BBC

BBC


በአዲስ አበባ በሚሌኒየም አዳራሽ በኮቪድ-19 ለተያዙ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጠው ማዕከል የጽኑ ሕሙማን ክፍል አልጋዎች ሙሉ በሙሉ በሕሙማን ሲያዙ፤ ከፊል ጽኑ ሕሙማን ክፍልን የሚያስተናግደው ክፍልም እየሞላ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናገሩ።

ማዕከሉ በኮቪድ-19 የታመሙ እና የሕክምና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች ሕክምና እንዲያገኙበት በሚል የተደራጀ ነው።

በሚሊኒየም አዳራሽ ለይቶ ማቆያ ከሁለት መቶ በላይ ታካሚዎች መኖራቸውን የማዕከሉ ዳይሬክተር ዶ/ር ውለታው ጫኔ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በአሁኑ ሰዓት ሕክምና ማዕከሉ በቀን በአማካኝ በጽኑ የታመሙ 20 ሕሙማንን እየተቀበለ እያስተናገደ እንደሚገኝ የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ በአሁኑ ሰዓት ከ210 በላይ ታካሚዎች አልጋ ይዘው እያታከሙ እንደሚገኙ አብራርተዋል።

ከእነዚህ ታካሚዎች መካከል ወደ 118 የኦክስጅን ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው መሆናቸውን ጨምረው ገልፀዋል።

የማዕከሉ የሕክምና ክፍሎች በአራት ደረጃ ተከፍለው መደራጀታቸውን ዳይሬክተሩ ይገልጻሉ።

የመጀመሪያው የጽኑ ሕሙማን ክፍል በከፍተኛ ግፊት ኦክስጅን ማግኘት ያለባቸው ታካሚዎች የሚታከሙበት ክፍል፣ ሁለተኛው ክፍል በኦክስጅን ድጋፍ የሚታከሙበት ክፍል፣ ሦስተኛው መጠነኛ የሆነ የኦክስጅን ድጋፍ የሚፈልጉ ታካሚዎች የሚታከሙበት ክፍል፣ የመጨረሻው ተጓዳኝ ችግር ኖሮባቸው በቤታቸው ራሳቸውን መለየት የማይችሉ እና የባለሙያ ክትትል የሚፈልጉ ሕሙማን የሚታከሙበት ክፍል ነው።

ሁሉም ክፍሎች አለመሙላታቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማም ሆነ በአገር ደረጃ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን በመግለጽ፤ በጽኑ የሕክምና ክፍል ካሉ አልጋዎች አብዛኛዎቹ በሕሙማን መያዛቸውን ይገልፃሉ።

ለዳይሬክተሩ ቃለ መጠይቅ ባደረግንላቸው ዕለት (ነሐሴ 20 ቀን 2012 ዓ. ም.) በከፍተኛ ግፊት የኦክስጅን ድጋፍ የሚፈልጉ ሕሙማን ክፍል አምስት አልጋዎች ብቻ ክፍት መሆናቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

መጠነኛ የኦክስጅን ድጋፍ በሚፈልጉ ታካሚዎች ክፍል ግን ከዚያ በላይ አልጋዎች ክፍት መሆናቸውን ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት አልጋዎች ሙሉ በሙሉ የሞሉ ባይሆንም “ሂደቱ ያስፈራል፤ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የማንጠነቀቅና መከላከሉ ላይ በርትተን የማንሰራ ከሆነ የኦክስጅን ፍላጎት ያላቸው ታማሚዎች አልጋ ሊያጡ ይችላሉ” ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ ማዕከሉ በጽኑ ታምመው የሚመጡ ሰዎችን የመቀበል አቅሙ ፈተና ውስጥ ሊወድቅ እንደሚችል ይናገራሉ።

ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ማዕከሉ ያሉት የአልጋ ቁጥሮች ብቻ ሳይሆን በጽኑ ታምመው የሚመጡ ሰዎች በቶሎ አልጋ ለቅቀው የሚሄዱ ባለመሆናቸው ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።

ሕሙማኑ ለማገገም ጊዜ ስለሚወስድባቸው ቢያንስ ለሁለት ሳምንት አልጋው ይዘው ይቆያሉ በማለት በማዕከሉ ያለውን ልምድ የሚያስረዱት ዳይሬክተሩ፤ ስለዚህ የኦክስጅን ድጋፍ የሚፈልጉ ሕሙማንን በዚህ መልክ ለሳምንታት ተቀብሎ መቀጠል እንደማይቻል ይናገራሉ።

እንደ ባለሙያ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከሕክምና ባለሙያዎችና ተቋማት አቅም ውጪ እንዳይወጣ ስጋት አለን ያሉት ኃላፊው፤ የመከላከልና የጥንቃቄ ስራው ላይ ጠንክሮ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ማዕከሉ የመቀበል አቅሙ 670 ሕሙማንን ሲሆን፤ ተጨማሪ ነገሮች ተደራጅተውበት 1000 ድረስ መቀበል እንደሚችል ይናገራሉ።

ማዕከሉ በኤሌትሪክ የሚሰሩ መጠነኛ ኦክስጅን የሚፈልጉ ሕሙማን ለመቀበል የሚያስችል ስራ እየሰራ መሆኑን ገልፀው፤ ከፍተኛ የኦክስጅን ድጋፍ የሚፈልጉ ሰዎችን ለመቀበል ግን የሚያስችል ስራ ለመስራት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እንደሚጠይቅ ያስረዳሉ።

እንደ ጤና ሚኒስቴር ገለጻ፤ ከ42 ሺህ በላይ ሰዎች በኮቪድ-19 የተያዙ ሲሆን፤ ከዚህ መካከልም ከፍተኛው ቁጥር የሚገኘው በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ነው።

Via :- BBC

@Yenetube @Fikerassefa

Report Page