BBC

BBC

ETHIO ሪፖርተር

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ በመተከል ዞን ነዋሪዎች ላይ ጥቃት ተፈጸመ!


የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ኮማንደር ነጋ ጃራ ለቢቢሲ እንደገለጹት "ፀረ ሠላም" ያሏቸው ኃይሎች በወንበራ ወረዳ መልካ በምትባል ቀበሌ ሠላማዊ ሰዎችን በማገት፣ የጦር መሣሪያዎችን በመቀማትና በአካባቢው ማኅበረሰብ ንብረት ላይ ዘረፋ ፈጽመዋል ብለዋል። በትላንትናው ዕለትም [ሰኞ] በቡለን ወረዳ ኤጳር በምትባል ቀበሌ እነዚሁ ኃይሎች በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የአፈናና የግድያ ወንጀል ከመፈጸማቸው በተጨማሪ የተለያዩ ጉዳቶችን ማድረሳቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቢቢሲ በአካባቢ ያሉ ነዋሪዎችን ጠይቆ እንደተረዳው በተለያዩ ጊዜያት ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በሚፈጸመው ጥቃት የተነሳ የዕለት ከዕለት ተግባራቸውን በስጋት ውስጥ ሆነው እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል። በሚፈጸሙት ጥቃቶችም በሰው ህይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ በመሆኑ እንቅስቃሴያቸው መገደቡንና ክስተቱም ሁሉም በነጻነት እንዳይንቀሳቀስ በማድረጉ በአካባቢዎቹ ባለው ሥራ ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የወረዳው የመንግሥት ሠራተኛ ተናግረዋል።

ጥቃት ፈጻሚዎቹ ከአካባቢው ነዋሪዎች በተጨማሪ የጤናና ግብርና ባለሙያዎችን ለማፈን ከመሞከራቸውም በላይ በመንግሥት መዋቅር ላይ ጥቃት ለማድረስ የሞከሩ መሆኑን ጠቅሰው ከመካከላቸው አንዳንዶቹ ወደ ሌላ ወረዳ መሸሻቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት ተከትሎ በወጣው መረጃ መሰረት የአካባቢው ፖሊስ፣ የመከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ ልዩ ኃይል በጋራ በመሆን ወደ ወረዳዎቹ በመግባት ጥቃቱን ለማስቆምና ፈጻሚዎቹን ለመቆጣጠር በቅንጅት እየሠሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ምክትል ኮሚሽነር ኮማንደር ነጋ ጃራ በወረዳዎቹ እንደሚሉት ጉዳት እያስከተለ ያለው ጥቃት የሚፈጸመው ስሙን ለጊዜው መጥቀስ ባልፈለጉት "የተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድን አባላት" መሆኑንና በቁጥጥር ስር እያዋሉ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ እስካሁን የታገቱ እና የሞቱ ሰዎች ቁጥር በተመለከከተ "በቁጥር ደረጃ በዝርዝር አልተለየም" ያሉት ኮማንደር ነጋ፤ መረጃው ተሰባሰቦ ሲያልቅ እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል።

ምክትል ኮሚሽነሩ በክልሉ ባሉ አንዳንድ አካባቢዎች እየተፈጸመ ካለው ጥቃት ጋር በተያያዘ "ፀረ ሠላም" ያሏቸው ኃይሎች ከውጪ አገር ጭምር ድጋፍ እንደሚደረግላቸው መረጃ መገኘቱን ጠቅሰው "ወጣቶችን ለመመልመል እንደሚንቀሳቀሱም" ጨምረው ተናግረዋል። ጥቃት ፈጻሚዎቹ ከቀናት በፊል መልካን በሚባል ቀበሌ 30 ሰዎችን አፍነው የነበረ ሲሆን አሁን እነሱን መልቀቃቸውን አመልክተው፤ የያዟቸውን ሰዎች ቡድኑን እንዲቀላቀሉ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በተለያዩ ጊዜያት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ማንነታቸው ያልተገጹ ቡድኖች በነዋሪዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ከማድረሳቸው ባሻገር በተደጋጋሚ ሰዎችን እያገቱ እንደሚወስዱ ሲዘገብ ቆይቷል። ይህንንም ለማስቆም የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ከአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን ጥቃት ፈጻሚዎቹን ለመቆጣጠርና ድርጊቱን ለማስቆም እየጣሩ መሆኑ ተገልጿል።

Report Page