GM

GM

ገራዶ ሚዲያ

በአማራና ትግራይ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ የተከሰተው ምንድን ነው?

ትናንት ከማለዳ ጀምሮ በወልቃይት ጠገዴ በተለይም በአማራ እና ትግራይ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት እንደነበር የአካባቢው የፀጥታ አካላት ተናገሩ። የሁለቱም ክልል የፀጥታ ኃላፊዎች እንደሚናገሩት አንዳቸው በሌላኛቸው ክልል ወገን ግጭት ተቀስቅሶ ነበር።

በአማራ ክልል ሥር የሚገኘው የጠገዴ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ሙሉጌታ እንደሚሉት፣ እርሳቸው በሚያስተዳድሩት ወረዳ ምንም ግጭት እንደሌለና በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኘው የጸገዴ ወረዳ ግን ከምርጫው ጋር ተያይዞ ግጭት መፈጠሩን እንደሰሙ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል ፀጥታ ከፍተኛ ኃላፊ ደግሞ በምዕራብ ትግራይ ጸገዴ አካባቢ በትግራይ መሬት ገብቶ የተኮሰ አካል እንደሌለ በመግለጽ "በአማራ ክልል ውስጥ ግን ተኩስ እንደነበረ ሰምተናል" ሲሉ ተናግረዋል። ይህ ሙከራ "ህዝብን ለማደናገጥ የታሰበ" ቢሆንም ህዝቡ ግን በነቂስ ወጥቶ ድምጹን ሰጥቷል ብለዋል ሀላፊው።

የህወሓት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ከቢቢሲ ኒውስ ደይ የሬድዮ ፕሮግራም ላይ በነበራቸው አጭር ቆይታ በትግራይ ደቡብ አካባቢ ምርጫውን የማደናቀፍ ሙከራዎች እንደነበሩ ገልጸዋል። የትግራይ ምርጫ ኮሚሽን በበኩሉ "የትምክህት ሃይሎች" ሲል በገለጻቸው አካላት ከምርጫ ጣቢያ ራቅ ባለ አካባቢ ትንኮሳ እንደነበር በፌስቡኩ አሳውቋል። "በቂ ሃይል ስለነበር ትንኮሳው አልተሳካም። ሙከራው ለደቂቃዎች ብቻ እንደነበረም ለማወቅ ችለናል" ብሏል ኮሚሽኑ።

በሌላ በኩል የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክብረዓብ ቸርነት፣ በትግራይ ክልል በሚገኘው የጸገዴ ወረዳ ውስጥ ልዩ ስሙ ጨቋር ኩዶቢን በሚባል ቦታ ከሌሊቱ 8 ሰዓት አካባቢ የትግራይ ልዩ ኃይል ነዋሪው ወጥቶ እንዲመርጥ እና ሚሊሻው ደግሞ "አማራ ሊወርህ እየመጣ ስለሆነ መንገድ ዝጋ" የሚል ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው ይገልጻሉ። ነገር ግን ሕዝቡ የመምረጥም ሆነ መንገድ የመዝጋት ፍላጎት አልነበረውም ያሉት አቶ ክብረዓብ ሕዝቡ ምላሽ ባለመስጠቱ "ከትግራይ ልዩ ኃይል በኩል ተኩስ ተከፈተበት" ብለዋል። ይህንን ተከትሎም ሕዝቡ ራሱን በመከላከሉ ግጭት ተነስቶ እንደነበር ገልጸዋል።

አሁን አካባቢው የተረጋጋ ቢሆንም ምርጫውን ተከትሎ ግን የተለየ ነገር ሊኖር እንደሚችልም ጠቁመዋል። ባለፉት ወራት በአካባቢው ብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲካሄዱ እንደነበር የሚገልፁት አቶ ክብረአብ ይህንንም ለሚመለከታቸው አካላት ቢያመለክቱም እስካሁን መልስ አለማግኘታቸውን ገልጸዋል። ከዚህ በፊትም የምርጫ ካርድ ለምን አላወጣችሁም በሚል ሳቢያ ከ500 በላይ የወልቃይት ጠገዴ ተወላጅ ወጣቶች በትግራይ ክልል መንግሥት መታሰራቸውን የማንነት ኮሚቴው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ተናግረዋል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Report Page