#BBC

#BBC


የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የክስ መዝገብ ሥር ንብረታቸው እንዳይንቀሳቀስ የተደረገባቸው ተከሳሾች ጉዳይን ዛሬ ተመልክቷል።

ከእነ አቶ ጃዋር ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት ቶኩማ ዳባ (ዶ/ር) በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሠረት ንብረታቸው እንዳይንቀሳቀስ የተደረገባቸው ተከሳሾች ዝርዝር ወጪያቸው ምን ያክል እንደሆነ በጽሑፍ ለፍርድ ቤት ማቅረባቸውን ይናገራሉ።

ተከሳሾች ለቀለብ፣ የቤት ኪራይ እና የባንክ እዳ ለመክፈል እና ሌሎች ወጪዎቻቸውን ለመሸፈን እንዲቻላቸው እግድ እንዲነሳላቸው ጠይቀዋል።

የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ንብረት ላይ የተጣለው እግድም እንዲነሳ ጥያቄ አቅርበዋል።

አቃቤ ሕግ ግን ጠበቆቹ ያቀረቡት የወጪ ዝርዝር በማስረጃ የተደገፈ አይደለም፤ የኦኤምኤን ንብረትም መመለስ የለበትም ሲል ተከራክሯል።

ተከሳሾች ምን አሉ?

ፖለቲከኛው ጃዋር መሐመድ "ከእኔ ጋር ለአንድ ቀን ሻይ የጠጡ ሰዎች የባንክ ሂሳባቸው ታግዷል፤ ብዙ ነገር አብሬ የሰራሁት የመንግሥት ባለስልጣናት ግን የባንክ ሂሳባቸው አልተዘጋባቸውም" ሲሉ ዛሬ ለፍርድ ቤቱ መናገራቸውን ጠበቃው ይናገራሉ።

አቶ ጃዋር መሐመድ ከመኖሪያ ቤታቸው የተወሰደው ንብረት ስርዓትን ተከትሎ ተመዝግቦ የተወሰደ ሳይሆን ዘረፋ ነው የተፈጸመብኝ ሲሉም ተናግረዋል።

"መኖሪያ ቤቴ ውስጥ ከ100ሺህ ብር በላይ፣ ወርቅ፣ የእጅ ሰዓት እና በሽልማት ያገኘኋቸው የተለያዩ ሜዳሊያዎች ፖሊስ ወስዶ የራሱ ንብረት አድርጎታል። ለምንድነው የምዘረፈው" ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ጃዋር መሐመድ "ከእኔ ጋር ለአንድ ቀን ሻይ የጠጡ ሰዎች የባንክ ሂሳባቸው ታግዷል፤ አሁን ስልጣን ላይ ካሉ ባለስልጣናት ጋር ግን አብሮ ሻይ መጠጣት ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ ነገር አብሬያቸሁ ሰርቻለሁ። እግዱ እውነተኛ ከሆነ ለምን የእነሱ የባንክ ሂሳብ አልታገደም?" በማለት ፍርድ ቤቱን መጠየቃቸውን ጠበቃው ቶኩማ ዳባ (ዶ/ር) ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ በቀለ ገርባ በበኩላቸው ተሸከርካሪን ጨምሮ ንብረታቸው ላይ የተላለፈው እግድ ከሕግ ውጪ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት እግዱ እንዲነሳላቸው ጠይቀዋል።

"እኔ ለ37 ዓመታት የመንግሥት ሰራተኛ ሆኜ የሰራሁ ሰው ነኝ። ይህን ያክል ዓመት የሰራ ሰው እንዴት አሮጌ መኪና ይኖረዋል ማለት ትክክል አይደለም። ወደ አዳማ እና ነቀምቴ በሄድኩ ጊዜ ሕዝቡ ምን ዓይነት አቀባበል እንዳደረገልኝ ታውቃላችሁ። ወደ ውጪ በሄድኩ ጊዜም መኪና ተሸልሜ ነበር። ይህችን አሮጌ መኪና ንብረት አፈራ ተብሎ ማገዱ ትክክል አይደለም" ብለዋል።

አቶ በቀለ የታገደው ተሽከርካሪ ከተከሰሱት ወንጀል ጋር ግንኙነት እንደሌለው እና የባንክ ሂሳባቸው እንዲታገድ የተደረገው ቤተሰባቸውን ለችግር እንዲጋለጥ እና እርሳቸው ለማዳከም እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቱም በጉዳዩ ላይ የአቃቤ ሕግ ምላሽን ለመስማት ለጥቅምት 24 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ምንጭ፦ BBC


Report Page