BBC

BBC

ቲክቫህ ኢትዮጲያ

የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ዳይሬክትር ጃዋር መሀመድ በመንግሥት ተመድበውለት የነበሩት የደህንነት ጥበቃ አባላት በምሽት እንዲነሱብኝ ታዘዋል በሚል በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያስተላለፈው መልዕክት ቁጣና ተቃውሞን ቀሰቀሰ።

በዚህም ሳቢያ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የተቃውሞ ሰልፎች ያጋጠሙ ሲሆን በርካታ ወጣቶችም ድርጊቱን በመቃወም አዲስ አበባ በሚገኘው የጃዋር መሀመድ ቤት አቅራቢያ ተሰብስበዋል።

የጸጥታ ኃይሎችም በአካባቢው ተሰማርተው እንዳሉ የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ገልጸዋል::

ይህንንም በተመለከተ ቢቢሲ የፌደራል ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተርን ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡን ጠይቆ ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

ጃዋር እንደሚለው ማክሰኞ ዕኩለ ሌሊት አቅራቢያ ሁለት መኪኖች ወደሚኖርበት ቤት አካባቢ በመምጣት ጥበቃዎቹን "እኔ ሳላውቅ እቃቸውን ይዘው ቤቱን ለቀው እንዲወጡ" እንደተነገራቸው በፌስ ቡክ ገጹ ላይ አስፍሯል።

አክሎም ጥበቃዎቹ ለምን እንዲወጡ እንደጠየቁና ለስልጠና እንደሆነ እንደተነገራቸው እነሱም እንዳልተቀበሉ፣ ከዚያም ስልክ ተደውሎላቸው በአስቸኳይ ቤቱን ለቀው ካልወጡ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ጠቅሷል።

በጥበቃዎቹ ላይ ግፊቱ ሲበረታ ከእንቅልፉ ቀስቅሰው ሁኔታውን እንደነገሩትና እሱም ወደ አዛዡ ጋር ደውሎ ማብራሪያ እንደጠየቀና በመጀመሪያ ላይ "የተለመደው ጥበቃዎችን የመቀየር ሂደት መሆኑን" እንደተነገረው፤ ከዚያም ኃላፊው የተሰጠውን ትዕዛዝ ብቻ እያስፈጸመ መሆኑን ጽፏል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጄይላን አብዲ ከቢቢሲ የጃዋር መሃመድ ጥበቃ ያለ እርሱ እውቅና ለሊት ላይ ሊነሱ ነበር ስለሚለውና አሁን ስላለው ጉዳይ ከተቋማቸው በይፋ የደረሳቸው መረጃ አለመኖሩን ገልፀው እያጣሩ እንደሆነና መረጃው እንደደረሳቸው ምላሽ እንደሚሰጡን ገልፀዋል።

ጃዋር ቀጥሎም ጉዳዩን የበለጠ ለማወቅ ከፖለቲካና ከጸጥታ አመራሮች ጋር መነጋገሩን እነሱም የተከሰተውን ነገር ከስር መሰረቱ ለማወቅ ቃል እንደገቡለት ገልጿል።

ይህንንም ተከትሎ በቤቱ አካባቢ በርካታ ደጋፊዎቹ መሰብሰባቸውንና በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በጃዋር ላይ የሚገጥሙ ማንኛውንም ነገሮች በመቃወም ሰልፎች እየተካሄዱ ነው።

በአንዳንድ ቦታዎችም መንገዶች መዘጋታቸውንና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ መገታቱን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በአካባቢያቸው ያለውን ሁኔታ በተመለከተ የሚገልጹ ሰዎች በፎቶ ጭምር እያመለከቱ ነው።

Report Page