BBC

BBC

ቲክቫህ ኢትዮጵያ

በርግጥ ወጣቶቹ የእርቅ ሃሳባቸው ምንድን ነው?

ዳንኤል ዳባ፣ አብዲሳ ንጉሴ እና ተሰማ ገመዳ ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተገኙ ወጣቶች ናቸው። እነዚህ ወጣቶች ከየመጡበት አካባቢዎች ያገኙትን ሰላምና እርቅ ሃሳብ በማደራጀት 'እኔም የእርቅ ሃሳብ አለኝ' ሲሉ ተወዳድረው ነበር።

ለመሆኑ የእርቅ ሃሳባቸው ምንድን ነው?

ቢሾፍቱ

አብዲሳ ንጉሴ የቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪ ሲሆን በወሎ ዩኒቨርስቲ አምስተኛ አመት የሕግ ተማሪ ነው። የእርቅና ሰላም ኮሚሽን የሰላም ቀንን በማስመልከት ባዘጋጀው ውድድር ውድድር ላይ "እኔም የእርቅ ሃሳብ አለኝ" በሚል ርዕስ ተወዳድሮ ማሸነፍ ችሏል።

የእርቅና ሰላም ኮሚሽን ኣዘጋጀው ይህ ውድድር እኔም የእርቅ ሃሳብ አለኝ በሚል ስም የተዘጋጀ ሲሆን የእርቅ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች በማወዳደር ሸልሟል።

አብዲሳ በቢሾፍቱ አካባቢ ያስተዋለውን የሽምግልና ስርዓት ላይ መሰረት በማድረግ ነበር የእርቅ ሃሳብ አለኝ በማለት የተወዳደረው።

"ሽምግልና በኦሮሞ ባሕል ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው። በሽምግልና ወንጀል የማሕበረሰብ፣ የቤተሰብ ጉዳይ ሊፈታበት ይችላል። በሽምግልና ሕብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ልዩነቶች ሳይሰፉ መፍታት ይቻላል" የሚለው አብዲሳ ሕዝቡ የተለያየ የሆነ የሽምግልና ባሕል እንዳለው በመግለጽ፣ እርሱም ይህንን የማሕበረሰቡን የሽምግልና ባሕል መሰረት በማድረግ የዕርቅ ሃሳቡን ማቅረቡን ገልጾ፣ "አዲስ ነገር ከራሴ አልጨመርኩም" ይላል።

በሌላ በኩል ደግሞ እርሱ ያዘጋጀው ጥናታዊ ጽሑፍ ወጣቶች የራሳቸውን ባሕል እንዲማሩ ያግዛልሲል ለቢቢሲ ገልጿል።

ወጣቶች በአሁን ሰዓት ባሕላቸውን እየረሱ ነው። ይህ ጥናታዊ ጽሑፍም ወጣቶች የራሳቸውን ባሕል እንዲረዱ እና በሽምግልና ስርዓት ውስጥ እንዲሳተፉ ያግዛቸዋል ሲል ያስረዳል።

ወጣቶች የራሳቸውን ባሕል ማወቅ አለባቸው ችግሮች ቢኖሩም በገዳ ስርዓት ውስጥ ታቅፈው ነው መፍታት ያለባቸው በማለት ምክሩን ያስተላልፋል።

ወደፊት እዚህ ውድድር ላይ ከተሳተፉ ወጣቶች ጋር በጋራ በመሆን ሕዝባቸውንና አካባቢያቸውን ለመርዳት በጋራ ለመስራት እቅድ እንዳላቸው ይናገራል።

አዲስ አበባ

ዳንኤል ዳባ አዲስ አበባ ነው ተወልዶ ያደገው። የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አጥንቷል። ዳንኤል 'እኔም የእርቅ ሐሳብ አለኝ' ለሚለው ውድድር ቤተ እምነቶች እንዴት ሰላም በማምጣት ውስጥ ሊሳተፉ ይችላሉ በሚል ጽሁፉን ማቅረቡን ይናገራል።

መጀመሪያ ቤተ እምነቶች ሰላምን በማምጣት ረገድ ምን ሊሰሩ ይችላሉ የሚለውን ሃሳብ በሥራ ቦታው አካባቢ ለመስራት እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት ነው 'የእኔም የእርቅ ሃሳብ አለኝ' የሚለው ውድድር መኖሩን የሰማው። ከዚህ በኋላም ይህንኑ ሃሳቡን ሰፋ አድርጎ ለውድድሩ አቀረበ።

በኋላ ላይ ግን የቤተ እምነቶች ሰላምን በማስፈን ረገድ የታየባቸው ክፍተት ምንድን ነው? ጥንካሬያቸውስ የሚለውን በዝርዝር በማየት ለመስራት መሞከሩን ያስታውሳል።

ዳንኤል በርካታ ኢትዮጵያውያን በቤተ እምነቶች ውስጥ ማደጋቸውን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበባቸውን፣ ቅዱስ ቁርዓን መቅራታቸውን በማንሳት ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ውስጥ ቤተ እምነቶች ቁልፍ ሚና እንደሚኖራቸው ያስረዳል።

ይህ ብቻም ሳይሆን ደግሞ በአገር ውስጥ በሚኖር አለመግባባትን ለማስታረቅ ወደፊት የሚመጡ ሰዎች በየእምነት ተቋም ውስጥ ያሉ አባቶች እንደሚሆኑ ማስተዋሉን ያነሳል።

እነዚህ ሁለት የማይታለፉ ነጥቦች ለሰላምና እርቅ ወሳኝ መሆናቸውን ዳንኤል ይጠቅሳል።

የቤተ እምነቱ ተከታዮች መሪዎቻቸውን ስለሚሰሙ የሰላምና የእርቅ ሀሳብ በእነሱ በኩል መምጣት አለበት የሚለው ዳንኤል አስታራቂም ሆነው ሰባኪ እነዚህ የቤተ እምነት አባቶች ቢሳተፉ መልካም መሆኑን ማስተዋሉን ይናገራል፡፡

"ሰላም ከግለሰብ የሚጀምር ነው" የሚለው ዳንኤል ነገውን የሚያስብ ወጣት የራሱን እንዲሁም የሌሎችን ሰላም በሚጠብቅበት ወቅት ሰላሙን ለሌሎች እንደሚያካፍል ይህም ለአገር እንደሚተርፍ ይናገራል።

ይህ የሰላም እና የእርቅ ሀሳብ ቀድሞውንም በማህበረሰቡ እና በቤተ እምነቶች ውስጥ ያለ መሆኑን በመግለጽም " እርሱ እንዴት ይጎልብት" የሚለው ላይ ማተኮር መፈለጉን ይናገራል።

ስለ ሰላም ወጣቶች እና ሕጻናት ላይ አበክሮ መስራት እንደሚያስፈልግ በመግለጽም የሃይማኖት አባቶችም እነዚህ አካላት ላይ አተኩረው መስራት እንደሚያስፈልጋቸው አስተውሏል።

ሰላም ከወጣትነት፣ ከስሜት ከብሔር ከሁሉም ይበልጣል ሲልም ይገልጻል።

ኮንሶ

ተሰማ ገመዳ የመጀመሪያ ዲግሪውን በኢኮኖሚክስ የትምህርት ዘርፍ ነው ያገኘው። ኮንሶ ተወልዶ ያደገው ተሰማ የእርቅ ሃሳብ ብሎ ካቀረበው መካከል በኮንሶ ማሕበረሰብ ዘንድ ያለ ባህላዊ የእርቅ ሃሳብ መሆኑን ይገልጻል።

ባሕላዊ የእርቅ ሀሳብ ውስጥ ተሳትፎ ሲያደርጉ የሚታዩት በእድሜ ከፍ ያሉ፣ አዛውንቶች መሆናቸውን በመግለጽ በእርሱ ግምገማ ወጣቶች በእርቅ ስርዓት ውስጥ ሲሳተፉ አልተመለከተም።

በእድሜ በገፉት ሰዎች ዘንድም ወጣቶቹን ከባህል አፈንጋጭ አድርጎ የመመለክት አዝማሚያ አለ የሚለው ተሰማ፣ ወጣቶቹም ኋላ ቀር ስርዓት አድርጎ የመመልከት ዝንባሌ እንዳላቸው አስተውሏል።

ይህ የትውልድ ክፍተትን ለመፍታት ወጣቶችን በእርቅ ስርዓቱ ውስጥ ማሳተፍ ቢቻል መልካም መሆኑን፣ ወጣቱንም መሳብ እንደሚቻል ይናገራል።

በባሕላዊ እርቁ ላይ የሚወሰኑ ውሳኔዎችም ሰብዓዊ መብትን የሚጥሱ፣ የሃይማኖት ነጻነትን የማያከብሩ ሆነው ያገኘበት ወቅት መኖሩን በመግለጽ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች በዚህ ረገድ ስልጠና ቢወስዱ ወጣቶችን የበለጠ ለማሳተፍና ለመማረክ ይችላሉ ሲል ሃሳቡን ለቢቢሲ አጋርቷል።

ተሰማ ወጣቶችን በእርቅ እና በሰላም ሂደት ውስጥ ማሳተፍ ግጭቶችን ለመቀነስና ለማስቀረት ሁነኛ መፍትሔ ይሆናል ሲልም ያስረዳል።

በግለሰቦች መካከል የሚነሳ ግጭት አድጎና ሰፍቶ የአገር ሰላም እንደሚያደፈርስ እንዲረዱ፣ ግጭቶች የሚያደርሱትን ምጣኔ ሃብታዊና ማሕበራዊ ጫና እንዲመለከቱና እንዲማሩ ማድረግ ወጣቶቹ ለሰላም የሚኖራቸውን ድርሻ ያጎላዋል ይላል።

በአገራችን ሰላም እና እርቅ ላይ ወጣቶችንና ሴቶችን ማሳተፍ ወሳኝ መሆኑንም ያነሳል።

ሰላም በሚደፈርስበት ወቅት ቀድመው ሲሯሯጡ የሚታዩት ፖለቲከኞች መሆናቸውን ያስተዋለው ተሰማ፣ የአገር ሽማግሌዎች በሰላምና እርቅ ጉዳይ መቼ ነው መሳተፍ ያለባቸው፣ ፖለቲከኞችስ ጣልቃ መግባት ያለባቸው መቼ ነው የሚለው ቢለይ መልካም መሆኑን ይናገራል።

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ ወጣቶች የእርቅ ሃሳባቸውን በማምጣት መወያየትና ጠቃሚውን መማር ቢቻል ለዘላቂ ሰላም አማራጭ መሆኑን ይገልጻል።

ለወደፊት ውድድሩን አዘጋጅቶ የነበረው የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ጋር ወደ ፊት ለመስራት ሃሳብ እንዳለው ይናገራል።

Report Page