉን ባልደረባችን ይናገራል።

የባንኮች መዘጋት ፦

ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጀምሮ የግል እና የመንግሥት ባንኮች በትግራይ ሙሉ በሙሉ ዝግ ናቸው።
ከሁለት ቀናት በፊት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በትግራይ የሚገኙ ሁሉም ባንኮች የደኅንነት ስጋት ስላለባቸው በክልሉ የሚገኙ ሁሉም የባንክ ቅርንጫፎች እንዲዘጉ ወስኗል።

በክልሉ ነዋሪዎች ላይ አስቸጋሪው ኩነት የባንኮች አገልግሎት መቋረጥ መሆኑን ሪፖርተራችን ይናገራል።
የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ንግሥቲ መለስ በባንክ ያላትን ገንዘብ ወጪ ማድረግ ባለመቻሏ ችግር ላይ መሆኗን ትናገራለች።

ወ/ት ዓለምነሽ ገብረሥላሴ በጉሊት ገበያ የችርቻሮ ንግድ ላይ ተሰማርታ ነው ህይወቷን የምትመራው። ወ/ት ዓለምነሽ ገዢ ጠፍቷል ትላለች። "ሰዎች እየገዙ አይደለም፤ እኔም ገቢ እያገኘሁ ስላልሆነ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው የምገኘው" ብላለች።

ባንኮች ከመዘጋታቸው አንድ ቀን በፊት፣ የጥሬ ገንዘብ እጥረት በገበያ ውስጥ መታየቱን ሪፖርተራችን ዘግቧል። የባንኮች መዘጋት እና የጥሬ ገንዘብ እጥረት ነዋሪዎች ወደ ገበያ ወጥተው መሠረታዊ ፍጆታዎችን እንዳይሸምቱ ጋሬጣ እንደሆነባቸው ይናገራሉ።

የትራንስፖርት አገልግሎት ፦
ጦርነቱ እንደተጀመረ ማክሰኞ ጥቅምት 24 የትግራይ ክልል መንግሥት ባወጣው የመጀመሪያው መግለጫ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋረጥ መወሰኑን ይፋ አድርጎ ነበር።

ይህ እግድ ለሁለት ቀናት ከዘለቀ በኋላ፤ ከመኖሪያ ቀያቸው ርቀው የነበሩ ሰዎች ከትግራይ ፖሊስ ኮሚሽን ልዩ ፍቃድ እየተቀበሉ ወደ መኖሪያቸው መመለሳቸውን ሪፖርተራችን ተመልክቷል።

ይህ ልዩ ፍቃድ የሌለው ወይም ማግኘት የማይችል የክልሉ ነዋሪ ግን ወደ የትኛው የክልሉ ስፍራ መንቀሳቀስ አይችልም።

ክልሉ ከሌሎች አጎራባች ክልሎች ጋር በሚዋሰንባቸው ድንበሮች ዙርያ ወታደሮች ስለሰፈሩ ከትግራይ ወደ አዲስ አበባና ወደሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች መጓዝ የማይታሰብ ሆኗል።

የአየር ድብደባ ስጋት ፦
ሐሙስ ጥቅምት 26 ከሰዓት ላይ አንድ ተዋጊ ጄት በመቀለ ዙርያ በራ ነበር። ይህም ነዋሪዎችን በከፍተኛ ሁኔታ አስደንግጦ እንደነበረ ዘጋቢያችን ለመታዘብ ችሏል።
ምሽቱን የክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ይህ የጦር ጄት ቦምብ እንደጣለና ሰዎች ላይ ግን ጉዳት እንዳልደረሰ ገለጧል። ይህ ግን በሪፖርተራችንም ይሁን በገለልተኛ አካል አልተረጋገጠም።

ባሳለፍነው እሑድ ወደ ቤተ-ክርስቲያን ሲሄዱ የነበሩ ሰዎች የጦር ጄት ድምጽ ሲሰሙ በፍጥነት ተሯሩጠው ሲበተኑም ተመልክቷል።

በዚያው ዕለት ምሽት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለትግራይ ሕዝብ በከተሞች አከባቢ እና በተለያዩ ወታደራዊ ጥቃት ሊያጋጥማቸው በሚችሉ ስፍራዎች በብዛት ሆነው ከመንቀሳቀስ እንዲቆጠቡ ጥሪ አስተላለፉ።
ይህም ተጨማሪ የአየር ድብደባ እንደሚኖር ያመላከተ ነበር።

ጥቅምት 29 እሑድ ምሽት ላይ የፌደራል መንግሥቱን የጦር ጄት መትተን ጥለናል ሲሉ የሕውሃት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገረው ነበር።

የአገር መከላከያ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሜጀር ጀነራል መሐመድ ተሰማ ግን ይህ የሐሰት ዜና ነው ሲሉ ትናንት ጥቅምት 30 ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

የነዳጅ እጥረት ፦
በመቀለ የሚገኘው ሪፖርተራችን ግጭቱን ተከትሎ በትግራይ በተለይም በክልሉ መዲና የነበረው የንግድ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ይናገራል።
የንግድ ብቻ ሳይሆን የትራፊክ እንቅሴውም ቀንሷል ይላል። ለዚህ ደግሞ ከምክንያቶች አንዱ በክልሉ የነዳጅ እጥረት በመከተሱ ነው።

አቶ ሐለፎም ተክላይ መኪናቸውን ሙሉ በሙሉ ለማቆም መገደዳቸውን ይናገራሉ። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያታቸው የነዳጅ እጥረት እንደሆነ ይናገራሉ።

የክልሉ መንግሥት ምን ይላል?

ከፌዴራልም ሆነ ከክልሉ መንግሥት በትግራይ እየተከሰቱ ባሉ ሁኔታዎች ዙርያ በቂ የሚባል ማብራሪያ የክልሉ ሕዝብ ማግኘት እንዳልቻለ ሪፖርተራችን ይናገራል።

የክልሉ ሕዝብ ግራ መጋባትና ስጋት ውስጥ ባለበት ሁኔታ ወሳኝ የሚባሉ መረጃዎች ከመንግሥት አካላት አያገኘ ነው ለማለት አያስደፍርም ይላል ዘጋቢያችን።

የትግራይ ክልል የሕዝብ ግንኙት ቢሮ አሁን ያሉት ችግሮች 'በአጭር ጊዜ ውስጥ ይፈታሉ' ከሚል አጭር መልስ ውጪ ተጨማሪ ማብራሪያ ሊሰጥ አልቻለም።

የነዋሪዎቹ ጥያቄዎቹ "ወደ የት እየተኬደ ነው? ይህ ሁሉ መጥፎ ሁኔታስ መቼ ነው የሚያበቃው?" የሚሉት ጥያቄዎችን እያነሱ መሆኑን ሪፖርተራችን ይናገራል።
የከተማዋ ነዋሪም የጦርነትን አስከፊነት በተደጋጋሚ ይናገራል። ነዋሪዎች ግጭቱ በቶሎ የሚፈታበትን ሁኔታና ዕድል እንዲፈጠር በጉጉት እየጠበቁ ይገኛሉ ይላል ባልደራባችን።

አንዴት እዚህ ነገር ውስጥ ተገባ?

በህወሓት እና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል ልዩነቶች እየሰፉ የመጡት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ያካሄዱትን የለውጥ እርምጃ ተከትሎ ነው።

ኢሕአዴግ ከስሞ ወደ ብልጽግና ፓርቲ መቀየሩ እንዲሁም የፌደራል መንግሥት በኮሮናቫይረስ ስጋት ያሸጋገረው አገራዊ ምርጫን ወደ ጎን በመተው የትግራይ ክልል ክልላዊ ምርጫ ማካሄዱ በሁለቱ አካላት መካከል ከፍተኛ መቃቃር እንዲፈጠር ምክንያት እንደሆኑ ይነገራል።

የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል የተካሄደውን ምርጫ ሕገ-ወጥ ነው ሲለው ሕውሃት በበኩሉ የጠቅላይ ሚንስትሩ መንግሥት የሥራ ዘመን አብቅቶለታል ሲል ነበር።

ነገሮች ተባብሰው ጥቅምት 24 ላይ የትግራይ ልዩ ኃይል፣ በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ የአገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን በመጥቀስ ጠቅላይ ሚንስትሩ የአገር መከላከያ ሠራዊት ሕውሃት ላይ እርምጃ እንዲወስድ ማዝመታቸውን ተናግረዋል።
ምንጭ፦ BBC

Report Page