BBC

BBC

ETHIO ሪፖርተር

ምርጫ 2013 ፡ ምርጫው ከመካሄዱ በፊት የሚቀድሙ ነገሮች አሉ የሚለት ተቃዋሚ ፓርቲዎች

የምስሉ መግለጫ,
አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፣ አቶ ጣሂር መሐመድ እና መረራ ጉዲና (ፕሮፌ.)

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ትናንት [አርብ] በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ አስፈላጊው ጥንቃቄ ማድረግ ከተቻለ ስድስተኛው ዙር አገራዊ ምርጫ ሊካሄድ እንደሚችል የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ማስታወቃቸው ይታወቃል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በአገሪቱ ያለውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሁኔታን በተመለከተ የመሥሪያ ቤታቸውን ግምገማ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ጊዜ ነው አገራዊውን ምርጫ ለማካሄድ እንደሚቻል ያመለከቱት።

ካለው የወረርሽኝ ስጋት አንጻር የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመከላከል የሚያስችሉ እርምጃዎችን ከግምት ውስጥ የሚያስገባ ሁኔታ የምርጫ ሥነምግባር፣ ደንብና ማስፈፀሚያ መመሪያዎችን በማዘጋጀት ስድስተኛውን አጠቃላይ ምርጫ ማካሄድ እንደሚቻል ሚኒስትሯ አመልክተዋል።

ባለፈው ዓመት ሊካሄድ ታስቦ የነበረው ምርጫ በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ ሲተላለፍ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተለያየ ሃሳብ ተንጸባርቆ ነበር። አንዳንዶች የምርጫውን መራዘም ውሳኔ ሲደግፉ ሌሎች ደግሞ ተቃውመው ቅሬታ ሲያሰሙ ቆይተዋል።

ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምን ይላሉ?

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር)፤ የመንግሥት ፍላጎት በተለያየ ጊዜ ሊቀያየር እንደሚችል ገልጸው፤ "አሁን ደግሞ ፍላጎታቸው ምርጫ ማድረግ ነው" ብለዋል።

መረራ (ፕሮፌ.) ከዚህ ቀደም "ብሔራዊ መግባባት ላይ ሳይደረስ ምርጫው እንዴት ሊካሄድ ይችላል? ምንስ ጠቀሜታ ይዞ ይመጣል?" የሚል ጥያቄ እንደነበራቸው አስታውሰው፤ ይሁን እንጂ ምርጫው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሊዘገይ ችሏል።

ከዚህ ቀደም ምርጫው እንዲራዘም የተደረገው የጤና ሚኒስቴር በሽታው አሳሳቢ መሆኑን በመግለጹ መሆኑን ያስታወሱት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጣሂር መሐመድ፤ አሁን ላይ ጥንቃቄዎችን በማድረግ ምርጫውን ማካሄድ ይቻላል መባሉን በበጎ እንደሚመለከቱት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀመንበር አቶ አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው ምርጫ መካሄድ ይቻላል መባሉ ገና በመንግሥትና በተወካዮች ምክር ቤት አለመፅደቁን ጠቅሰው፤ ጤና ሚኒስቴር ይህን ካለ ማንም ሰው ከባለሙያዎች ጥናትና ዕውቀት በበለጠ ሁኔታዎችን መገምገም ስለማይችል የእነርሱን ግምገማ መቀበል እንደሚገባ አመልክተዋል።

ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ ይህን ይበሉ እንጂ ባለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ምርጫ ይካሄዳል መባሉን ጥያቄ ውስጥ ከተውታል።

"ፖለቲካዊ ጥያቄዎች አስኪመለሱ ድረስ ምርጫው መቆየት አለበት" ትዴፓ

አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) አገሪቷ ካለችበት ሁኔታ አንጻር ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ሕዝቡ የሚቀበለው ተዓማኒ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ አለ ወይ? የሚለውን ጥያቄ መመለስ የግድ ነው ይላሉ።

በርካታ ግጭቶች እየተከሰቱ ባለበት ወቅት የሰላምና የመረጋጋት ሁኔታ ጥያቄ ውስጥ መግባቱን የሚያነሱት አረጋዊ (ዶ/ር)፤ ከዚህም በተጨማሪ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ሁሉም ተቋሞች ዝግጁ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

በእርሳቸው ፓርቲ ምልከታም "ሁሉም ተቋሞች ያሉበት የዝግጅት ሁኔታ አጠያያቂ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ መገምገም ችለናል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከመገናኛ ብዙሃ አንጻርም ምርጫውን ለሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በእኩልነት መዘገብ ይችላሉ ወይ? የሚለውም ጥያቄ ግልፅ መልስ እንደሚያሻው ጠቅሰዋል።

በመሆኑም "እነዚህና መሰል ጥያቄዎች በቂ መልስ ስለማናይባቸው፤ በቂ መልስ እስከሚያገኙ ድረስ ምርጫው መቆየት አለበት የሚል እምነት አለን" ብለዋል።

ምርጫ ማካሄድ የሚቻለውም የቅድመ ምርጫው ሁኔታው ሲመቻቹ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ስለዚህም ምርጫ መካሄድ አለበት፤ የለበትም የሚል አቋም የሚኖራቸው ቅድመ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት እንደሆነ ተናግረዋል።

"በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ብቻ የታሰሩት ሊፈቱ ይገባል" አብን

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጣሂር መሐመድ ምርጫውን ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ እንዲሆን ሁሉም በጨዋታው ሕግ ለመዳኘት በቅድሚያ መዘጋጀት አለበት በቀዳሚነት ጠቅሰዋል።

"በእኛ አገር ዲሞክራሲ ሆነ በአፍሪካ ዲሞክራሲ ተሞክሮ ምርጫን ተከትሎ የሚከሰቱ አደጋዎችን የሚፈጥረው ገዢ ፓርቲ ነው" ያሉት አቶ ጣሂር፤ የሚመጣውን ነገር በአግባቡ ለመቀበልና በምርጫው ሂደት ላይ ከአፈናና የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን ከማሳደድ ተቆጥቦ ምርጫውን በነፃነትና በጥንቃቄ ማድረግ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ከዚህም ባሻገር "በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ብቻ" የታሰሩ ሰዎችን በአፋጣኝ አጣርቶ ነፃ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል። "ከሌላው ወገን የታሰረን አካል ሚዛን ለመጠበቅ የታሰሩ ሰዎች በአስቸኳይ ሊፈቱ ይገባል" ብለዋል አቶ ጣሂር።

በሕግ አግባብ ወንጀል የሰሩና ያልሰሩ ሰዎችን በተጨባጭ ማስረጃ ለይቶ ውሳኔ ማሳለፍ እንደሚያስፈልግም አሳስበው፤ እነዚህ ጥያቄዎች ከተመለሱና ሁኔታዎች ከተመቻቹ ለምርጫው መካሄድ ዝግጁነት እንዳለ አመልካች መሆናቸውንም አቶ ጣሂር ተናግረዋል።

"ሕዝቡ ሰላም የሚያገኘው ምርጫ ስለተካሄደ ብቻ አይደለም" ኦፌኮ

መረራ ጉዲና (ፕሮፌ.) ምርጫ ቦርድ በራሱ ገለልተኛ ሆኖ ምርጫውን ያስጽማል ወይ በሚለው ላይ ጥያቄ እንደነበራቸው ይናገራሉ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት ሲደረግ "ምርጫ ከመከናወኑ በፊትም መንግሥት የሚያደርሰውን ጫና ማቆም አለበት። የዲሞክራሲው ምህዳር መስፋት አለበት። በምርጫው መሳተፍ የሚፈልግ በምርጫ መሳተፍ አለበት። እስር መቆም አለበት" ብለዋል።

"ምርጫ ቀልድ አይደለም። የሚሊዮኖች ዲሞክራሲያዊ መብት የሚረጋገጥበት ነው። ምርጫ እኮ በንጉሡም፣ በደርግም በመለስ ዘመንም ሲካሄድ ነበር። ይህን ምርጫ ምን አዲስ ነገር ያደርገዋል?" ሲሉ በመጠየቅም፤ ሕዝቡ ሰላምና መልካም አስተዳደር የሚያገኘውም ሆነ ሕይወቱ የሚሻሻለው ምርጫ ስተደረገ ብቻ አለመሆኑን አንስተዋል።

ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ለማካሄድ መሟላት ያለባቸው በርካታ ቅድመ ሁኔታዎች እንዳሉ የጠቀሱት መረራ (ፕሮፌ.)፤ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ አለመደረሱን ተናግረዋል።

ምርጫው በወረርሽኝ ምክንያት እንደማይካሄድ ውሳኔ በተላለፈበት ጊዜ ከበሽታው አንጻር ያሉ ለውጦችን መሠረት በማድረግ የጤና ባለሙያዎችና ተቋማት በሚሰጡት ምክር አማካይነት መቼ መካሄድ እንደሚገባው እንደሚገለጽ ተወስኖ ነበር።

በዚህም መሠረት ነው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የወረርሽኙን ሁኔታ በመገምገም ከበሽታው አንጻር ምርጫና ሌሎች እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ምክረ ሐሳብ ያቀረበው።

በተከታይነትም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚሰጠው ውሳኔ መሠረት ምርጫው የሚካሄድበትን ጊዜና ሁኔታ በቅርቡ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።


ምንጭ፦ BBC አማርኛ

® ETHIO-ሪፖርተር

Report Page