BBC

BBC

ቲክቫህ ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የሠላም ኖቤል ተሸላሚው ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታራቂና የሚያቀራርቡ ንግግሮቻቸውን ወደ ተግባር እንዲለውጧቸው ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ጠየቀ።

ቡድኑ በተጨማሪም ያለውን ውጥረት ለማርገብ አስፈላጊ ከሆነም የአፍሪካ ሕብረት ወይም የአፍሪካ መሪዎች በማሸማገሉ በኩል ተሳትፎ ሊያደርጉ ይችላሉ ከማለት በተጨማሪ በተለይ የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር የሆኑት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ ብሏል።

ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ፣ በተለይም የትግራይንና የማዕከላዊውን መንግሥት ፍጥጫ ትኩረት ሰጥቶ በገመገመበት ባለ 14 ገጽ ሰነድ እንደጠቀሰው በኦሮሚያ ክልል የሰላም መደፍረስና የፌዴራል መንግሥት ከትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳደር ጋር የገባበት ፍጥጫ በንግግር ሊፈታ ይገባል ሲል መክሯል።

አለበለዚያ ግን ተስፋ የተጣለበት ፖለቲካዊ ሽግግሩ እንቅፋት ሊገጥመው ይችላል ሲል ስጋቱን አንጸባርቋል።

በኦሮሚያ ከተሞች በቅርቡ የታዩት ሠላም መደፍረሶች ኢትዮጵያ የጀመረችውን ፖለቲካዊ ሽግግር አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችል አሳሳቢ ቀይ መብራቶች ናቸው ብሏል ድርጅቱ።

የትግራይ ክልል ልሂቃን ክልላዊ ራስን የማስተዳደር መብት በክልልላችን ምርጫ ማካሄድ ሙሉ መብት ያጎናጽፈናል የሚል አቋም እንደያዙና የፌዴራል መንግሥት በበኩሉ ሕገ መንግሥቱ ይህን እንደማይፈቅድ በመግለጹ ፍጥጫው መከሰቱን ካብራራ በኋላ ሁለቱም ወገኖች ፖለቲካዊ ጡዘቶችን እንዲያረግቡ ተማጽኗል።

ሁለቱም ወገኖች የያዙትን አቋም ያስቀመጠው ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ማዕከላዊ መንግሥት በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ላይ ለማሳደር እየሞከረ እንደሆነ የጠቀሰ ሲሆን ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ በበኩሉ ምርጫ አካሄዳለው ብሎ ዝቷል።

ሆኖም እንደ ክራይስስ ግሩፕ ከሆነ ሁለቱም የያዙት አቋም አያዋጣም። የሁለትዮሽ ንግግርንም አያበረታታም።

ሁለቱም "የገደል ጫፍ ላይ ናቸው" ያለው ድርጅቱ በብልጽግናና በህወሓት መካከል ያለው መጠላላትና ሽኩቻ በመጨረሻ የአገር ተስፋን የሚያጨልም ነው ብሎታል።

ሰነዱ የትግራይ ልሂቃን ከምርጫ ጋር በተያያዘ ካሉ ሁኔታዎች ለማትረፍ የሚያደርጉት ሙከራ አደገኛ ነው ካለ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም የአገር መሪና የሠላም ኖቤል ተሸላሚ እንደመሆናቸው ይበልጥ እርሳቸው የሞራል ልዕልናው ኖሯቸው አስታራቂ መንፈስ ያለው አንደበታቸውን (ንግግሮቻቸውን) ወደ ተግባር እንዲመነዝሩ ጠይቋል።

የፎቶው ባለመብት,ICG

ለተቃዋሚዎችም ሆነ አሁን ከእርሳቸው በተቃራኒ ለቆመው የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ፓርቲ የእርቅ ዕድሎችን እንዲያመቻቹም አሳስቧል።

በማዕከላዊው መንግሥትና በህወሓት መካከል ያለውን ፍጥጫና መከራር ለማለዘብ በሰኔ ወር የሽማግሌዎች ቡድን ሙከራ ጀምሮ እንደነበር ያስታወሰው ሰነዱ፤ ሆኖም ሁለቱም ባላቸው ግትር አቋም የተነሳ ሽምግልናውን ከበድ ላለ አካል ማስተላለፍ ሳያስፈልግ አይቅርም ብሏል።

ምናልባት ለህወሓትና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅርብ የሆኑ ስመጥር የአፍሪካ መሪዎች በሽምግልናው ላይ ቢገቡ መልካም ይመስላል ሲል ሃሳብ አቅርቧል።

ሆኖም ግን የሚመጡት ሸምጋዮች የኢትዮጵያ መንግሥታት ለውጭ ጣልቃ ገብነት ያላትን አሉታዊ አመለካት ከግምት በማስገባት ከአፍሪካ መሪዎች ሸምጋይ የሚሆኑት ርዕሳነ ብሔራት ብልህና ስልተኛ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ከወዲሁ አሳስቧል።

በዚህ ረገድ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበርና የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ አዎንታዊ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ተስፋ አድርጓል፤ ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ።

በሽምግልና የሚሳተፉ ተሰሚነት ያላቸው የአገር መሪዎች መጀመርያ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ወታደራዊ እርምጃ ቀርቶ ምንም አይነት የፋይናንስ ጫና በህወሓት ላይ እንዳያሳድር መምከር ይኖርባቸዋል ብሏል ድርጅቱ።

በተመሳሳይ መቀለ ያለውን አመራር ምርጫ የማካሄዱን ሐሳብ እንዲተው ማግባባት ይጠበቅበታል።

ሆኖም ድርጅቱ ሁለቱ ወገኖች ጽንፍ በመያዛቸው አስታራቂና አማካይ መንገድ ማግኘት ቀላይ እንደማይሆን ይጠበቃል ብሏል።

የትግራይ ክልል ምርጫ የማካሄድ ሙሉ ሥልጣን አለኝ ካለ ሁሉንም የሕግ ሂደቶች አሟጦ መጠቀም ይኖርበታል ይላል።

ለምሳሌ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ትርጉም የመስጠት ስልጣን ስላለው ክልሎች በራሳቸው ምርጫ ማካሄድ አለባቸው ወይስ የለባቸውም በሚለው ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥ ክልሉ ይግባኝ እንዲልና የሕግ መስመርን ብቻ እንዲከተል መክሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የአራት ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት የሆነውና ለሦስት አስርት ዓመታት ያህል አገሪቱን ያስተዳደረው ገዢ ፓርቲ ኢህአዴግ ከስሞ አንድ ወጥ አገራዊ ፓርቲ እንዲመሰረት አድርገዋል።

ከኢህአዴግ መክሰም በኋላ አዲስ ወደ ተመሰረትው የብልጽግና ፓርቲ መግባት ያልፈለገው በአገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የነበረው ህወሓት ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር አለመግባባት ውስጥ ቆይቷል።

በተለይም በዚህ ወር መጨረሻ ላይ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው አገራዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለሌላ ጊዜ መተላለፉን ህወሓት አምርሮ የተቃወመው ሲሆን በሚያስተዳድረው ክልል ውስጥ የተናጠል ምርጫ አካሂዳለሁ በማለቱ አለመግባባቱ እየተባባሰ ሄዷል።

Report Page