#BBC

#BBC


የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ፅህፈት ቤት በክልል ደረጃ መዋቀር አለበት በሚልና ሌሎች ጥያቄዎች ምክንያት አለመግባባት ውስጥ የነበሩት የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ፅህፈት ቤት አደራጅ ኮሚቴና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ እርቅ ላይ መሆናቸው ተገልጿል።

የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ፅህፈት ቤት አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ቀሲስ በላይ መኮንንም ለቢቢሲ እንደገለፁት ለመታረቅ መንገድ መጀመራቸውን ነው።

ይህንንም በዋነኝነት እየመሩ ያሉት የኦሮሚያ ቤተ ክርስቲያን እንዲደራጅ ሲኖዶሱን ሲጠይቁ የነበሩ የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋዮች እንዲሁም ለእምነቱ ቀናኢ የሆኑ በመንግሥትም ሆነ በግል ስራ የተሰማሩ ኃላፊዎች የተውጣጣ ኮሚቴ ፈቃደኝነታቸውን እንደጠየቁና መስማማታቸውንም ቀሲስ በላይ ይናገራሉ።

የሚስማሙባቸውን ዝርዝር ነጥቦች አስቀምጠው ለቋሚ ሲኖዶሱ ያስገቡ ሲሆን፤ ቋሚ ሲኖዶሱም ተቀብሎ ለምልዓተ ጉባኤው አቅርቦታል።

ምልዓተ ጉባኤውም ይወስናል የሚል እምነት አላቸው። ዝርዝር ሁኔታውን ምልዓተ ጉባኤው ከወሰነ በኋላ እንደሚገልፁም አስረድተዋል።

ሆኖም በአንዳንድ ሁኔታዎች "እከሌ ተንበረከከ፤ አንበረከከው" የሚሉ ነገሮች መነሳታቸውን ጠቅሰው ተገቢ አይደለም ብለዋል።

ቀሲስ በላይ "ይቅርታ ጠየቀ፤ ይቅርታ አስጠየቀው የሚባል ነገር የለም። በቤተ ክርስቲያናችን እሱ አይደለም ፍትሃ ነገስታችን የሚያዘው፤ የቤተ ክርስቲያን አሸናፊነት ነው። በእርቅ ውስጥ ሁሉም አሸናፊ ነው። አንዱ ተሸንፎ፤ አንዱ ይቅርታ ጠይቆ፣ አንዱ ይቅርታ አስጠይቆ አይደለም።"

ካሉ በኋላ "የኛና የአባቶች ፍላጎት አንድ ሆኗል። እሱም ምንድን ነው የመጨረሻ መቋጫው ቤተ ክርስቲያን የምትስፋፋበት፣ የምትጠናከርበት የኦሮሞ ህዝብም ከቤተ ክርስቲያን የሚፈልገው፤ በቤተ ክርስቲያን ያለው ድርሻ ከፍ ያለና እንዲሁም የሚደሰትበት። እንደፈለገው የኔ ናት ብሎ ቋንቋው ባህሉ የሚከበርበት ቤተ ክርስቲያን እንድትሆን የቤተክርስቲያን አባቶችም የኛም ፍላጎት ነው" ብለዋል።

የአዲስ አበባ ኃገረ ስብከት የህዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ መላከህይወት አባ ወልደየሱስ ሰይፉ በበኩላቸውም አንዳንድ የሃይማኖቱ አባቶች ለማስታረቅ እየሞከሩ እንደሆነ ገልፀዋል።

ሊቃነ ጳጳሳቶቹ ቀሲስ በላይ ይቅርታ መጠየቅ ስለሚፈልጉ ይቅርታ ተደርጎላቸው ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ገብተው አገልግሎቱን መስጠት ቢችሉ የሚል ሃሳብ መያዛቸውንም መላከ ህይወት ይናገራሉ።

" ሲኖዶሱ እንደ ሃሳብ ነው እንጂ የያዘው፤ ተግባራዊ የሆነ ነገር የለም። ማንም ሰው እንዲጠፋ አንፈልግም፤ ተመልሶ የቤተ ክርሰቲያን ደንብና ህግ ጠብቄ እኖራለሁ ካለ ቅሬታ የለንም" ብለዋል።

ቀሲስ በላይ ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች የኦሮሞ ህዝብ በቋንቋው መማር፣ በኦሮምኛ ቅዳሴን ጨምሮ አገልግሎት መስጠት መላከ ሕይወትም ሆኑ ቤተ ክርስቲያኒቷ የምታምንበት መሆኑን ገልፀው ዋናው ተቃውሞ የኦሮሚያ ቤተክህነት ተብሎ መቋቋሙ መሆኑን ገልፀዋል።

"አንዲት ቤተ ክህነት ናት ያለችው፤ ኦሮሚያም እንደ ሌሎቹ አገረ ስብከት ነው እንጂ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መባል የለበትም" የሚሉት መላከ ህይወት

"ዋናው የተቃወምነው ቤተ ክህነቱ ለብቻው መገንጠሉን ነው እንጂ የኦሮሞ ህዝብ በራሱ ቋንቋ ይማር፣ በኦሮምኛ ቅዳሴ ይቀድስ የሚለው እኔም ኦሮሞ እንደመሆኔ የኔም ጥያቄ ነው። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያኒቱን ከፍሎ ወይም ገንጥሎ ሳይሆን ይሄንን ጥያቄ ማስፈፀም የሚቻለው ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋር አንድ ሆኖ ጥያቄያችንን ለሚመለከተው ለቅዱስ ሲኖዶሱ አቅርበን በዛው መሰረት መልስ እንዲያገኝ ነበር።" ብለዋል

ቤተ ክህነት እያለ ሌላ ቤተ ክህነት ማቋቋም በሲኖዶሱ እውቅና እንደሌለው ገልፀው እነ ቀሲስ በላይ የሚያነሷቸው የቋንቋ ጥያቄ ተገቢ ነው ይላሉ።

ሲኖዶሱ በየትኛውም ቋንቋ ወንጌል እንዳይሰበክ፣ ቅዳሴ እንዳይቀደስ እንቅፋት እንዳልሆነም ጠቅስው ችግሩ የተደራሽነት ነው ይላሉ።

የበጀት እጥረት ካለ በጀት በመጨመር፣ የሰው ኃይልም ችግር ካለ የሰው ኃይል በማሰልጠን፣ በኦሮሚያ መንፈሳዊ ኮሌጆችን በመክፈት ችግሩን በተወሰነ በመቅረፍ የተደራሽነቱን እጥረት መቅረፍ ይቻላል ብለው እንደሚያምኑ ገልፀው ይህንንም አብሮ መስራት ይቻላልም ብለዋል።

በዋነኝነት ተቃውሞው ከመዋቅር ውጭ የለበትም የሚሉት መላከህይወት ለብቻው ተገንጥሎ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ተብሎ የተቋቋመው ነገር ይፈርሳል ማለት ነው ብለዋል።

ምንጭ፡ BBC

Report Page