#BBC

#BBC


ዓለም አቀፉ ክራይሲስ ግሩፕ በትግራይ ክልል እና በፌደራል መንግሥት መካከል ያለው ውጥረት አይሎ ወደ ግጭት ሊሸጋገር ይችላል አለ።

ቡድኑ በሁለቱ አካላት መካከል ያለው አለመግባባት ተባብሶ ወዳልተፈለገ ደረጃ ከመድረሱ በፊት መፍትሄ ይሆናሉ ያላቸውን አማራጮች ሰንዝሯል።

በመፍትሔ ሐሳብነት በዋነኛነት የተቀመጠው የፌደራል መንግሥትም ሆነ የትግራይ ክልል መንግሥት ያስቀመጧቸውን ቅድመ ሁኔታዎች አለዝበው ለድርድር መቅረብ እንዳለባቸው ነው።

የበጀት ጉዳይ

ክራይሲስ ግሩፕ የፌደራል መንግሥት በሚቀጥለው ሳምንት ለክልሎች በጀት ማከፋፈል የሚጀመርበት ወቅት እንደሆነ ይጠቅሳል።

ይሁን እንጂ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን ተከትሎ የፌደራል መንግሥት ለትግራይ ክልል የበላይ አካል በጀት አልሰጥም ማለቱን በማስታወስ፤ ይህ በሁለቱ አካላት መካከል ያለውን ውጥረት ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ይገልጻል።

የፌደራል መንግሥት ለትግራይ ክልል የሚውለው በጀት እንደከዚህ ቀደሙ ለክልሉ በቀጥታ ሳይሆን በወረዳ እና በከተማ ደረጃ ላሉ የመንግሥት እርከኖች በጀቱ ይተላለፋል ማለቱ ይታወሳል።

የትግራይ መንግሥትም ለዚሁ ምላሽ በሰጠበት ወቅት ይህ የፌደራል መንግሥት አካሄድ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው፤ "ጦርነት የማወጅ ያክል ነው" ማለቱ ይታወሳል።

መፍትሔው ምንድነው?

ሁለቱም አካላት ልዩነቶቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ይኖርባቸዋል ይላል ክራይሲስ ግሩፕ።

ይሁን እንጂ እንደ ክራይሲስ ግሩፕ ከሆነ፤ ሁለቱ አካላት በጠረጴዛ ዙሪያ ለመነጋገር ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠዋል።

ህወሓት ምን ይላል?

እንደ ክራይሲስ ግሩፕ ከሆነ፤ የትግራይ ክልልን እየመራ ያለው ህወሓት፤ ከፌደራል መንግሥት ጋር ለመደራደር ካስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል ጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ አሕመድ የማይመሩት የሽግግር መንግሥት መቋቋም አለበት የሚለው ይገኝበታል።

ህወሓት፤ ይህ የሽግግር መንግሥት ምርጫውን በበላይነት መከታተል ይኖርበታል የሚል አቋም ይዟል። ከዚህ በተጨማሪም በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተፈተው የድርድሩ አካል መሆን አለባቸው ይላል።

ህወሓት በትግራይ ሌላ ክልላዊ ምርጫ አይደረግም የሚል አቋም ይዟል ይላል ክራይሲስ ግሩፕ በሪፖርቱ።

ከዚህ በተጨማሪም የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ ገብተዋል ሲሉ ይከሳሉ።

ክራይሲስ ግሩፕ፤ ህወሓት ወደ ድርድር ለመምጣት ያስቀመጣቸውን ቅድመ ሁኔታዎችን ማለሳለስ ይኖርበታል ይላል።

የፌደራል መንግሥት ምን ይላል?

ክራይሲስ ግሩፕ፤ የፌደራል መንግሥት ህወሓት ያስቀመጠውን ቅድመ ሁኔታዎች ተቀብሎ ወደ ውይይት የሚመጣበት እድል አነስተኛ ነው ይላል።

በተቃራኒው የብልጽግና ፓርቲ ባለስልጣናት በቅድሚያ ህወሓት ያካሄደው ክልላዊ ምርጫ ሕጋዊነት የሌለው እንደሆነ አምኖ መቀበል አለበት ይላሉ።

የፌደራል መንግሥት ለውይይቱ አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር በቅድሚያ በጀት ላይ የጣለውን ክልከላ ማንሳት አለበት ይላል።

ፌዴሬሽን ምክር ቤት ለክልሉ የሚሰጠውን በጀት በተመለከተ ያስተላለፈውን ውሳኔ የፌደራል መንግሥቱ በጊዜያዊነት ቢያቆም መልካም ነውም ይላል።

ይህም ለድርድር የሚሆን ጊዜ ሊያስገኝ እንደሚችል ቡድኑ ይጠቁማል።

ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ምን ይጠበቃል?

ክራይሲስ ግሩፕ፤ ዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ኢትዮጵያ የገባችበት አጣብቂኝ እንዳይባባስ ከፈለጉ ብሔራዊ መግባባት ላይ እንዲደረስ የበኩላቸውን ሚና መወጣት ይኖርባቸዋል ይላል።

የአሜሪካ መንግሥት እና የአውሮፓ ሕብረት የፌደራል መንግሥት ከትግራይ መንግሥት ጋር ወደ ውይይት እንዲመጣ ጫና መፍጠር አለባቸው ይላል።

የትግራይ ክልልም የፌደራል መንግሥት እንደ ትንኮሳ የሚመለከተውን መግለጫ ማውጣት እንዲያቆም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና ማሳደር ይኖርበታል።

ለኢትዮጵያ ቅርብ የሆኑት ቻይና እና የባህረ ሰላጤው አገራትም ሁለቱ አካላት ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ እንዲመጡ ጫና መፍጠር አለባቸው።

በሁለቱ አካላት ዘንድ ተሰሚነት ያላቸው የአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ሊቀ መንበር የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ ወደ ድርድር እንዲመለሱ ጥረት ማድረግ አለባቸው ብሏል።

ክራይሲስ ግሩፕ፤ ችግሮቹ መፍትሄ የማያገኙ ከሆነ በአፍሪካ በሕዝብ ቁጥር ሁለተኛ በሆነችው አገር ጦርነት ተከስቶ ቀውስ ሊከሰት ይችላል ብሏል።

ምንጭ፦ BBC

Report Page