BBC

BBC

ቲክቫህ ኢትዮጲያ

ትናንት ሌሊት በአክቲቪስት ጀዋር መሃመድ መኖሪያ ቤት አጋጠመ የተባለውን ክስተት ተከትሎ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች በርካታ ሰዎች ለተቃውሞ ሰልፎች አደባባይ ወጥተዋል።

የተቃውሞ ሰልፍ ከተደረገባቸው ከተሞች መካከል አምቦ፣ አዳማ እና ሻሸመኔ ከተሞች ይጠቀሳሉ። በዚህም በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።

አምቦ

በአምቦ በተቀሰቀሰው ግጭት ቢያንስ ሦስት ሰዎች በጥይት ተመተዋል ተብሏል።

በአምቦ በተቀሰቀሰው ግጭት ነዋሪዎች አምስት ሰዎች በጥይት መመታታቸውን ለቢቢሲ የተናገሩ ሲሆን፤ የሆስፒታል ምንጮች በበኩላቸው ሦስት ሰዎች ለሕክምና ወደ አምቦ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ሌሊቱን በአክቲቪስት ጀዋር መሃመድ መኖሪያ ቤት ተፈጸመ የተባለውን ክስተት ተከትሎ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ አደባባይ ወጥተዋል።

ለተቃውሞ የወጡትን ሰዎች ለመበተን የጸጥታ ኃይሎች አስለቃሽ ጭስ ከተኮሱ በኋላ ተቃዋሚዎች ፖሊሶች ላይ ድንጋይ መወርወር እንደጀመሩ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ያስረዳሉ።

ይህ ተከትሎም ነዋሪዎች አምስት ሰዎች በጥይት መመታታቸውን የተናገሩ ሲሆን፤ የአምቦ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ደበበ ፈጠነ በበኩላቸው ሦስት ሰዎች በጥይት ተመተው ለህክምና ወደ ሆስፒታላቸው መምጣታቸውን አረጋግጠዋል።

"እድሜያቸው ከ17-28 የሚገመቱ ሦስት ወጣቶች ወደ ሆስፒታላችን በጥይት ተመተው መጥተዋል። አንዱ ሆዱ ላይ የተመታ ሲሆን ከፍተኛ ጉዳት አጋጥሞት የቀዶ ህክምና ተደርጎለታል። ሁለተኛው መራቢያ አካሉ ላይ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን በአሁኑ ሰዓት የቀዶ ህክምና እየተካሄደለት ነው። ሦስተኛው ትከሻው አካባቢ ቀላል የሚባል ጉዳት የደረሰበት ሲሆን ለእርሱም ህክምና ተደርጎለታል" በማለት አስረድተዋል።

ግጭቱ የተከሰተው ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር መሆኑን ያስረዱት ነዋሪዎቹ፤ አንድ የፖሊስ መኪና ሙሉ ለሙሉ በቃጠሎ መውደሙን ጨምረው ተናግረዋል።

ግጭቱን ተከትሎ በከተማው የንግድ እንቅስቃሴ መቆሙን እና ከተማውን አቋርጦ የሚያልፈው መንገድ ዝግ መሆኑን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አዳማ

በተመሳሳይ መልኩ በአዳማ ከተማ የተቃውሞ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው። የታውሞ ሰልፎቹ ባህርያቸውን በመቀየር በሁለት ጎራ በተከፈሉ ሰዎች መካከል ግጭት መከሰቱን በሥፍራው የሚገኘው ሪፖርተራችን ተመልክቷል።

"ቄሮ ሌባ" በሚል ቡድን እና ለጀዋር መሐመድ ድጋፍ ለማሳየት በወጡ ወጣቶች መካከል ግጭት እንደተፈጠረ ሪፖርተራችን ከሥፍራው ዘግቧል።

የሃገር መከላከያ ሠራዊት እና ኦሮሚያ ፖሊስ በሁለት ቡድን ተከፍለው ወደ ግጭት ባመሩ ኃይሎች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ዘጋቢያችን ተመልክቷል።

እስካሁን በአዳማ በተከሰተው ግጭት በሰው እና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት በግልጽ ማወቅ ባይቻልም የሰው ህይወት ሳያልፍ እንዳልቀረ የተማው ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአዳማ ከተማ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ራውዳ ሁሴን "ሰው ሳይገደል እንዳልቀረ መረጃው ደርሶናል። ማን እና በምን ሁኔታ እንደተገደለ ግን እስካሁን ግልጽ መረጃ የለኝም" ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በሥፍራው የሚገኘው ሪፖርተራችን በከተማዋ የተቃውሞ ሰልፉን ተከትሎ ሱቆችን የመዝረፍ፣ የሥርዓት አልበኝነት ተግባራት ሲፈጸሙ ታዝቧል።

ይሁን እንጂ የንግድ እንቅስቃሴዎች ከመቆማቸውም በላይ ወደ ከተማዋ የሚያስገቡ መንገዶች ዝግ ናቸው።

ሻሸመኔ

በሻሸመኔ ከተማም በተመሳሳይ ሁኔታ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል።

የተቃውሞ ሰልፉ ተሳታፊ የሆነ አንድ ወጣት ለቢቢሲ ሲናገር "በጀዋር መሃመድ ላይ የሚደረገው ማስፈራሪያ መቆም አለበት" በማለት ተናግሯል።

ይህ ወጣት የተቃውሞ ሰልፉ ከሌሊቱ 10፡30 ጀምሮ ሲካሄድ እንደነበረ ያስረዳል።

ምንም እንኳን ወደ ሻሸመኔ የሚያስገቡ መንገዶች ሙሉ ለሙሉ ተዘግተው ቢገኙም፤ የተቃውሞ ሰልፉ በሰላም እየተከናወነ እንደሆነ ሌሎች የተቃውሞ ሰልፉ ተሳታፊዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

Report Page