BBC

BBC

ቲክቫህ ኢትዮጵያ

የአቶ በቀለ ገርባ ቤተሰብ አባላት የአቶ በቀለ ጤና ሁኔታ እጅጉን አሳስቦናል አሉ!

የአቶ በቀለ ገርባ ባለቤት ወ/ሮ ሃና ረጋሳ ባለቤታቸው ዓይናቸው ላይ ሕመም ያጋጠማቸው ከዚህ ቀደም ለ7 ዓመታት ያክል እስር ቤት በቆዩበት ወቅት መሆኑን አስታውሰዋል። በአሁንም በቂ ሕክምና እያገኙ ስላልሆነ የግራ ዓይናቸው ሁኔታ አሳስቦናል ብለዋል።

"ግራ ዓይኑን ነው የሚያመው። ሕመሙ የጀመረው እስር ቤት ሳለ ነው። በወቅቱ ከእስር ቤት እየተመላለሰ ይታከም ነበር" የሚሉት ወ/ሮ ሃና፤ አሁን ላይ አቶ በቀለ የሕክምና ክትትል እያገኙ ስላልሆነ ግራ ዓይናቸው የማየት አቅም 50 በመቶ ብቻ መሆኑን ይናገራሉ።

አቶ በቀለ ሕክምና ማግኘት አለመቻላቸውም ትልቅ ስጋት እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ በወንጀል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የሚገኝ ሰው የጤና እክል ባጋጠመው ወቅት ሕክምና የማግኘት መብት አለው፤ መንግሥትም ይህን የማስፈጸም ግዴታ አለበት ይላል።

የፌደራል ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ፍቃዱ ጸጋ፤ አቶ በቀለ ገርባ ዓይናቸውን የመታመማቸውን ጉዳይ ከማህበራዊ ሚዲያዎች መስማታቸውን እንጂ በይፋዊ መንገድ ወደ መስሥሪያ ቤታቸው የመጣ መረጃ አለመኖሩን ይናገራሉ።

"ስለዚህ ጉዳይ የማውቀው ነገር የለም። በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ነው የተመለከትኩት። በመሥሪያ ቤታችን ውስጥ የተጠርጣሪዎች መብት መከበሩን የሚከታተሉ ጠበቆች አሉን። ስለዚህ ጉዳይ ከሰማን በኋላ ሁኔታዎችን አቀናጅተን ወደ ስፍራው ልከናቸዋል" ብለዋል።

ወ/ሮ ሃና በበኩላቸው አቶ በቀለ ሕክምና እንዲያገኙ ፍርድ ቤት የፈቀደ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ ላይ ‹‹አቶ በቀለ በግል ሕክምና ተቋም ሄደው ይታከሙ አይልም›› በሚል ምክንያት የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሕክምናውን መከልከሉን ተናግረዋል።

"ሐኪም ግራ ዓይኑ የማየት አቅሙ ከ50 በመቶ በታች እንደሆነ ነግሮታል። ስለዚህም በየወሩ ዓይኑ ላይ የሚወጋውን መርፌ ማቋረጥ እንደሌለበት ነበር የተነገረው" ይላሉ።

ከአቶ በቀለ ገርባ ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ቱሊ ባይሳ፤ የአቶ በቀለ ጉዳይ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እየታየ በነበረበት ወቅት ፍርድ ቤቱ ዓይናቸውን በግል የጤና ተቋም እንዲታከሙ ፈቅዶላቸው ነበር ይላሉ።

አቶ በቀለ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ከተዘዋወሩ በኋላ ግን የማረሚያ ቤቱ አስተዳዳሪዎች የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አልደረሰንም በማለት ሕክምና እንዲያገኙ ፍቃድ መከልከሉን ይናገራሉ።

አቶ ቱሊ "ፍርድ ቤት በግል የሕክምና ተቋም እንዲከታከሙ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ማረሚያ ቤቱ ይህን እየፈጸመ አይደለም። ስለዚህ አቤቱታችንን ጉዳያቸው እየታየ ባለቤት ፍርድ ቤት እናቀርባለን" ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ አቶ ፍቃዱ ጸጋ አንድ ተጠርጣሪ ፍርድ ቤት ሕክምና እንዲያገኝ ፈቅዶለት ተጠርጣሪው ሕክምና እንዳያገኝ መከልከል ወንጀል ነው ካሉ በኋላ የተጠርጣሪውን መብት የከለከለ አካል በሕግ ይጠየቃል ብለዋል።

Report Page