BBC

BBC

Greatful-Ethiopia

በኦሮሚያ እና ድሬዳዋ ባጋጠሙ ግጭቶች ቢያንስ አራት ሰዎች መገደላቸው ተነገረ!


ትናንት እና ከትናንት በስቲያ በኦሮሚያ ክልል የሃረርጌ ዞኖች፣ በምዕራብ አርሲ ዞን እና በድሬዳዋ ከተማ ባጋጠሙ ግጭቶች ቢያንስ 4 ሰዎች መገደላቸውን እና በርካቶች መቁሰላቸውን ፖሊስ፣ የሆስፒታል ምንጮች እና የየአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።


👉ጭሮ

በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የሚገኘው የአቶ ጃዋር መሐመድ ጤና ታውኳል የሚለው ዜና መሰማቱን ተከትሎ ሰዎች ከትናንት በስቲያ እና ትናንት በጭሮ ለተቃውሞ ከወጡ በኋላ ግጭት ተከስቶ ቢያንስ ሁለት ሰዎች መገደላቸውን የሆስፒታል ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።የጭሮ ሆስፒታል ተጠባባቂ ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ሳዳም አሉዋን በጥይት ተመትተው ወደ ሆስፒታላቸው ከመጡ 24 ሰዎች መካከል የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ትናንት ለቢቢሲ ተናግረዋል።"በጥይት ተመትተው የመጡ ሰዎች አሉ። አጠቃላይ ቁጥራቸው 24 ነው። ከእነዚህ መካከል የ2 ሰዎች ሕይወት አልፏል" ብለዋል። ዶ/ር ሳዳም "ከሞቱት መካከል አንዷ ትልቅ ሴት ነች። በ40ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ ትሆናለች። ጀርባዋን ተመትታ ነው የተገደለችው። ሌላኛው በ20ዎቹ ውስጥ የሚገኝ ወጣት ወንድ ነው። እሱም ከጀርባው ነው የተመታው" ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ዶ/ር ሳዳም ከሆነ፤ አንድ በጽኑ የተጎዳ ወጣት ለተጨማሪ የሕክምና እርዳታ ወደ አዳማ መላኩን ተናግረው፤ የተቀሩት አብዛኛዎቹ እጃቸውን እና እግራቸውን የተመቱ እና የአጥንት መሰበር ያጋጠማቸው መሆናቸውን ገልጸዋል። ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን እንዳንገልጽ የጠየቁን የጭሮ ከተማ ነዋሪ፤ ከትናንት በስቲያ ከሰዓት 11 ሰዓት አካባቢ ቀበሌ 03 ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ ግጭት ተከስቶ እንደነበረ ተናግረዋል። ትናንትም ከጭሮ ዙሪያ በርካቶች ለተቃውሞ ወደ ጭሮ ከተማ በሚመጡበት ወቅት የመንግሥት የጸጥታ ኃይል ሰዎቹን ለመበተን ተኩስ መክፈታቸውን ተናግረዋል።


👉ድሬዳዋ

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ትናንት በሰጠው መግለጫ በከተማዋ ከተከሰተው ሁከት እና ረብሻ ጋር ተያይዞ የሁለት ሰው ህይወት ማለፉን እና በአራት ሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋ መድረሱን አስታውቋል። የከተማው ፖሊስ አስተዳደር "እኩይ አላማን ያነገቡ ኃይሎች ሰላማዊው ህብረተሰብ ውስጥ ተሸሽገው "12.12.12" በሚል ከውጪ የተሰጣቸውን የጥፋት ተልዕኮ ለማስፈፀም ላይ ታች ሲሉ የዋሉና የጣሩ ቢሆንም በጸጥታ ሃይላችን እና በሰላም ወዳዱ የከተማችን ነዋሪ ጥረት የጥፋት ድግሳቸው መና አድርጎ በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል" ብሏል በመግለጫው። የከተማው ፖሊስ ጨምሮም፤ ለከተማዋ ሰላም እና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር 'ለአፍታም ሸብረክ እንደማንል በድጋሚ ማረጋገጥ እንወዳለን' ሲል አስታውቋል።


👉አወዳይ

ትናንት እና ከትናንት በስትያ (ሰኞ 11/12/2012 እና ማክሰኞ 12/12/2012) በአወዳይ ከተማ ለተቃውሞ የወጡ ሰዎች ከመንግሥት የጸጥታ ኃይል ጋር መጋጨታቸው ተነግሯል። አንድ የአወዳይ ከተማ ነዋሪ ሰኞ እኩለ ቀን ላይ አቶ ጃዋር ታመዋል የሚለው ዜና ሲሰማ፤ 'ጃዋር መታከም አለበት፣ ከእስር መለቀቅ አለበት' የሚሉ መፈክሮችን የሚያሰሙ ወጣቶች መሰባሰብ ሲጀምሩ የመንግሥት የጸጥታ ኃይል አባላት ሰዎችን ለመበተን ተኩስ መክፈት መጀመራቸውን ለቢቢሲ ተናግሯል። "መፈክር እያሰሙ ሰልፍ ለመውጣት ሲሞክሩ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል እና መከላከያ ሰራዊት ሰዎችን ማስቆም ጀመሩ። ከዛ ተኩስ ተከፍቶ ወደ 10 ሰዎች በጥይት ተመተዋል" ያሉ ሲሆን እኚህ የዐይን እማኝ ሁለት ሰዎች በጥይት ተመትተው መገደላቸውን አስረድቷል። ማክሰኞ እለትም በአወዳይ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ሙከራ መደረጉን የከተማ ነዋሪው ለቢቢሲ ተናግሯል። "ከ4 ሰዓት ጀምሮ ሰልፍ ሲካሄድ ነበር። በሽር የሚባል አካባቢ ተኩስ ተከፍቶ አንድ ሰው ተገድሏል። ከተማው አሁን ጸጥ ብላለች። የትራንስፖርት እንቅስቃሴ የለም። ሱቆችም ዝግ ናቸው" ብሏል።


👉ሐረር

የተቃውሞ ሰልፍ እና የገበያ አድማ መደረግ አለበት የሚሉ ሰዎች ለተቃውሞ ትናንት ረፋድ ላይ ለመሰባሰብ ሲሞክሩ በመንግሥት ጦር መበተናቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል። ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ሐረር ከተማ በሚገኘው የሃረማያ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ውስጥ ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ቢቢሲ ካነጋገራቸው የሐረር ከተማ ነዋሪዎች ሰምቷል።


👉ሻሸመኔ

በተመሳሳይ በሻሸመኔ ከተማም የአቶ ጃዋር የመታመም ዜና ሲሰማ "ሰዎች እየተጯጯሁ ወደ ዋና መንገድ መውጣት" መጀመራቸው ተነግሯል። አንድ የከተማው ነዋሪ ለቢቢሲ ስትናገር፤ በተፈጠረው አለመረጋጋት ተኩስ ተከፍቶ አንድ በጥይት ተመቶ የወደቀ ወጣት መመልከቷን ተናግራለች።


👉የክልል መንግሥት ምላሽ

የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ባልቻ በበኩላቸው፤ በአርሲ እና ሃረርጌ ዞኖች ግጭት መከሰቱን ገልጸው፤ በሰው እና በንብረት ላይ ስለደረሰው የጉዳት መጠን ግን መረጃ እስካሁን እንደሌላቸው ተናግረዋል። "ስለ ሻሸመኔ ብዙ መረጃ የለኝም። እንደ ዶዶላ እና አሳሳ ባሉ ከተሞች ግን እንደዚህ አይነት [የግጭት] ምልክቶች ታይተዋል። በአወዳይም መንገድ ለመዝጋት ጥረት ተደርጎ ነበር። ይህ ግን ከሙከራ ያለፈ አይደለም" በማለት አቶ ጌታቸው ለቢቢሲ ገልፀዋል። ቃል አቀባዩ ምንም እንኳ በተለያዩ አካላት በመላው ኦሮሚያ የሚጸና የተቃውሞ እና የገበያ አድማ ጥሪዎች ቢቀርቡም ይህ ሳይሳካ መቅረቱን ተናግረዋል። "በየትኛው የኦሮሚያ አቅጣጫ የመጓዝ እቅድ ያለው መሄድ ይችላል። መንገድ የተዘጋበት አካባቢ ስለመኖሩ ምንም አይነት መረጃ የለኝም" ብለዋል አቶ ጌታቸው። "በዚህች አገር ሁሉም ሰው ከሕግ ፊት እኩል ነው። በሕግ መጠየቅ ያለበት በሕግ ይጠየቃል" ያሉት አቶ ጌታቸው፤ ሰዎች ድምጻቸውን በሰላማዊ መልኩ ማሰማት የሚፈልጉ ከሆነ ሕጋዊ ስርዓቱን ተከትለው ለሚመለከተው አካል ስለ ሰላማዊ ሰልፉ አሳውቀው ድማጻቸውን ማሰማት ይችላሉ። ከዚህ ውጪ በዘፈቀደ የሚኖርባት አገር አይደለችም" ብለዋል። "ከአሁን በኋላ በፈለጉበት እየኖሩ የአመጽ እና የመንገድ መዝጋት ጥሪ በማቅረብ ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር የሚቻል አይደለም" ሲሉም አቶ ጌታቸው አክለዋል።

Report Page